“የጠገበች ነፍስ የማር ወላላ ትረግጣለች፤ ለተራበች ነፍስ ግን የመረረ ነገር ሁሉ ይጣፍጣታል።” (ምሳሌ ፳፯፥፯)

በቃሉ እሱባለው
የካቲት ፲፫፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም

ንጉሥ ሰሎሞን የሰው ልጅ በጥጋብ ሲኖር ፈጣሪው እግዚአብሔርንም እንኳን እንደሚረሳ “የጠገበች ነፍስ የማር ወለላ ትረግጣለች” እያለ የጥበብ ቃልን ተናገረ። ለፈቃድ መገዛት እና ሆዳምነት ጠቢቡ እንደተናገረ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ተደጋግሞ ሲነገር በሊቃውንት አበው በተስፋ ተገልጧል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የዮሐንስ ወንጌልን በተረጎመበት ፵፭ኛ ድርሳኑ ሆዳምነት የሰው ልጆችን ወደ ዲያብሎስ መንገድ የሚወስድ የጥፋት ሁሉ መጀመሪያ እንደሆነ ይነግረናል። “ከሆዳምነት በላይ የከፋ እና አዋራጅ ምንም ነገር የለም። አእምሮን ያፈዛል፣ ነፍስን በጠፊ ሐሳብ ያስራል፣ የያዛቸውንም ሰዎች አውሮ እንዳያዩ ያግዳቸዋል።” [ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ትርጓሜ ወንጌለ ዮሐንስ፣ ድርሳን ፵፭]

ይህን ያክል አስከፊ ከሆነው ከዚህ የፈቃድ እስር ሰው ይላቀቅ ዘንድ፣ በተፈጥሮው የተሰጠውን ነጻነት ወደራሱ ይመልስ ዘንድ የድኅነት በር የሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን ከምንመስልባቸው ምግባራት ጨምራ ጾምን እንደ መድኃኒት ታቀርባለች። ጾም የሥርዓተ አምልኮዋ አንድ አካል አድርጋው ሥርዓት ሠርታ እና አዘጋጅታ፣ ቀኖና ቀንና ለአማንያኑ ታስተምራለች። ያለንበት ጊዜም ዐቢይ ጸም የሚጀመርበት በመሆኑ በዚህ ጽሑፍ ጾም ስንል ምን ማለታችን ነው? ዓላማው ምንድን ነው? ስንጾም ምን ማድረግ ይገባናል? የሚሉ ጉዳዮችን ለማየት እንሞክራለን።

የጾም ትርጉም

ቤተ ክርስቲያናችን እንደ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ምንጭ የምትጠቀመው ፍትሐ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፲፭ ላይ ጾምን እንደ አንድ ርእስ አድርጎ ያነሳል። ጾምን ሲተረጉመውም “ጾምስ በሕግ ውስጥ በታወቀው ጊዜ ሰው ከምግብ መከልከል፤ በደሉን ለማስተስረይ፣ ዋጋውን ለማብዛት፣ እርሱን ወዶ ሕግን ለሠራለት እየታዘዘ፣ የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ ለነባቢት ነፍሱም ትታዘዝ ዘንድ ነው” በማለት የጾምን ምሥጢር ያብራራዋል። በዚህ የጾም ትርጉም ውስጥ የጾምን ትርጉም ስናስብ መያዝ ያለብንን ሁለት ሐሳቦች በጎላ እና በተረዳ ነገር እንድናይ ይጋብዘናል።

የመጀመርያው ከሰውነት ፈቃዳት ዋነኛው የሆነውን መብልን በታወቀ ሰዓት (በተወሰነ ጊዜ) መከልከልን ነው። ይህ መሠረታዊው የጾም ትርጉም ሲሆን በብሉይ ኪዳንም ይሁን በሐዲስ ኪዳን በአምልኮተ እግዚአብሔር የኖሩ አበው ይህንን ይዘው ወቅት እና ጊዜ ለይተው ከምግብ እና ከሚያሰክር መጠጥ፣ በሥጋ ላይ ምቾት ሊያመጣ ከሚችል ከማንኛውም ዓይነት መባልዕት ይከለከሉ ነበር። (ዳንኤል ፲፥፪-፫፣ ፪ኛ ዜና ፳፥፫-፬፣ ዮናስ ፫፥፭-፲፣ ዕዝራ ፰፥፳፩-፳፫፣ ማቴዎስ ፮፥፲፮-፲፰፣ ፱፥፲፬-፲፭፣ ሐዋ. ፲፫፥፪-፫፣ ፲፬፥፳፫ ን ይመልከቱ]

ሁለተኛው በዚያው በፍትሐ ነገሥት የጾም ትርጉም (አንቀጽ ፲፭) “እርሱን ወዶ ሕግን ለሠራለት እየታዘዘ” የሚለው ውስጥ የምናገኘው ዕለት ዕለት የምናደርገውን ነው። ሰው ጾሙ ጾም የሚባለው ራስን በመግዛት፣ ራስን እግዚአብሔር ለሰጠን ዓላማ በማስጠመድ እና ለእርሱ ፍቅር ራስን ጽሙድ በማድረግ መግለጥ ሲችል ነው። ይህ የጾም መዳረሻ ትርጉሙም ነው፤ ሰው ጾምን የእውነት ጾመ የሚባለው ሕዋሳቱን ከኃጢአት እና ከዚህ ዓለም ሐሳብ ማራቅ እና ከእነርሱም መጾም ሲጀምር ጭምር ነው። ቅዱስ ያሬድ “ይጹም ዓይን፤ ይጹም ልሳን፤ ዕዝንኒ ይጹም እምሰሚዓ ሕሡም በተፋቅሮ ዓይን ክፉ ከማየት ይጹም፤ አንደበት ክፉ ከመናገር ጆሮም ክፉ ከመስማት ይጹም“ እያለ እንደሚዘምር አብረነው በሥርዓተ አምልኮ የምንሳተፍ እኛ ክርስቲያኖችም በዓይናችን ክፉ ከማየት፣ በአፋችን ክፉ ከመናገር፣ በጆሮቻችን ክፉ ከመስማት እንታቀባለን። [ጾመ ድጓ ዘዘወረደ ዘሠሉስ]

እነዚህ የጾም ትርጉሞች እንደ እንግዳ ደራሽ የተገኙ አይደሉም። እግዚአብሔር የሰው ልጅን በመልኩ በፈጠረው፤ በንጉሥ ግብር በዚህ ዓለም ላይ ሾሞ በገነት ባኖረው ጊዜ በሚገዛው ዓለም ፍቅር ተታሎ ሕይወት የሰጠውን ክብሩን እርሱ ፈጣሪውን እንዳይረሳ ከሕግ ሁሉ ቀዳሚ አድርጎ የጾምን ትእዛዝ ሰጥቶታል። (ዘፍ. ፪፥፲፯) ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ ይህ እግዚአብሔር የሰጠው የቀደመ ትእዛዝ አስቀድመን የተናገርናቸውን (ከምግብ መከልከል እና ራስን መግዛትን) እንደያዘ “ጾም ሰው ከመሆን እኩል ዕድሜ ያለው ነው፣ በገነት ውስጥ የተሰጠ ነው። አዳም “ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ” ተብሎ የተቀበለው የመጀምሪያው ትእዛዝ ነው። ‘አትብላ’ በማለት ጾምና ራስን መግዛትን ሰጠው” እያለ ያብራራልናል። [ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ፣ ድርሳን ቀዳማዊ በእንተ ጾም፣ አንቀጽ ፫] አሁንም እኒህን አንድ አድርጋ ቤተ ክርስቲያናችን ጾምን ታውጃለች።

የጾም ዓላማው ምንድን ነው?

ጾም በራሱ የመጨረሻ ግብ አይደለም። “ጾመኛ ነኝ” ለማለት የምናደርገው ግብር አይደለም፥ ይህን የፈሪሳውያንን ግብር ጌታ ተቃውሞታልና። የምንጾመው ሰውነታችንን ለመጉዳት አይደለም፥ እግዚአብሔር የእኛ ሰውነት መጉዳት የሚያስደስተው አይደለምና። ከሁሉ በላይ የከፋው ደግሞ በዘመናችን “ሳይንስም እኮ ‘ጾም ለሰውነት፣ ለአእምሮ መልካም ነው።’ ብሏል” ብሎ የጾምን ዓላማ አጣመን እንድንረዳ የሚያደርግ ብሒል በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ ይስተዋላል። እኛ ግን የምንጾመው ለእኒህ ሁሉ ምክንያት አይደለም፣ ሳይንስ “ጾም እንዲህ ወይም እንዲያ” ነው ስላለ ሊሆን አይችልም። ጾም መሠረቱ መንፈሳዊነት ነው፣ እግዚአብሔር ጾምን ለቤተክርስቲያን የሰጠባቸው መሰረታዊ ምክንያቶች፦

፩. የፈቲው ኀይል ለማድከም

ሰውነታችን ይህንን ዓለም እና በውስጧ ያሉ ነገሮችን የሚገነዘብበት እና የሚያስተውልበት የስሜት ሕዋሳት አሉት። ሰው በእነዚህ ሕዋሳቱ እውነተኛውን እግዚአብሔር በፍጥረት ውስጥ ያስቀመጠውን የእርሱን ሐሳብ እንዲረዳበት ነበር የሰጠው። የሰው ልጅ ግን በራሱ ሐሳብ እና ፈቃድ እኒህን ተፈጥሮአዊ ፍላጎቶች እና ሕዋሳት ለተፈጠሩበት ዓላማ ከመጠቀም ይልቅ፣ ከእነዚህ ዓለም ውጪ ሌላ ምንም እንደሌለ በማሰብ፣ ለዓለማዊ ፍላጎቶች ራሱን ባርያ አድርጎላቸው ይገኛል። እነዚህን ስጦታዎችን (ሕዋሳቶቻችንን ) እግዚአብሔርን ለማመስገኛ እና ወደ እርሱ የማደጊያ አድርጎ ከመጠቀም ይልቅ፣ የዓለምን ቁሳዊ ጥቅም ብቻ የምናጋብስበት መንገድ አድርገን ተቀምጠናል። ይህንን ባሩያ አድርጎ ያስቀረንን ፈቲው ለማድከም እግዚአብሔር የሰጠንን የመምረጥ ነጻነት ወደራሳችን ዳግም እንድንመልስ የምንወደውን ነገር ምግብን በፈቃድ እንቢ በማለት ከእንሰሳትም ከፍ ያልን እንድንሆን ጾምን እንጾማለን። ምግብን በፈቃድ እንቢ በማለት ውስጥ ስሜቶቻችንን እንቢ ማለትን እንለማመዳለን።

፪. መልካም መንፈሳዊ ግብርን ገንዘብ ለማድረግ

ጾም በመታዘዝ ውስጥ የሚፈጸም ግብር ስለሆነም፣ በጾም ጊዜ የምንይዘው ዓላማችን እግዚአብሔር እንድናደርግ ያዘዘንን ተያያዥ ምግባራት እንድንይዝ ያደርገናል። ለዚህም ነው መንፈሳዊ ልምምድ በጾም ወቅት የግድ እና አይቀሬ ሆኖ የሚታዘዘው። ጿሚውም ሰው ራስን በመግዛት ውስጥ በሌላ ጊዜ አልቻል ያሉትን መንፈሳዊ ምግባራት(ጸሎት፣ ምጽዋት፣ ትሕትና) ከዓለማዊ ሐሳብ ራሱን ባቀበ ጊዜ ለማድረግ ይበልጥ ቀላል ይሆንለታል። የሚጾም ሰው ይበልጥ ወደነኚህ ምግባራት ይሳባል። ለዚህም ነው ቅዱስ ያሬድ “እስመ ጾም ዐቢይ በቁዔት ባቲ ታግዕዘክሙ ነፍስክሙ እምኃጢአት ትሜህሮሙ ለወራዙት ጽሙና ዛቲ ጾም ቅድስት ትፈሪ ሰላመ ወተዓሥዮሙ ትፍሥሕተ – ጾም ታላቅ ጠቀሜታ አላት፣ ነፍሳችሁን ከኃጢአት ነጻ ታወጣታለች፣ ለወጣቶችም ርጋታንና ራስን መግዛትን ታስተምራቸዋለች፡፡ ይህች ጾም ቅድስት ናት፣ ሰላምን ታፈራለች፤ ለሚያደርጋት ሰው ደስታን ትሰጠዋለች” በማለት የሚናገረው። (ቅዱስ ያሬድ፣ ጾመ ድጓ ዘቅድስት፣ ዘሐሙስ)

በቅዱሳት መጻሕፍት ተጽፎ እንደምናገኘውም በብሉይ ኪዳን የነበሩ የእግዚአብሔር ነቢያት (እነ ሙሴ፣ እነ ኤልያስ፣ እነ ዳንኤል) መልካም ምግባር ከመጀመራቸው በፊት ጾመዋል፣ በዚህም መንፈሳዊ ጥቅምን ስለመጠቀማቸው “እስመ በጾም ኤልያስ ሰማያተ ዐርገ፤ በጾም ኤልያስ ወደሰማይ ዐረገ” እያለ እንዚራ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ያሬድ የሚነግረን (ጾመ ድጓ ዘዘወረደ፥ ዘሰንበት)። በሐዲስ ኪዳንም የእምነታችን ጀማሪ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማስተማር አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት እንደጾመ ወንጌል ሲነግረን (ማቴ. ፬፥፩-፲፩) ሐዋርያቱም ይህንኑ የጌታን ግብር በመያዝ ከአገልግሎታቸው በፊት በመጾም ምሳሌ ትተውልን አልፈዋል። (ሐዋ. ፲፫፥፭-፫)

፫. ፍቅረ እግዚአብሔር በልባችን እንዲጨምር ያግዛል

ከዚህ በፊት የነበሩትን የጾም ዓላማዎች ሁሉ መያዛችን ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ለመጨመር ነው። ስለዚህም ጾም እኛ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ለማጠንከር የምንፈጽመው ግብር ነው። የሚጾም ሰው በመጾም ውስጥ ወደራሱ በሚመልሰው ነጻ ፈቃዱ ፍጥረተ ዓለም ውስጥ ያሉ ነገሮችን ካላቸው ጊዜያዊ ሁነት በተጨማሪ ያላቸውን ከፍ ያለ ትርጉም እንዲገነዘብ በር ይከፈትለታል። በፍጥረት ውስጥ፣ አጠገቡ ባለው ወንድሙ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት የሚገኘው የእግዚአብሔር ምሥጢር ክፍት ስለሚሆንለት ይበልጥ እግዚአብሔርን ወደማወቅ፣ እርሱን ወደ ማመስገን እና እርሱን ወደ ማፍቀር ይደርሳል። በዚህም ምክንያት ጭምር ነው ታላላቅ የድኅነት ምሥጢራት ከተፈጸሙባቸው ከበዓላት በፊት ከበዓላቱ ምሥጢር ጋር ለመሳተፍ እንዲያግዘን ሁለንተናችን ወደዚያ እንዲጓዝ እንዲችል ጭምር ጾም አስቀድሞ የሚታወጀው። ይህንን በተመለከትም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በተደጋጋሚ በጾመ ድጓ ድርሰቱ “ንጹም ጾመ ወናፍቅር ቢጸነ ወናክብር ሰንበቶ ለእግዚእነ፤ ጾምን እንጹም፣ ባልንጀራችንን እንውደድ፤ የጌታንም ሰንበት እናክብር” እያለ የሚያውጀው። በሚመጣውም የጌታ ትንሣኤ በዓልን ለማክበር ዐቢይ ጾም ብላ ቤተክርስቲያን የማወጁ ምሥጢር ከዚህ ጋር በእጅጉ ይቆራኛል።

ታድያ እንዲህ የምንጠብቀውን ጾም እንዴት እንጹም?

የምንጾማት ጾም ወደ ጽድቅ የምታደርስ በር፣ ሰውነትን በዓለማዊ ምኞት ከመታጠር የምንጠብቅባት ጥሩር እንደመሆኗ፣ ይህችን ጾም ስንጾም እንዴት መጾም እንዳለብን በጥቂቱ እንመልከት።

፩. የምንጾምበትን ዓላማ ማስታወስ

ሁልጊዜም ጾምን ከመጀመራችን በፊት ያለውን ሳምንት ቤተ ክርስቲያናችን ቅበላ ብላ በሥርዓተ አምልኮ ጊዜ ሰሌዳዋ አካታለች፣ ይህ የሆነበት ምክንያትም ጾም መምጣቱን አስበን ለዚያ የሚገባ መንፈሳዊ ዝግጅት እንድናደርግበት ነበር። ግን በተለይ በዘመናችን መንፈሳዊውን የጾምንም ጣዕም ጭምር እንዳናጣጥም በሚከለክል መልኩ እስከጾም መግቢያ ዕለት ድረስ መባልዕት በማግበስበስ፣ በስካር እና በኃጢአት እያሳለፍነው እንገኛለን። ይህ በራሱ ኃጢአት ከመሆን አልፎ “የጠገበች ነፍስ የማር ወላላ ትረግጣለች” እንዲል ጾማችንን ሁሉ የዓለምን ጣዕም እየናፈቅን እንድናሳልፈው ይዞ ማስቀረቱ እሙን ነው። ይህ የመሆኑ መሠረታዊ መንሥኤው ደግሞ በልምድ ጾም ደርሷል ከማለት በዘለለ፣ የጾምን ዓላማዎች በልባችን ባለመያዛችን ነው። በዚህ እኛ እንኳን ለምን እንደምንጾም በረሳነው ጾም “እግዚአብሔር ለምን አልተመለከተንም” ማለትም በእግዚአብሔር ከመዘባበት ከቶ አይለይም። ስለዚህም ጾምን ከመጀመራችን በፊት ከላይ የዘረዘርናቸውን የጾም ዓላማዎችን በቅበላ ጊዜ ማስታወስ፣ እንዳንረሳው ከመምህረ ንስሐ፣ ከቤተሰብ ከጓደኛ ጋር መጨዋወት በኋላ ለሚኖረን የሠመረ ጾም መሠረት የሚጥል ነው።

፪. ግብ ማስቀመጥ

ጾም ዓላማው በሚታይ የፈቲውን ኃይል ለማድከም፣ መንፈሳዊ ምግባርን ገንዘብ ለማድረግ ነው ብለን ከላይ ተመልክተን ነበር። ስለዚህም አንድ ክርስቲያን ጾምን ሲጾም ሊተወው የሚፈልገውን ኃጢአት፣ ሊይዘው የሚፈልገውን ምግባር አስቀድሞ ቢያቅድ እና እርሱን እያሰበ ቢጾም በሥውርም በግልጥም የሰራው በደል ይቅር ይባልለታል፤ እግዚአብሔርም ወደ እርሱ እና ወደ ጾሙ ይመለከታል። ያች ጾምም የበደል ማስተስረያ የተወደደች መሥዋዕት ሆና ትቀርባለች። መብል ያመጣችብንን የሞት ደብዳቤ መብልን በፈቃድ በመከልከል ወደ ልዕልና እና ወደ ጥንተ ባሕርያችን ማደግ እና የክብር አክሊል ከሚሸለሙት ንጹሐን ጋር ራስን ለመደመር መትጋት፣ ግባችንን የክርስቶስን የፍቅር መዓዛ አድርጎ በዚህ በተቀደሰ ጾም የተወደደ መሥዋዕት ማቅረብ ይገባል።

አምላካችን እግዚአብሔር ከጾሙ ረድኤት በረከት ይክፈለን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!