የፀረ ተሐድሶ አገልግሎት በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
ነሐሴ ፲፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
‹‹እንግዲህ ሒዱና በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው አሕዛብን ዅሉ አስተምሩ፤›› (ማቴ. ፳፰፥፲፱) በማለት ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባዘዘው ቃል መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ተልእኮዋ ስብከተ ወንጌልን ለዓለም ማዳረስና ያላመኑትን በማሳመን፤ ያመኑትን እንዲጸኑ በማድረግ ዅሉንም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ማቅረብ ነው፡፡ ነገር ግን አካላቸው ከውስጥ፣ ልቡናቸው ከውጭ የኾነ፤ ራሳቸውን ተሐድሶ ብለው የሚጠሩ፤ በኅቡዕም፣ በገሃድም አስተምህሮዋን የሚፃረሩና ምእመናኗን የሚያደናግሩ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ለሐዋርያዊ ተልእኮዋ እንቅፋት ኾነውባታል፡፡ ይህን የመናፍቃንን ሤራ ለመከላከልም ልዩና ወጥ አሠራር መዘርጋት ተገቢ መኾኑ ስለ ታመነበት ቅዱስ ሲኖዶስ በወርኃ ግንቦት ፳፻፰ ዓ.ም ባደረገው ምልዓተ ጉባኤ የፀረ ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ኮሚቴ እንዲቋቋም ውሳኔ አሳልፏል፡፡
የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! በዛሬው ዝግጅታችን የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ከተግባር ላይ አውለው ሐዋርያዊ ተልእኳቸውን በትጋት እያከናወኑ ከሚገኙ አህጉረ ስብከት መካከል የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ፀረ ተሐድሶ ኮሚቴ አገልግሎትን በአጭሩ ልናስታውሳችሁ ወደድን፡፡ መልካም ንባብ!
በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የሚመራው የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ዐሥራ አምስት ወረዳ አብያተ ክህነት እና ከአራት መቶ በላይ አብያተ ክርስቲያናት እንዳሉት ከጽ/ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ትፍሥሕት ሙሉጌታ ቸርነት እንደ ገለጹልን፣ ሀገረ ስብከቱ ሰበካ ጉባኤያትን በየቦታው በማዋቀር፣ ሰባክያነ ወንጌልንና ካህናትን በመመደብ የስብከተ ወንጌል ተልእኮውን በማስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንቅፋት የኾነውን የተሐድሶ ነን ባዮች መናፍቃንን እንቅስቃሴ ለመቈጣጠርም የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ተቀብሎ የፀረ ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ኮሚቴን አቋቁሞ አገልግሎቱን ቀጥሏል፡፡ ከሥራ አስኪያጁ ማብራርያ እንደ ተረዳነው ኮሚቴው የተቋቋመው ከሀገረ ስብከት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ድረስ ነው፡፡ ዓላማው ምእመናን ከኑፋቄ ትምህርት ተጠብቀው በኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ ጸንተው እንዲኖሩ ማድረግ ሲኾን፣ አባላቱም ከሀገረ ስብከቱ ሠራኞች ጀምሮ ከካህናት፣ ከሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ ከማኅበረ ቅዱሳን አባላትና ከምእመናን የተመረጡ ናቸው፡፡
‹‹የመናፍቃንን ሤራ ለማፍረስና ምእመናንን ከቅሰጣ ለመከላከል የፀረ ተሐድሶ ኮሚቴው ድርሻ የጎላ ነው›› ይላሉ ሥራ አስኪያጁ የኮሚቴውን አስፈላጊነት ሲገልጹ፡፡ ሀገረ ስብከቱ በአፋጣኝ ኮሚቴ አቋቁሞ አገልግሎት መጀመሩ እንደሚያስመሰግነው የሚያብራሩት መጋቤ ትፍሥሕት ሙሉጌታ፣ በዚህ ተግባሩም ለሌሎች አህጉረ ስብከት እንደ አብነት ከመጠቀሱ አልፎ የልምድ ተሞክሮ በማካፈል ላይ መኾኑንም አስገንዝበዋል፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን የአዳማ ማእከል ቤተ ክርስቲያን በሰጠችው አደራ መሠረት አባላቱን በማስተባበር፣ መመሪያ በማዘጋጀት፣ ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ መረጃዎችን በማቅረብና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ከሀገረ ስብከቱ ጎን ኾኖ የኮሚቴውን አገልግሎት እየደገፈ እንደሚገኝና የማእከሉ ድጋፍም ለሀገረ ስብከቱም ኾነ ለኮሚቴው ብዙ ሥራ እንዳቀለለት አስረድተዋል፡፡
በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት የናዝሬት ደብረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ካቴድራል አስተዳዳሪ ሊቀ ጉባኤ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት ወልዱ ደግሞ የፀረ ተሐድሶ ኮሚቴው ሰብሳቢ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንዳብራሩት ኮሚቴው አገልግሎቱን የጀመረው በወርኃ ታኅሣሥ ፳፻፱ ዓ.ም ሲኾን፣ ወደ አገልግሎት ከመግባቱ አስቀድሞ መተዳደርያ ሕጉንና የሥነ ምግባር ደንቡን፣ እንደዚሁም የሥልጠና ሰነዱን በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ከማጸደቁ ባሻገር ለአባላቱ የሥራ ድርሻቸውን አሳውቋል፡፡ የኮሚቴውን ዓላማ ለምእመናን ማስተዋወቅ፤ በየዐውደ ምሕረቱ የሚሰጠው ትምህርት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግና ሥልጠና መስጠት ከኮሚቴው ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ሲኾን፣ የመናፍቃንን እንቅስቃሴ፣ ጫናዎቹንና መከላከያ መንገዶቹን በማመላከት ኦርቶዶክሳዊውን አስተምህሮ ማሳወቅም በሥልጠናው የተካተቱ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ኮሚቴው፣ ካሁን ቀደም ለሀገረ ስብከቱና ለየወረዳ ቤተ ክህነቱ ሠራተኞች፣ ለካህናት፣ ለሰንበት ት/ቤት አባላትና ለማኅበረ ምእመናን የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ሥልጠናውም በናዝሬት ከተማ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሙሉ ለሙሉ የተሰጠ ሲኾን፣ በየገጠሩ ለሚኖሩ ምእመናንም በቅርብ ጊዜ እንዲዳረስ ይደረጋል፡፡
ከሰብሳቢው ገለጻ እንደ ተረዳነው ስለ መናፍቃን እንቅስቃሴ መረጃ በማሰባሰብና ለምእመናን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና በመስጠት አገልግሎቱን የጀመረው ኮሚቴው፣ ወደፊትም ይህን መንፈሳዊ ተልእኮዉን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ተግባሩን በሥርዓት ለማከናወን እንዲያመቸውም በሳምንት አንድ ቀን ጉባኤ ያካሒዳል፡፡ የኮሚቴው አባላት እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ኾነው መሥራታቸው፤ ምሥጢር ጠባቂነታቸው፤ ከራስ ሐሳብና ጥቅም ይልቅ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ የሚያስቀድሙና ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት ልምድ ያዳበሩ መኾናቸው ለአገልግሎቱ መፋጠን ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው ይላሉ ሊቀ ጉባኤ የአባላቱን ጥንካሬ በማድነቅ፡፡
ማኅበረ ምእመናን ኦርቶዶክሳዊውን አስተምህሮ በሚገባ እንዲያውቁ የሚያበቃ ትምህርትና ሥልጠና መስጠት፤ በየዐውደ ምሕረቱ የሚቀርበው ትምህርተ ወንጌል በስፋት እንዲቀጥል መደገፍ፤ የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ እንዲዳከምና ኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ እንዲስፋፋ ማድረግ፤ ሐሰተኞች መምህራንን በመከታተል ከስሕተታቸው እንዲታረሙ መምከር፤ ካልተመለሱም ተወግዘው እንዲለዩ ለቅዱስ ሲኖዶስ ማቅረብ ኮሚቴው ወደፊት ለማከናወን ያቀዳቸው ተግባራት መኾናቸውንም ሊቀ ጉባኤ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት ጨምረው ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም አፅራረ ቤተ ክርስቲያን በተለይ ራሳቸውን ‹ተሐድሶ› ብለው የሚጠሩ መናፍቃን ማን ይነካናል ብለው በድፍረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እየተሳደቡ፣ አባቶችንም እያጥላሉ እንደ ኾነ፤ የተሳሳተ ትምህርታቸውን ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ፤ ቍጥራቸውም በዘመናት ሳይኾን በቀናት እየጨመረ እንደ መጣ ጠቅሰው፣ በሀገረ ስብከቱ የፀረ ተሐድሶ ኮሚቴ የተቋቋመው እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ ይህን የመናፍቃኑን እንቅስቃሴ ለመከላከል መኾኑን አብራርተዋል፡፡
የፀረ ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ኮሚቴው ጸሐፊ አቶ ኃይለ ኢየሱስ ከበረ በበኩላቸው ኮሚቴው ከሀገረ ስብከቱ ጀምሮ እስከ አጥቢያ ድረስ ባለው መዋቅር ልዩ ልዩ ክፍሎችን የሚመሩ ሰባት አባላት እንዳሉት፤ ከክፍሎቹ መካከልም የትምህርትና ግብረ መልስ፣ መረጃና ትንተና፣ ቁጥጥርና ክትትል፣ እንደዚሁም የመርሐ ግብር ክፍል ተጠቃሾች መኾናቸውን አስታውሰው፣ የመናፍቃንን እንቅስቀሴ በሚመለከት ለወጣቶች ልዩ ሥልጠና ለመስጠት መታቀዱንም ጠቁመዋል፡፡ ጸሐፊው እንዳስረዱት፣ ኮሚቴው ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ መቋቋሙ የልምድ ማነስ፣ የመረጃ ችግር፣ የድጋፍ ሰጪ አካላት እጥረት እና የመናፍቃን እንቅስቃሴ በፍጥነት መስፋፋት ከመሰናክሎች መካከል የሚጠቀሱ ሲኾን፣ በአዎንታዊ መልኩ ከሀገረ ስብከት እስከ አጥቢያ የሚደርስ ሰፊ መዋቅር ያለው መኾኑ፤ አገልግሎቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ በስፋት መዳረሱ፤ ወጥነት ባለው አሠራር መዋቀሩ የፀረ ተሐድሶ ኮሚቴውን አገልግሎት በአርአያነት እንዲጠቀስ ያደርገዋል፡፡
በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ፣ የኮሚቴው ሰብሳቢ እና ጸሐፊው የሚከተለውን መልእክት አስተላልፈዋል፤
‹‹በቤተ ክርስቲያን ላይ ፈተና ቢበዛባትም የተመሠረተችው በክርስቶስ ደም ነውና አትሸነፍም›› የሚሉት መጋቤ ትፍሥሕት ሙሉጌታ ቸርነት፣ የኮሚቴው ዓላማ ከግብ ደርሶ የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ተልእኮ ለማፋጠን ይቻል ዘንድ አባቶች ምእመናንን ተግተው ቃለ እግዚአብሔርን እንዲያስተምሩ፤ ምእመናኑም ትክክለኛ እረኞቻቸውን በመለየት ቃሉን እንዲማሩ፤ በአጠቃላይ መላው ሕዝበ ክርስቲያን በፈተናዎች ሳይደናገጡ በጸሎት እንዲበረቱና ራሳቸውንም ሌሎችንም ከኑፋቄ ትምህርት በመጠበቅ ክርስቲያናዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
ሊቀ ጉባኤ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት ወልዱ በበኩላቸው፤‹‹ከአሁን በፊት የተሐድሶ መናፍቃን ጉዳይ የማኅበረ ቅዱሳን የፈጠራ ወሬ ነው ይባል ነበር፡፡ አሁን ግን ጉዳዩ ቤተ ክርስቲያንን የሚፈታተን መኾኑ ተደርሶበታል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም የመናፍቃኑን እንቅስቃሴ በመከላከል ረገድ ከሕዝበ ክርስቲያኑ ጋር ኾኖ የሚጠበቅበትን የልጅነት ድርሻ በመወጣት ላይ ነው፡፡ ወደፊትም በዚህ መንፈሳዊ አገልግሎቱ ሊቀጥል ይገባል›› ሲሉ አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ በተጨማሪም የፀረ ተሐድሶ ኮሚቴው ዓላማ ኦርቶዶክሳዊውን አስተምህሮ በማስጠበቅ እነርሱን ለመንግሥተ ሰማያት ማዘጋጀት እንደ ኾነ ተገንዝበው፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ምእመናን በሐሳብ፣ በገንዘብ፣ በዕውቀት፣ ወዘተ. በመሳሰሉ መንገዶች አገልግሎቱን በመደገፍ የቤተ ክርስቲያንን ችግር ሊቀርፉና የስብከተ ወንጌል ተልእኮውን ሊያስፋፉ እንደሚገባ በኮሚቴው ስም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ የሀገረ ስብከቱ፣ የየወረዳ አብያተ ክህነቱና የየሰበካ ጉባኤያቱ ሠራተኞች፤ የየሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች፣ የማኅበረ ቅዱሳንና የሌሎችም መንሳውያን ማኅበራት ድጋፍ ኮሚቴው አገልግሎቱን በአግባቡ እንዲወጣ አድርጎታል የሚሉት አቶ ኃይለ ኢየሱስ ከበረ ደግሞ፣ ለወደፊትም ከዚህ በበለጠ ውጤታማ ይኾን ዘንድ የአባቶች፣ የወንድሞችና እኅቶች ተሳትፎ እንዳይለየን ሲሉ ድጋፍ ጠይቀዋል፡፡ የፀረ ተሐድሶ ኮሚቴውን ዓላማ በፍጥነት ከግብ ለማድረስ ይቻል ዘንድም ዅሉም ምእመናን በተለይ የሰንበት ት/ቤትና የማኅበረ ቅዱሳን አባላት የመናፍቃንን እንቅስቃሴ እየተከታተሉ ለኮሚቴው እንዲያቀርቡ፤ ማኅበረ ቅዱሳንን የመሰሉ ድጋፍ ሰጪ አካላትም በቁሳቁስ፣ በገንዘብ፣ በሐሳብ፣ በመረጃ አቅርቦትና ሥልጠና በመስጠት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ በማሳሰብ ጸሐፊው መልእክታቸውን አጠቃለዋል፡፡
ዝግጅት ክፍላችንም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት አስተምህሮ ሳይበረዝና ሳይከለስ ለትውልዱ ይዳረስ ዘንድ የፀረ ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ኮሚቴ እንዲቋቋም ውሳኔ በማሳለፉ ለቅዱስ ሲኖዶስ ያለውን አክብሮት እየገለጸ፣ እንደ ምሥራቅ ሸዋ ዅሉ ሌሎች አህጉረ ስብከትም ሐዋርያዊ ተልእኮውን እንዲያስፋፉና የፀረ ተሐድሶ ኮሚቴ አቋቋመው የመናፍቃንን ሤራ እንዲከላከሉ በመደገፍ ዅላችንም የቤተ ክርስቲያናችንን አስተምህሮ የመጠበቅና የማስጠበቅ ሓላፊነታችንን እንወጣ ሲል ያሳስባል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡