የጥምቀት በዓል
እንኳን አደረሳችሁ!
ዲያቆን ዘሚካኤል ቸርነት
ጥር ፱፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም
ሀገራችን ኢትዮጵያ የክርስትና እምነትን በሦስቱም ሕግጋት በሕገ ልቡና፣ በሕገ ኦሪት እና በሕገ ወንጌል እግዚአብሔርን ስታመልክ ኖራለች፡፡ የክርስቶስን አምላክነት በመጀመሪያ፣ በቤተ ክርስቲያን ልደት በሚባለው በበዓለ ኀምሳ ለሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ በወረደላቸው ጊዜ በተሰበከው ስብከት ምእመናን ጋር አብረው እንደተቀበሉ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለ በዓለ ኀምሳ በተናገረበት ድርሳኑ ያስረዳል፡፡
በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ፰ ከቊጥር ፳፮ እስከ ፳፰ ላይም የተነገረው ታሪክ በ፴፬ ዓ.ም ከኢትዮጵያዊው ጃንደረባ (ባኮስ) በፊልጶስ እጅ ተጠምቆ ለኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ሐዋርያ እንደሆነ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች አውሳቢዮስ ዘቂሳሪያ እና ሄሬኔዎስ እንዲሁም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ተናግረዋል/ጽፈዋል/፡፡ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን በአብርሃ ወአጽብሐ ዘመነ መንግሥት በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተገቢው ሁኔታ መከናወን ጀመሩ፤ ክርስትና ብሔራዊ ሃይማኖት ሆነ፡፡ ነገር ግን እስከ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የጥምቀት በዓል የዚህ ዓይነት የአከባበር ሥርዓት አልነበረውም፡፡
በዐፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት ከኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ዜማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ በየዓመቱ ጥር ፲፩ ቀን ታቦታት ጠዋት ከመምበረ ክብራቸው በመነሣት ወደ ወንዝ ወርደው ማታ ወደ መንበረ ክብራቸው እንዲመለሱ ይደረግ ነበር። ይህ ሥርዓት እስከ ዛጒዌ ሥርወ መንግሥት ቀጥሏል። የሰማያዊ መቅደስን አምሳል በምድር በመሥራት በኪነ ሕንፃ ጥበቡ የከበረ ጻድቅ ቅዱስ የበዓሉ አከባበር በኢትዮጵያ ካህንና ንጉሥ የሆነው ቅዱስ ላሊበላ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ለየብቻው በሚቅርባቸው ቦታ ሲፈጽሙት የነበረውን ክብረ በዓል አስቀርቶ በአንድ ቦታ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በአንድ ላይ በመሆን በአንድ ጥምቀተ ባሕር እንዲያከብሩ ትእዛዝ አስተላልፎ እንዲከበር አድርጓል።
በዚህም ምክንያት በዓሉ በይበልጥ የተለየና የደመቀ ሥርዓት እንዲኖረው ሆነ። በተያያዘም ጻድቁንና ቅዱሱን ባሕታዊ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን በአክሱም፣ በላስታ፣ በሸንኮራ፣ በአንኮበር፣ በመቀሌና በመርጡለ ማርያም እየተዘዋወሩ ባሕረ ጥምቀቱን እንዲባርኩ አድርጓል።
በዐፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት በ ፲፫ ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያዊ ሐዋርያ፣ ጻድቅ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አሳሳቢነት ይህ ሥርዓት ተጠናክሮና ተስፋፍቶ እንዲቀጥል በዐዋጅ አስተላልፈዋል። ሕዝቡም በነቂስ ወጥቶ ያከብር ነበር። የበዓሉ አከባበር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደመቀ፣ እየሰፋና አድማሱም ብሔራዊነትን እየያዘ መጣ። የመካከለኛው ዘመን ፈርጥ ድርሰትን ከንግሥና ጋር አጣምሮ የኖረው ብዙ መንፈሳዊ ድርሳናትን ለቤተ ክርስቲያን ያስተላለፉት ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ በአንድ ቀን ሄዶ የሚመለሰው ሥርዓት ቀርቶ ጥር ፲ ቀን ታቦቱ በኪደተ እግር ወርደው ውሆችን እንዲባርኩ በዚያም እንዲያድሩ በሄዱበትም እንዳይመለሱ (ሲሄዱ የባረኩትን ያህል በሌላ ቦታ ያለውን ሲመለሱ እንዲባርኩ የሃይማኖት ጽናት ብቻ ሳይሆን የወንጌል መንግሥት መስፋፋትን እየሰበኩ እንዲመለሱ) በዐዋጅ ወሰኑ።
ምእመናንም በሆታ፣ በእልልታ፣ በይባቤ በማክበር በቦታው በማደር ሥርዓቱን ይፈፅማሉ፤ ሊቃውንቱንም ለበዓሉ የሚገባውን ቃለ እግዚአብሔር በማድረስ ያድራሉ። የሚዘመረው መዝሙር ፣ የሚነገረው ቃለ እግዚአብሔርም በጥምቀት የምናገኘውን ጸጋና በረከት የሚያመሠጥር ነው። የሚከናወነውን ሥርዓትም ሃይማኖታዊ ታሪክና ምሳሌ የሚያጠይቅ ነው። ይኸውም ታቦቱ የጌታችን፣ ታቦቱን የሚሸከመው ካህን የቅዱስ ዮሐንስ፣ ጥምቀተ ባሕሩ የዮርዳኖስ ወንዝ፣ ታቦቱን አጅበው የሚሄዱ እና በዓሉን የሚያከብሩ ምእመናን ወደ ቅዱስ ዮሐንስ እየመጡ የንስሐ ጥምቀት ሲጠመቁ የነበሩ ሰዎች ምሳሌ ናቸው። ታቦተ ከመንበረ ክብራቸው ተነሥተው ወደ ጥምቀተ ባሕሩ መውረዳቸው ጌታችን መዳኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በባሕረ ዮርዳኖስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ከማታው ጀምሮ መውረዱን ያጠይቃል።
ዐዋጅ ነጋሪ በሆነው ቅዱስ ዮሐንስ የሚመሰለው የቤተ ክርስቲያን ደወል ሲደወል ምእመናን ከልጅ እስከ ዐዋቂ በነቂስ ወጥተው በዐፀደ ቤተ ክርስቲያን ይሰባሰባሉ። ታቦቱ በተለያዩ ኅብረ ቀለማት በተሸለሙ ልብሰ ተክህኖ የደመቁ ካህናትና የመፆር መስቀል ባነገቡ ዲያቆናት ታጅበው፣ ከቤተ መቅደስ ተነሥተው ወደ ጥምቀተ ባሕሩ ይሄዳል። ካህናቱም ‹‹በፍሥሐ ወበሰላም ወረደ ወልድ እምሰማያት ውስተ ምጥማቃት›› እያሉ ጌታችን ለመጠመቅ ወደ ዮርዳኖስ መውረዱን በዝማሬያቸው ይገልጻሉ። ዕጣኑ፣ ዝማሬው፣ እልልታው፣ ጸሎቱም ታቦቱም አገሩን ይባርካሉ።
ቀድመው በጥምቀተ ባሕሩ የተገኙ ምእመናን በእልልታ እና በስግደት ይቀበላሉ። መዘምራን ዝማሬ አቅርበው፣ ቃለ ቡራኬ ተሰጥቶ፣ ታቦታቱ በተዘጋጀላቸው ማደሪያ በመንበረ ክብራቸው ያርፋሉ። ካህናቱም ለበዓሉ የሚስማማውን ቃለ ማኅሌት ሲያደርሱ ያድራሉ። ከምእመናን ወገን የበረታ በማኅሌት ያልቻለ በታቦታቱ ዙሪያ ድንኳን ከትመው ያድራሉ። የዕለቱ ቅዳሴ ተቀድሶ ሲነጋ ካህናቱ ባሕረ ጥምቀቱን ከበው መጽሐፈ ጥምቀት ይነበባል። የዕለቱ ቃለ እግዚአብሔር ደርሶ ሲያበቃ ጥምቀተ ባሕሩ የሚገኝበት ቦታ መንበረ ፓትርያርክ ከሆነ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያሊኩ፣ የመንበረ ጵጵስና ቦታ ከሆነ ሊቀ ጵጵሱ፣ ጳጳስ ጳጳሱ ይህ ካልሆነ ቆሞስ አልያም በቦታው በክብርና በማዕረግ ከፍያለ ካህን ወይም ገባሬ ሠናይ ቄስ ባሕረ ጥምቀቱን ይባርካል።
አራት የሚበሩ ጧፎች የታሰረበት መስቀል ወደ ባሕሩ ይለቀቃል፤ ይህም ጌታችን ሲጠመቅ ብርሃን የመውረዱ ምሳሌ ነው። ጸሎተ አኮቴት ደርሶ፣ ሥርዓተ ቡራኬ ከተፈፀመ በኋላ ሕዝቡ በረከት ለመቀበል ጠበሉን እየተሻሙ ይረጫሉ። በግፊያው ውስጥ ጉጉት አለ፤ በሽሚያ ውስጥ ፍቅር አለ። ረገጥኸኝ ብሎ ማንም ማንንም አይገላመጥም፤ ተገፋሁ ብሎ ቅር የሚለው ሰው የለም፤ ሁሉም የሚረጨውን ጠበል ከሰውነቱ ጋር ለማገናኘት ይጓጓል። የጠበሉን ፍንጣቂ ካገኘ ፍጹም በረከትና ሙሉ ጸጋ እንዳገኘ አምኖ ቦታውን ለሌላ ወገኑ ይለቃል። ‹‹ከሁሉ ለምትበልጥ፣ ክብርን የምታሰጥ ጸጋ ለማግኘት ትጉ›› እንዳለ ቅዱስ ያሬድ። ምእመናን ቡራኬ ካገኙ በኋላ ታቦታቱ ካደሩበት ወጥተው በተዘጋጀላቸው ቦታ ይቆማሉ። መዘምራንም ‹‹ኀዲጎ ተሰአ ወተስአተ ነገደ ቆመ ማእከለ ባሕር ገብአ ወወፅአ በሰላም፤ ዘጠና ዘጠኙን የመላእክት ነገድ ትቶ በባሕር መካከል ቆመ›› እያሉ ይዘምራሉ።
ከዚያም ቡራኬ ተሰጥቶ መንቀሳቀስ ይጀመራል፤ እልልታ መዝሙሩ፣ ሽብሸባው ውዳሴው፣ ምስጋና ጸሎቱ ይደምቃል፤ ጠጠር መጣያ እስኪጠፋ ሕዝቡ በአንድነት ያመሰግናል። ግፍያው አያሳቅቀውም፤ ለእግዚአብሔርና ለቅዱሳኑ ካለው ክብር የተነሣ ላቡን እያፈሰሰ ፍጹም ኃይል በተሞላበት ደስታ እየዘለለ እግዚአብሔርን በማመስገን ታቦቱን አጅቦ ጉዞውን ይቀጥላል። ካህናቱ ወረቡን ሲያሳምሩ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን የመለያ ልብሳቸውን ለብሰው ሲዘምሩ፣ ጎበዛዝቱም በእልልታ፣ በሆታ ሲያመሰግኑ፣ እናቶች ትሕትናና ፍቅር በተሞላበት ምስጋና በታቦቱ ፊት ሲሰግዱና ሲማልዱ ሁሉም በየድርሻው በክብር አጅቦ ያወጣውን ታቦት በክብር ይመልሳል።
ታቦቱም ከጥምቀተ ባሕሩ ተነሥተው ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄዳቸው ጌታችን ከተጠመቀ በኋላ ሳይውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ መሄዱን ያጠይቃል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በገዳመ ቆሮንቶስ ትመሰላለችና። ይህ ቅዱስ በዓል ኦርቶዶክሳዊ ሥርዓቱ ቤተ ክርስቲያናዊ ትውፊቱን የጠበቀ ሆኖ እስከ ዛሬ የደረሰ ቢሆንም በአሁን ጊዜ ግን ክርስቲያናዊ ሕይወት የራቀ ምንም ዓይነት መንፈሳዊነት ትሩፋት የሌለው ከእግዚአብሔር ጋር የማያገናኝ የመዳሪያና ዝሙትን የሚቀሰቅስ፣ መንፈሳዊ መነቃቃትን ሳይሆን ሥጋዊ ፍትወትን የሚያበረታታ፣ የበደል አከባበሮች በእያንዳንዱ ከተሞች ይስተዋላሉ፡፡ እነዚህ ድጊቶች የሥጋ ሥራ የሚባሉ ናቸው። ‹‹ሥጋ ሥራም የተጋለጠ ነው፤ እነርሱም ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ስካር፣ ዘፋኝነት፣ ይህንንም የሚመስል ነው›› እንዲል፡፡ (ገላ.፭፥፳፪)
በሌላ ቦታም መጽሐፍም እንዲህ ይላል፤ ‹‹በመንፈስ ብንኖር በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ፤›› (ገላ.፭፥፳፭) አጉል ከሆነ የሰይጣን ፈቃድ ‹‹ከመጎምጀትም ሁሉ ተጠበቁ፤›› (ሉቃ.፲፪፥፲፭) ይልቁንም ‹‹ሁላችሁ ከክፉ መንገዳችሁና ከሥራችሁ ክፋት ተመለሱ፤ እግዚአብሔርም ከዘለዓለም ወደ ዘለዓለም ለእናንተና ለአባቶቻችሁ በሰጣችሁ ምድር ተቀመጡ፡፡›› (ኤር.፳፭፥፭) ለአባቶቻችሁ በሰጣችሁ ሥርዓት ወግ ትውፊት በቤተ ክርስቲያን በክርስቲያናዊ ሕይወት ተመላለሱ። ‹‹የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞት በስካርም፣ በዘፈንም፣ ያለልክም፣ በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት በማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና።›› (፩ኛ ጴጥ.፬፥፫) አሁን ግን ‹‹መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ›› እንዲል፡፡ (፩ኛ ጴጥ.፪፥፭) ከኃጢአት ርቀን፣ በቅንነት፣ በእምነት፣ በበጎ ሕሊና እንድንመላለስ ከብርሃነ ከጥምቀት ጸጋና በረከት እንድናገኝ የአምላካችን ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን።
ስብሐት ለእግዚአብሔር ኪያነ ዘፈጠረ ከመ አምልኮ!