የግቢ ጉባኤያት ተተኪ ሰባኪያነ ወንጌል ተመረቁ

 መስከረም 12 ቀን 2007 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

በአምስት የማኅበረ ቅዱሳን ማስተባበሪያ ማእከላት አስተባባሪነት በስድስት የሥልጠና ቦታዎች ለአንድ ወር ሲሰጣቸው የነበረውን የደረጃ ሁለት ሥልጠና በማጠናቀቅ 357 የግቢ ጉባኤያት ተተኪ ሰባክያነ ወንጌል ተመረቁ፡፡

በአማርኛ ቋንቋ በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምና የካህናት ማሠልጠኛ 70፤ በሐዋሳ ደብረ ታቦር ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን 45፤ በጅማ ፍኖተ ብርሃን የካህናት ማሠልጠኛ 42፤ በማይጨው የካህናት ማሠልጠኛ 34፤ በባሕር ዳር ሰላም አርጊው ቅድስት ማርያም 83 ሠልጣኞች የሠለጠኑ ሲሆን፤ በኦሮምኛ ቋንቋ በአሰላ ደብር ቅዱስ ደብረ መዓዛ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም የካህናት ማሠልጠኛ 83 የግቢ ጉባኤያት ተተኪ ሰባክያነ ወንጌል ሥልጠና ወስደው ተመርቀዋል፡፡

በሐዋሳ ደብረ ታቦር ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን በተሠጠው ሥልጠና ብፁዕ አቡነ ገብርኤል የሲዳማ፣ ጌዲኦ፣ አማሮና ቡርጂ ሀገረ ሰብከት ሊቀ ጳጳስ፤ በማይጨው የካህናት ማሠልጠኛ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የደቡባዊ እና ደቡባዊ ምሥራቅ ትግራይ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለተተኪ ሰባክያነ ወንጌል ሥልጠና በመሥጠት ተሳትፈዋል፡፡ እንዲሁም በቂ ልምድ እና ዕውቀት ባላቸው መምህራን ሥልጠናው መሰጠቱን፤ ሲመረቁም በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተባርከው የምሥክር ወረቀት መቀበላቸውን ከየሀገረ ስብከቱ ማእከላት የደረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በሐዋሳ ጳጉሜን 2 ቀን 2006 ዓ.ም በደቡብ ማእከላት ማስተባበሪያ አማካይነት ከግቢ ጉባኤያት ለተወጣጡት 45 ተተኪ ሰባክያነ ወንጌል ብፁዕ አቡነ ገብርኤል የሲዳማ፣ ጌዲኦ፣ አማሮና ቡርጂ ሀገረ ሰብከት ሊቀ ጳጳስ ለተመራቂዎቹ የምሥክር ወረቀት ከሰጡ በኋላ ባስተላለፉት መልእክት ”ቤተ ክርስቲያን ከመቼውም ጊዜ በላይ ዛሬ እንደ እናንተ አይነት አገልጋዮች ያስፈልጓታል፡፡ የተሰጣችሁ ሓላፊነትም ታላቅ ነው“ ብለዋል፡፡

በቀንና በማታ ሲሰጥ የቆየው የክፍል ውስጥ ሥልጠና ነገረ ሃይማኖት፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፤ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፤ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እና ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን፤ ትምህርተ ክርስትና እና ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር፤ ነገረ ቅዱሳን፤ ሐዋርያዊ ተልእኮ፤ ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ችግሮችን ከመፍታት አንጻር የሰባክያነ ወንጌል ድርሻና ያሬዳዊ መዝሙር ያካተተ ነበር፡፡ በተጨማሪም የተግባር ላይ ሥልጠናና የእርስ በርስ የልምድ ልውውጥ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

ከ1991 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2006 ዓ.ም. በተካሄዱት የ6ዙር ሥልጠናዎች 2301 በአማርኛ፤ 453 በኦሮምኛ ቋንቋዎች በድምሩ 2754 ተተኪ የግቢ ጉባኤያት መምህራንን ማፍራት መቻሉን በማኅበረ ቅዱሳን በትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የስብከተ ወንጌልና የሥልጠና ማስተባበሪያ ክፍል ገልጿል፡: