የጥያቄዎቹ ምላሾች
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
መስከረም ፳፰፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? አዲሱ ዓመት እንዴት ነው? ዘመን መለወጫን አከበርን፤ ከዚያም የመስቀልን በዓል አከበርን፤ ደስ ይላል አይደል! አሁን ደግሞ ትምህርት ጀምራችኋልና መበርታት ይገባል፡፡ እንግዲህ ከአሁኑ ጀምራችሁ መምህራን የሚሰጧችሁን ትምህርት በንቃት ተከታተሉ! መጻሕፍትን አንብቡ፤ ምክንያቱም አሁን ካላጠናችሁ በኋላ ፈተናዎችን ማለፍ ይከብዳችኋል!
ታዲያ ልጆች! ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መማርንም እንዳንዘነጋ! በሰንበት ሄደን በመማር በሥነ ምግባር ያጌጠ፣ በሃይማኖቱ የጸና ጎበዝ ተማሪ ሆኖ ማደግ ያስፈልጋል፤ መልካም! ዛሬ ባለፈው ለጠየቅናችሁ ጥያቄዎች ምላሹቹን እንነግራችኋለን! አንብባችሁ ምላሽ የሰጣችሁ በርቱ! ያልመለሳችሁ ደግሞ በቀጣይ በምናዘጋጀው ጥያቄና መልስ ተሳተፉ!
፩ኛ. የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል አይሁድ በክፋት ከቀበሩት ከ፫፻ (ከሦስት መቶ) ዓመታት በኋላ በጌታ ፈቃድ ከተቀበረበት ያወጣችው ማን ናት? ለሚለው ጥያቄ ምላሹ ንግሠት እሌኒ ነው፡፡ በክርስያኖች ላይ ይደርስ ከነበረው መከራ ነጻነትን የሰጣቸው ልጇ ደግሞ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ይባላል፡፡
፪ኛ.ቅዱስ ላሊበላ ከዐለት (ከድንጋይ) ቤተ መቅደስ ሲሠራ አብራው የነበረች፣ በላስታ ላሊበላ ከሚገኙ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ቤተ አባ ሊባኖስ የተባለውን ቤተ መቅደስ የሠራችው ቅድስት መስቀል ክብራ ትባላለች፡፡
፫ኛ. ስለ ጌታችን ሲያስተምር “ለምን ታስተምራለህ” በማለት በድንጋይ የወገሩት፣ እርሱ ግን ለሚደበድቡት የጸለየላቸው ቅዱስ እስጢፋኖስ ቀዳሜ ሰማዕት ይባላል፡፡
፬ኛ. በንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ መከራ ሲመጣባት አርማንያ ወደ ተባለ አገር የተሰደደች፣ በዚያም ድርጣድስ የተባለው ንጉሥ መከራ አጽንቶባት በሃይማኖቷ ጸንታ፣ መስከረም ፳፱ ቀንም በሰይፍ ተሰይፋ ሰማዕትነት ተቀበለችው ቅድስት አርሴማ ናት፡፡
፭ኛ.እግዚአብሔር ድንቅ ነግር ስላደረገላት ዓለምን ንቃ ወደ ምንኩስና ሕይወት የገባች፣ በሰዎች ላይ ክፉ የሚያደርገውን ሰይጣን (ዲያቢሎስ) ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ የጠየቀች ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ናት፡፡
፮ኛ.ምንም ሳታጠፋ በቅናት ተነሣስተው እንድትቀጣ በሐሰት ያልሠራችውን ጥፋት ሠርታለች ብለው የወነጀሏትና ነቢዩ ዳንኤል የሐሰት ምስክሮችን ሐሰተኛነታቸውን ዐውቆ እርሷን ከሞት ያዳናት ቅድስት ሶስናን ነው፡፡
፯ኛ.ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት በሥርዓተ ጸሎት ጊዜ ልንዘጋጅባቸው የሚገቡ ውጫዊና ውሳጣዊ ዝግጅቶች የሚባሉት የሚከተሉት ናቸው?
- ውጫዊ ዝግጅት፡-ንጽሕናችንን በመጠበቅ፣ ነጠላችንን መስቀልያ መልበስ ፣መብራት( ሻማ፣ጣፍ) ማብራት፣ በቅዱሳት ስእላት ፊት ቀጥ ብሎ በመቆም መዘጋጀት
- ውስጣዊ ዝግጅት፡- ስንጸልይ በፍቅር መሆን አለበት፤ጽኑ እምነት ሊኖረን ያስፈልጋል፤ በውጣችን ደግሞ ቂም በቀል መያዝ የለብንም፡፡
፰ኛ.በሥነ ፍጥረት ትምህርታችን እግዚአብሔር በዕለተ እሑድ የፈጠራቸው ሰባቱ የብርሃን ሰማያት ስም፡- ጽርሐ አርያም፣ መንበረ መንግሥት፣ ሰማይ ውዱድ፣ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት፣ ኢዮር፣ ራማ፣ ኤረር ናቸው፡፡
፱ኛ. ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከክዋክብት የተፈጠሩት በዕለተ ረቡዕ ነው፡፡
፲ኛ. አምስቱ አዕማደ ምሥጢረት የሚባሉት የሚባሉት ምሥጢረ ሥላሴ፣ ምሥጢረ ሥጋዌ፣ ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ቁርባን፣ ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ናቸው፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ትማሩት ከነበረው ብዙ ትምህርት “የቱን ታስታውሳላቸሁ” በሚል ለጠየቅናችሁ ጥያቄዎች ምላሾቹ እነዚህ ናቸው፡፡
በሌላም ጊዜ ከምንነግራችሁ ታሪክ እንዲሁም መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ምን ያህሉን እንደተረዳችሁ ለማወቅ ጥያቄ ይዘን እንመጣለን፡፡ ወላጆቻችን ለእኛ ብዙ ነገር እያደረጉልን በትምህርታችን ጎበዝ ስንሆን፣ በሥነ ምገባር ስንታነጽ ደስ ይላቸዋልና በርትታችሁ ተማሩ፤ በሌላ ትምህርት እስክንገናኝ ቸር ይግጠመን !!!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!