የፍትሕ ነፃነትን የሚያስከብር የመንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች ማጠናከሪያ ሕግ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸደቀ


ኅዳር 22/2004
ዓ.ም

ዲ/ን አብርሃም አንዳርጌ
  • ረቂቅ ሕጉን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚያጸድቀው ይጠበቃል፡፡

የፍትሕ ነፃነትን የሚያስከብር የመንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች ማጠናከሪያ ሕግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁ ተገለጸ፡፡

ሕጉ የጸደቀው የሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባኤ ጥቅምት 23 ቀን 2004 ዓ.ም ባደረገው ዓመታዊ የምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ሲሆን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ 30ኛውን ዓመታዊ አጠቃላይ ሰበካ ጉባኤ ሲከፍቱ በአስተላለፉት ቃለ በረከት “ውኃው ከአጠገባቸው እያለ ተጠምተው የሞቱ ብዙ ናቸው” ብለዋል፡፡ አያይዘውም የሕግ ምንጭ የሆነችው የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ፍትሕ ፍለጋ የዓለማዊውን ፍርድ ቤት ሲናፍቁና ሲያጨናንቁ ማየት ችግር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ መፍትሔውም የዳኝነት ነፃነትን የሚያስከብረውን የሕግ ረቂቅ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ  ማቅረብና  ማጽደቅ በመሆኑም ይህንኑ ማድረግ መቻሉም በማኅበረ ክርስቲያኑ ፍትሕን ለማስፈን የቆመ የመሠረት አለት ነው ብለዋል፡፡

የጠቅላይ ቤተ ክህነት ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ዋና ሰብሳቢ መልአከ ምሕረት አምኃ መኳንንት በበኩላቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከዘመነ ሕገ ልቡና ጀምሮ የሕግ ምንጭ ሁና ለትውልድና ለሀገር ያበረከተችውን ሁለንተናዊ ሥርዓት የታሪክ መዛግብቱና ሊቃውንቱ የሚመሠክሩት እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡ ይህንም መሥመር በመከተል የቤተ ክርስቲያኗን መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች እንደገና ለማቋቋምና ለማጠናከር በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና በሕግ ባለሙያዎች ተጠንቶ የተዘጋጀው ባለ 10 ገጽ የሕግ ረቂቅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኩል እውቅና አግኝቶ በሥራ ላይ እንዲውል ቅዱስ ሲኖዶስ የሕጉን ረቂቅ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን ጨምረው አስታውቀዋል፡፡

ሕጉ የሚሰጣቸውን ጠቀሜታዎች አስመልክተው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ዋና ሰብሳቢ መልአከ ምሕረት አምኃ መኳንንት ጨምረው  እንዳስታወቁት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ባሉ አገልጋዮች፣ ሠራተኞችና በተቋማቱ መካከል ለሚነሡ ክርክሮች ሕጋዊ መፍትሔ መስጠቱ፤ እንዲሁም ከሞት በኋላ በውርስ ጊዜ በተለይ የመነኮሳትን ሀብት በመፈለግ ብቻ ሕጋዊ ባልሆነ ተዛምዶ /ዝምድና/ ሰበብ የቤተ ክርስቲያንን ክብር ለማስነቀፍ ከሚሞክሩ አካላት መከላከል ስለሚያስችልና በክርክር ጊዜ የተከራካሪዎችን ሃይማኖታዊ ክብር ማስጠበቁ በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ ከ500.000 በላይ የሚሆኑትን የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ሠራተኞች መብትና ግዴታ በሕግ ለማስከበር ማገዙ የሚጠቀስ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን በራሷ ፍርድ ቤት ፍትሕ ለማስፈን የምታደርገውን ጥረት እንደሚያግዝ ይጠቅማል ብለዋል፡፡

የዳኝነት ነፃነትን የሚያስከብረው የመንፈሳዊ ፍርድ ቤቶችን ማጠናከሪያ ሕግ እንዲጸድቅ ለሥራው መቃናት ዋናው ፈቃደ እግዚአብሔር ሆኖ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የኢሉባቦርና የጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ በሰጡት ቅን አመራር የሕጉ ረቂቅ በጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባኤ ታይቶ በ30ኛው አጠቃላይ ሰበካ ጉባኤ ድጋፍ አግኝቶ ብፁዕነታቸው በሚመሩት ፍትሐዊ አመራር ተመቻችቶና ተዘጋጅቶ እንደቀረበ ለማወቅ ተችሏል፡፡