የጥምቀት በዓል ፋይዳና ተግዳሮቶቹ
ለሦስት ቀናት ያህል (ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ) በተከታታይ የሚከበረው ይህ ታላቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገለጫ ከመሆኑም በላይ ለምዕመኑ በረከት የሚያስገኝ ነው።
«እልልታን የሚያውቅ ሕዝብ ምስጉን ነው» መዝ 88፥15
ይህንን ውብና ድንቅ ክብረ በዓል ለማክበር አገር ተሻግረው ሥርዓቱን ለማየት የሚመጡ የውጭ ሀገር ዜጎች ከዓመት ወደ ዓመት ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል። ይህም ጥንታዊት፣ ኦርቶዶክሳዊትንና ሐዋርያዊት የሆነችውን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያናንን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ያለው ድርሻ በዓለም ከፍተኛ መሆኑ አያጠራጥርም። በማያውቁት ሀገር እና በማያውቁት ቋንቋ በሚደረገው መጽሐፍ ቅዱሳዊና ሰማያዊ ሥነ- ሥርዓት መንፈሳዊ ሀይል ተማርከው የሚጠመቁም የውጭ ዜጎች አልጠፉም።
ጥምቀት በጎንደር
የዚህች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን የነገ ተስፋ እና የቅርሱና የሥርዓቱ ውርስ ተቀባይ የሆነው ወጣት በበዓሉ ላይ ትልቅ ተሳትፎ ያደርጋል። በዓሉ ከመከበሩ ከወራት በፊት በየሰንበት ትምህርት ቤቱ በልዩ ኮሚቴዎች የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲያደርግ ቆይቷል።
በተለይ ደግሞ በዓሉ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት አካባቢን ከማስዋብ ጀምሮ በከተማዋ ለሚገቡ እንግዶች ኢትዮጵያዊ የሆነ አቀባበልና መስተንግዶም ተደርጓል።
ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ታይቶ እና ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ ለታቦታቱ ልዩ ክብር በመስጠትም የምንጣፍ ማንጠፍ ሥነ ሥርዓትንም ጀምረዋል። ይህ አባቶችን ከማስደመም አልፎ በወጣቱ ሥነ ሥርአትም ያላቸውን እምነትም ጨምሯል። ወጣቱ ለሃይማኖቱ ያለውን ፍቅርና ተቆርቋሪነትም በግልጽ አሳይቷል።
ከዚህ ባለፈም ወጣቱ የበዓሉ ዝማሬ በመንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት እንዲከናወን ሥርዓት አልባ የሆኑና ሃይማኖታዊ መሠረት የሌላቸውን ጭፈራና ሆይታም ለማስቀረት ትልቅ እና አመርቂ የሆነ አንቅስቃሴ አድርጓል።
የዘንድሮም የጥምቀት በዓል ከመቼውም ጊዜ በላይ በደማቅ መልኩ ተከብሮ አልፏል። ከላይ በጽሑፌ ለመግለጽ እንደሞከርኩት እያንዳንዱ ዓመት የየራሱ መገለጫዎች እንዳሉት ሁሉ በዘንድሮውም አንዳንድ ለየት ያሉ ክስተቶች መታየታቸው አልቀረም።
ወደ መቶ ሺህ ገደማ የውጭ ሀገር ዜጎች፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና መንፈሳዊ ተጓዦች የታደሙበት የዘንድሮው የጥምቀት በዓል በሕዝቡ ቁጥር ረገድ ከቀድሞው ዓመታት ሁሉ የላቀ ነበር። ይህንን በቁጥር የበዛ ሰው ለማስተናገድም ሲባል በባሕረ ጥምቀቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ልዩ የሆነ የመቀመጫ ቦታ ተሰናድቶ ነበር ። ይህ በእግር ኳስ ሜዳ ውስጥ እንዳለ ክቡር ትሪቢውን ያለ የመቀመጫ ሥፍራ በአፄ ፋሲል መዋኛ ገንዳ ዙሪያ የተገነባ ነው። በዚህም ልዩ የሆነ ቦታ እንግዶች በክብር ሲስተናገዱ ውለዋል።
ያለ ምዕመናን?
ምንም እንኳን የሀገር ጎብኚዎቹ(ቱሪስቶች) ለማየት የሚመጡት ባሕረ ጥምቀቱን ካህናቱንና ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ቢሆንም ለዚህ ሁሉ ውበት የሚሰጠው ምዕመኑ ጭምር ነውና ምዕመኑም እንድ መስህብ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ስለዚህም ቢያንስ የተወሰነው ሰው ቀረብ ብሎ እንዲያይ(እንዲታደም) ቢደረግና የሕዝቡንም ጉጉት ለማስተናገድ ቢሞከር የተሻለ ይሆን ነበር። ብዙሃኑ ወጣት ለበዓሉ ዝግጅት እስፓልት ማጠብ እንኳን ሳይቀረው ደክሞ የበይ ተመልካች መሆኑ ቅር ማሰኘቱ አልቀረም። የሕዝቡ ቁጥር እንዳለ ሆኖ እንግዶች ቦታ ቦታ ከያዙ በኋላ እንኳን ምዕመኑ የሚገባው ክብር ተሠጥቶት ቢስተናገድ ተገቢ ነበር።
የአውሮፓውያን መንፈሳዊያን በዓላት ዓለማዊነት
17ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ መከበር የጀመረው ይህ ክብረ በዓል፥ የሮም ቤተ ክርስቲያን ንጹሕ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ነበር። ቀስ በቀስ ግን የአየርላንድን ባሕል ብቻ የሚያሳይ ዓለማዊ ክብረ በዓል እየሆነ መጥቷል።
የአየርላንድ የሃይማኖት መሪዎች በዓሉ ዓለማዊ ገጽታ እየተላበሰ መሄዱን ይገልጻሉ። በ2007 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ፋዘር ቪንሰንት የተባሉ አየርላንዳዊ ቄስ the world’s magazine በተባለ መጽሔት ላይ ባወጡት ጽሑፍ «በዓሉ የቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል፤ ዓላማውም ሃይማኖታዊ መሆኑን ማስገንዘቢያ ጊዜው አሁን ነው» ይላሉ።
በያዝነው የፈረንጆች አመት መጋቢት ወር ላይም በፋሽን፣ በፈንጠዝያ፣ በሙዚቃ፣ በመንገድ ላይ ቲአትሮችና በካርኒቫል ለማክበር እቅድ ተይዟል።
በሌላ ሁኔታ የ”Assumption Day” ከዚሁ ዕጣ ፈንታ አላለፈም። Assumption Day በሀገራችን ፍልሰታ ብለን የምናከብረው የእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት በዓል ነው። ዛሬ ዛሬ በስዊዘርላንድና በብዙ የአውሮፓ ሀገሮች ምንም ዓይነት የሚታይ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ሳይኖር በርችት፣ በችቦ፣ ጭፈራ፣ በህብረ ቀለማትና በመንገድ ላይ ትርዒት ብቻ የሚከበር ሆኗል።
እነዚህ በዓላት መንፈሳዊነታቸው የደበዘዘውና ሲብስም የጠፋው የምዕራባዊያን አብያተ ክርስቲያናት እንደ ቤተ ክርስቲያን መቆም ሲያቅታቸውና ተልዕኳቸው እየተዳከመ ሲሔድ መሆኑ አይረሳም። በኢትዮጵያ ግን ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቷ ሳይገታ በዓሉን በመንፈሳዊ ይዘቱ የሚያክብረው ምዕመን ሳይጠፋ ማቀላቀሉ ይጠቅም ይሆን? በጥብቅ ማሰብ ያሻል!
የበዓሉ ተግዳሮት
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለወጠ የመጣው የጥምቀት አከባበር ሌላ ትልቅ የማንነት ጥያቄም ከፊቱ ተጋርጦበት ይገኛል። ፈረንጆቹ እንዲህ አይነት የሕዝብ ስብስብ እና ሥርዓት በሃገራቸው የተለመደ ባለመሆኑ ይሄንን ክብረ በዓል ወደ ሚያውቋቸው የአደባባይ ትሪዒቶች ማጠጋጋታቸው አይቀርም። ከዚህም አንዱና ዋነኛው “ካርኒቫል” ነው። ይህ በተለይ በላቲን አሜሪካ አካባቢ የሚታወቅ የአደባባይ ትርዒት ነው። በዚህ ወቅት ብዛት ያላቸው ሰዎች ቀለም የበዛበት ወይም ለየት ያሉ አልባሳትን በመልበስ በየአደባባዩ ሲጨፍሩና ሲዝናኑ ይከርማሉ። ይህ ፍጹም አለማዊ የሆነ የአደባባይ ትርዒት ከየትኛውም መንፈሳዊ ክብረ ባህል ጋር ማወዳደር ከመቀሰፍ አያድንም።
የዘንድሮውን የጎንደር የጥምቀት በዓል ካርኒቫል እንዲኖረው አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል። ከዚህም ውስጥ ዋነኛው በየመንገዱ ላይ ጊዜአዊ ድንኳኖችና ዳሶችን በመጣል የባህላዊ መጠጥና ምግቦች መስተንግዶ ነው። እነዚህ በዋና ዋና መንገዶችና በጥምቀተ ባህሩ አቅራቢያ የተተከሉ ዳሶች ውስጥ ምግብና መጠጥ ከመስተናገዱም ባለፈ ዓለማዊ ዘፈኖችም ይከፈታሉ። ይህ መስተንግዶ ለእንግዶች ጥሩ አቀባበል ተያያዥ ጉዳቶችንም ማምጣቱ አልቀረም። ከዚህ ባለፈ የሚያስፈራው ደግሞ ይህ አካሄድ ወደ ፊት ወደ የት ሊያመራ እንደሚችል ነው። በአህዛብና በአማሌቃያውያን ጭምር የሚከበረው የጥምቀት በዓል የሕዝብ በዓል መሆኑ እንዳለ ሆኖ ሃይማኖታዊ መሠረቱ ግን መቼም ቢሆን ለአፍታ እንኳን ሊዘነጋ አይገባውም። ማንም ከየትኛውም አይነት የአደባባይ ትርዒት ጋር ቢያመሳስለው እንኳን የበዓኡን ትክክለኛ ትርጉምና አመጣጥ ማስረዳትና ማስተዋወቅ የእኛ የእምነቱ ተከታዮች ኃላፊነት ነው።
ከቱሪዝም አንፃርም ቢሆን ከፍተኛ የሃገር ውስጥ ገቢ የሚያስገኘው ይህ ክብረ በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱ ተጠብቆ እንዲቆይ ሁሉም የየራሱን ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅበታል። በዓሉም ጥንታዊነቱን ጠብቆ እንዲዘልቅ ትልቅ ጥንቃቄና ትኩረትን ይሻል።
እንግዲህ ዓለምን የሚያስደምምና የሚያማልል ሃይማኖታዊ ትውፊት ባለቤት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን የባለቤትነት ጥቅም ትሻለች። ኢትዮጵያና ቤተ ክርስቲያንን ቤተ ክርስቲያንንና ኢትዮጵያን ለይቶ ማየት ይከብዳል። ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ የምታሰኛትን ይህችን ቤተ ክርስቲያን በክብረ በዓላቱም ብቻ ሳይሆን ሁሌም ማሰብ ግድ ይላል። በአዘቦቱም ቢሆን በመላ አገሪቱ ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎች በአንድም በሌላም መንገድ ከቤተ ክርስቲያን ጋር የተገናኙ በመሆናቸው ቤተ ክርስቲያኗን መጠበቅ ሃገራዊ ግዴታ ያደርገዋል።
የቤተ ክርስቲያን ዓላማዋ ምንድን ነው?
ታቦቱ ሲወጣ ሴቶች በእልልታ ወንዶች በጭብጨባ የምናሰማው ደስታ፥ እኛ ከመሠዊያው ላይ ያገኘነውን የክርስቶስ ሥጋ በልተን ደሙን ጠጥተን ደስ ብሎናል። እናንተም ከደስታው ተካፋይ ሁኑ ማለቷ ነው፣ ቤተ ክርስቲያን።
እንደ እኔ እንደ እኔ