የጥምቀት በዓል በዮርዳኖስ ወንዝ /ለሕፃናት/

ጥር 9 ቀን 2005 ዓ.ም.
ከወልደ ኢየሱስ /ቤካ ፋንታ/

 

ልጆችዬ እንኳን ለጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ! ዛሬ ስለ ታላቁ በዓል ስለ ጥምቀት ብዙ የምነግራችሁ ነገር አለኝ፡፡ በደንብ ተከታተሉኝ እሺ፡፡

 

በገዳም ውስጥ ለሠላሳ ዓመት ለብቻው ሆኖ እግዚአብሔርን እያመሰገነ የሚኖር የእግዚአብሔር አገልጋይ ነበር፡፡ ስሙም ቅዱስ ዮሐንስ ይባላል፡፡ ልጆችዬ የቅዱስ ዮሐንስ ልብስ ምንድር መሰላችሁ የግመል ቆዳ ነበረ፣ የሚበላው ደግሞ በበረሃ የሚገኝ ማር ነው፡፡ በገዳም ሲኖር ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን በደስታ እየዘመረ ያመሰግነው ነበር፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን ከሚኖርበት ገዳም ተነሥቶ ዮርዳኖስ ወደሚባል ወንዝ እያስተማረ መጣ፡፡ ትምህርቱም “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ፡፡” የሚል ነው፡፡ ያን ጊዜ ይህንን ትምህርት የሰሙ በጣም ብዙ ሕፃናት፣ ወጣቶች እና ትልልቅ ሰዎች ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ተሰብስበው መጡና ያጠፉትን ጥፋት፣ የበደሉትን በደል፣ የሠሩትን ኃጢአት ሁሉ እየነገሩት /እየተናዘዙ/ በጸበል አጥምቀን አሉት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም የዮርዳኖስን ወንዝ በእግዚአብሔር ስም ሲባርከው ጸበል ሆነ፡፡ ከዚያም የተሰበሰቡትን ሁሉ ወንዶችን ሴቶችን እና ሕፃናትን በጸበሉ አጠመቃቸው፡፡

 

ልጆችዬ ከዚያም ምን ሆነ መሰላችሁ? ፈጣሪያችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሊጠመቅ መጣ፡፡ አጥማቂው ቅዱስ ዮሐንስም ኢየሱስ ክርስቶስን ሲያየው ፈጣሪዬ ሆይ አጥምቀኝ አለው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን አይሆንም አንተ አጥምቀኝ ብሎት በጥር 11 በቅዱስ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ፡፡ ስለዚህም አምላካችን በዚህች ቀን ስለተጠመቀ ዛሬ የምናከብረው የጥምቀት በዓላችን የተባረከ ሆነ፡፡

 

ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ ከውኃ ሲወጣ  በጣም የሚያስደንቅ ተአምር ታየ፡፡ ሰማያት ተከፈቱ፤ ከሰማዩ ውስጥም መንፈስ ቅዱስ በነጭ ርግብ ተመስሎ መጣና በጌታችንነ በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  በራሱ ላይ ተቀመጠ፡፡ ከዚያም አንድ ታላቅ ድምፅ ከሰማይ ውስጥ ተሰማ፡፡ እንዲህ የሚል “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፡፡”

 

ልጆችዬ ዛሬም እኛ ክርስቲያኖች ከጥር ዐሥር ጀምረን ነጭ የሀገር ልብስ ለብሰን ቅዱሱን ታቦት አጅበን እየዘመርን፣ እልል እያልን የምንዘምረውና በጸበል የምንጠመቀው በመስቀልም በአባቶቻችን ካህናት የምንባረከው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡

 

አገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ በሁሉም ቤተ ክርስቲያን ያሉት ታቦታት ጥር አሥር ቀን ከየቤተ ክርስቲያኑ ወጥተው ወደ ጥምቀተ ባሕር /ጸበሉ ቦታ/ ሄደው እየተዘመረ፣ እየተጸለየ በምስጋና ይታደራል፡፡ በነጋታው ጥር 11 በጠዋት ውኃው ተባርኮ ጸበል ይሆናል፡፡ በሥፍራው የተሰበሰቡትን ክርስቲያኖች ሁሉንም በጸበሉ እየረጩ ያጠምቋቸዋል፡፡ በመጨረሻም የእግዚአብሔር ማደሪያ ቅዱስ ታቦቱ በካህናቱ ዝማሬ በምእመናን እልልታ ታጅቦ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመለሳል፡፡

አሁን ደግሞ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፡-

  1. ቅዱስ ዮሐንስ የሚኖረው በየት ነበር?

  2. ጌታችን መድኃኒጻችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው የት ነው?

  3. ኢየሱስ ክርስቶስን ያጠመቀው ማን ነው?

  4. ቅዱስ ዮሐንስ ያጠመቃቸው  ወገኖች እነማን ናቸው?

ልጆችዬ ከመሰናበቴ በፊት ለዛሬ የምታነቡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ልንገራችሁ፡፡ ይኸውም የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ሦስት ነው፡፡ ስለተከታተላችሁኝ የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡ እመቤታችን ድንግል ማርያም ታሳድግልኝ፡፡ መልካም የጥምቀት በዓል ይሁንላችሁ፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር