የፍቅር ምርኮዎች
ታኅሣሥ ፮፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት
ፍጹም በሆነ ልዩ የልብ ስሜትና ኃይል ከራስ በላይ ለሌላ የሚኖር ደስ የሚያሰኝ መንፈስ፣ በሥቃይ ውስጥ የሚገኝ፣ እጅግ አስደናቂ ተፈጥሮ “ፍቅር ነው!” ፍቅር ሁለመናውን ይሰጣል፤ እንደራሱ ይወዳል፤ ለወደደው ያስባል፤ ይንገላታል፤ ይሠቃያል፤ ይሞታል፡፡
የፍቅር ባለቤት ጌታ ነው፤ በፍጹም ፍቅሩ ለሰው ልጆች ባሕይሪውን ዝቅ ያደረገ፣ ፈጣሪ ሆኖ ሳለ በሰዎች መካከል የተመላለሰ፣ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ በፍርድ ሸንጎ የቀረበ፣ የተከሰሰ፣ የተንገላታ፣ ጽኑ መከራን የተቀበለ፣ በሥቃይ ተሰቅሎ የሞተው አንዱ ጌታ ለፍቅር ነውና!
ድንቅ በሆነው ፍቅሩ ስቦ ተገዚዎቹ ያደረጋቸው የፍቅር ምርኮዎች ለፍቅር የሞተውን ጌታ በፍጹም ልባቸው፣ በፍጹም ነፍሳቸው፣ በፍጹም ኃይላቸው ወደዋል፡፡ (ማቴ.፳፪፥፴፯) ከራሳቸውም አልፎ ሰውን በፍጹም ልባቸው በመውደድ እጅጉን በሆነ ብዙ ሥቃይ እርሱን መስለው ተገኝተዋል፡፡ እውነትን ወደው ሐሰትን ጠልተዋልና፤ ከምድር ተድላ ይልቅ ሥጋዊ መከራን ፈቅደዋልና፤ ለፍቅር ሲሉ ተርበዋልና፤ ተጠምተዋልና፤ ተራቁተዋልና፤ ተሰደዋልና፤ ተንገላትተዋልና፤ ተሠቃይተዋልና፤ በግፍ ተድገለዋለና የፍቅር ምርኮዎች በመጨረሻ ያበራሉ!
ጸአር፣ ገአርና ኀሣር በሞላበት በዚች ጨለማ ዓለም፣ የምድራዊ ከንቱነት ታክቷቸው፣ ብርሃን የሆነውን ወንጌል በተስፋ ሰንቀው በጽድቁ ጎዳና በሚጓዙበት ጊዜ የሚመጣባቸውን ሥቃይ ስለ ፍቅሩ የሚቀበሉ ቅዱሳን በነጻ ፈቃዳቸው ለጌታ የሚገዙ የፍቅር ምርኮዎች ናቸው፡፡ በክርስቶስ ፍቅር የተንገበገቡ፣ ልባቸው የተቃጠለ፣ አንጀታቸው የተንሰፈሰፈ አፍቃሪዎቹ ናቸው፡፡
ዕለት ዕለት ስለ እርሱ ይገፋሉ፤ እውነትን ስለመሻታቸው ስደት ልማዳቸው ነው፤ ከሐድዲያንን ጠልተው ጽድቅን ይራባሉ፤ ቀን በበረኃ ውእየት፣ ማታ በጨለማ ቁር ይሠቃያሉ፡፡ በዱር ገደል መሽገው ዘወትር አምላካቸውን ያገለግላሉ፡፡ ይህን ሁሉ ስለ ጌታ ፍቅር አደረጉት!
ፍቅር እውነት በመሆኑም የእውነት ምስክሮች ሆኑ፤ ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም ‹‹ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ፡፡ ስለ እግዚአብሔር ደማቸውን አፈሰሱ፡፡ ስለ መንግሥተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሡ›› በማለት እንደተናገረው ክሕደትና ሐሰት፣ ስርቆትና ንጥቂያ፣ ማስመሰልና ከንቱነት በበዛበት በዚች ውጥንቅጥ ዓለም ውስጥ ሲኖሩ፣ ሲገፉና ሲበደሉ ትዕግሥትን ገንዘብ አድርገው፣ በጽናት በጨለማ ውስጥ እንደ ሻማ አበሩ፡፡ (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ) በዋሻ ሆኖ እንደሚለኮስ ጧፍ፣ በድቅድቅ ጉድጓድ ውስጥ እንዳለ ፋኖስ፣ በጠባብና ትንሽ ደሳሳ ጎጆ እንደሚያበራ መብራት ሆነው ደመቁ፡፡
ቀጥተኛ በሆነችው አንዲት ርትዕት ሃይማኖት፣ ለአንድ እውነተኛ አምላክ የመገዛታቸው ምስክር የክርስቶስን መከራ መስቀልም ስለ መሸከማቸው፣ ብርሃን የሆነው ጌታ በላያቸው ያበራል፡፡ ሕይወታቸው በሙሉ እርሱን በመፍራትና በመታዘዝ፣ ስለ ፍቅሩ ሲሉ ራሳቸውን ጥለው፣ ቤተ ሰቦቻቸውን ትተው፣ ቀያቸውን ለቀው፣ በስደትና በእንግልት መኖርን ስለፈቀዱ ብርሃን የሆነው አምላክ አይለያቸውምና፡፡
መላ ቅጡ በጠፋባት በዚህች መራራ ዓለም እንደ ጨው ሆነው ያጣፍጣሉ፡፡ ሐሰተኝነት ሲበዛ እውነት እንዳይጠፋ፣ ፍርድ ሲጓደል ፍትሕ እንዳይረሳ፣ ጥላቻ በሕዝብ መካከል ሲሠርጽ ፍቅር እንዳይጠፋ ምስክሮች ይሆናሉ፡፡ ስለት ሳያስፈራቸው፣ የጥፋት ሰንሰለት ሳያስራቸው፣ ሥቃይ ሳይበግራቸው ከጠላት ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጠው እውነተኛ ስለሆነው ፈጣሪ መስክረዋል፤ ከፍቅሩም የተነሣ ጽኑ ግርፋትን ተቀብለዋል፤ ቆዳቸውን ተገፈዋል፤ በብረት መጋዝ ተቆርጠዋል፤ በፍል ውኃ ተቀቅለዋል፤ በእሳት ተቃጥለዋል፤ ‹‹….እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤ ሌሎችም መዘባበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ›› እንዲል፡፡ (ዕብ.፲፩፥፴፭)
ዘወትርም ቀራንዮን በማሰብ የጌታን ሥቃይ በእምነት መነጽር እየተመለከቱ በሚያቃጥል እንባ ልቅሶን ያበዛሉ፤ የተገረፈውን ግርፋት በማሰብ ጀርባቸውን ተገርፈዋል፤ ፊታቸውን በጥፊ ጸፍተዋል፤ ከፍቅሩ ብዛት ራሳቸውን ከቆጥና ዛፍ፣ ከድንጋይም ራሳቸውን ወርውረዋል፤ ሞተዋል፡፡ ድንቅ በመሆነው ተአምራቱ እርሱ ደግሞ ያስነሣቸዋል፤ ይፈውሳቸዋልም፡፡ (ገድለ አቡነ አቢብ)
የፍቅር ምርኮዎች የፍቅር ተገዢዎች ስለመሆናቸው በበጎ ፈቃዳቸው በነጻነት ለሚገዛ አምላክ በፍጹም ፍቅር አምልኮት ይፈጽማሉ፤ ኑሮአቸውም ሆነ ውሎአቸው፣ በፍሪሃ እግዚአብሔር መኖርን ይመርጣሉ፡፡ እርሱ መመኪያቸው ነውና ስለምንም ምን አይጨነቁም፤ አይፈሩምም፡፡ ጋሻ መከታቸው፣ ኃይል ብርታታቸው፣ ጽናት ተጋደሎአቸው አንድ ፈጣሪ ነውና፡፡ ልብሳቸውም ይሁን ምግብ መጠጣቸው እርሱ ነውና፡፡
በችግር ጊዜም ቢሆን መሻገሪያ ድልድያቸው፣ በመራቆት ሰዓት የጽድቅ ልብሳቸው፣ በመራብ ጊዜ ምግባቸው እርሱ ነው፡፡ የዘለዓለማዊ መብልና መጠጥን የሚያድል ኤልሻዳይ አምላክ የመሆኑን ምሥጢር በሚገባ የተረዱ ናቸውና ስለ ሥጋዊ መራብና መጠማት አይጨነቁም፡፡ እውነተኛ ሕይወትን የሚሰጥ ጌታ ለዘለዓለም በፍቅሩ ጠብቆ በሰላምና በነጻነት እንደሚያኖራቸው ፍጹም እምነት ያላቸው በመሆናቸው ሰማይና ምድር ለፈጠረ አንድ አምላክ ተገዝተው መኖርን የመረጡ ናቸው፡፡ በመጨረሻም ስለ ፍቅሩ በመሞት፣ መንግሥቱን በመውረስ ለዘዓለም ከእርሱ ጋር በተድላ ደስታ ይኖራሉ፡፡
የሰማዕታት የቅዱሳን ጸሎት፣ አማላጅነትና ተረዳኢነት አይለየን፤ በረከታቸው ይደረብን፤ አሜን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር!
