የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች የንስሐ አባቶች ሴሚናር ተካሔደ

በ ዲ/ን  ኅሩይ ባየ

kahinatSeltenaበማኅበረ ቅዱሳን አዘጋጅነት ከጥር 16-18 ቀን 2004 ዓ.ም ድረስ  የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች የንስሐ አባቶች ሴሚናር   በማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል  ተካሔደ ፡፡

 

በማኅበረ ቅዱሳን የሀገር ውስጥ ማዕከላት ግቢ ጉባኤያት ማደራጃና ማስተባበሪያ ዋና ክፍል ሓላፊ የሆኑት ዲያቆን አንዱአምላክ ይበልጣል እንደገለጡት የንስሐ አባቶች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ተማሪዎችን ዘመኑን የዋጀ ትምህርት እንዲያስተምሩና አባታዊ ተልእኳቸውን እንዲወጡ ሴሚናሩ እንደሚያግዛቸው አብራርተዋል፡፡ በተጨማሪም በሥልጠናው ላይ የተገኙ ካህናት ከተለያዩ ቦታ የመጡ በመሆናቸው በአንድ የሥልጠና ቦታ ተገኝተው ልምዳቸውን እንዲለዋወጡና እንዲመካከሩ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ሴሚናር መሆኑን ገልጠዋል፡፡

ከደብረ ታቦር፣ መቀሌ፣ ሽሬ፣ ደሴ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ወሊሶ፣ አሰበ ተፈሪ፣ ጋምቤላ፣ ድሬዳዋ፣ ሐዋሳ፣ ፍቼ፣ ባሕርዳር፣ ሚዛንተፈሪ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ጅማ፣ መቱ፣ ሰቆጣ፣ ሎጊያ፣ ዲላ፣ ደብረ ብርሃን እና ከአዲስ አበባ የተገኙ 53 ካህናት በሴሚናሩ ተሳትፈዋል፡፡

የሴሚናሩ መርሐ ግብር እንደሚያመለክተው ለተከታታይ 3 ቀናት “የቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ሁኔታ ከተልእኮዋ አንጻር፣ የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ በማስፈጸም ረገድ የንስሐ አባቶች ሚና ምን መሆን እንዳለበት፣ የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ተሞክሮ የንስሐ ልጆቻቸውን ከመጠበቅ አንጻር ያላቸው ተልእኮ እንዲፋጠን ለማድረግ፣ ሉላዊነት እና ዓለማዊነት፣ መንፈሳዊ የምክር አገልግሎት ከሌሎች የምክር ዐይነቶች የሚለይበትን ጠባይ ምን እንደሆነ፣ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች መንፈሳዊ ዕድገት ለቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ እድገት ያለው ሚና፣ እና ማኅበረ ቅዱሳን በግቢ ጉባኤያት ያለው አገልግሎት የሚሉ ዐበይት ጉዳዮች በተያዘላቸው ጊዜ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ሴሚናሩ በተጀመረበት ዕለት ካህናቱ የሕዝብ መሪ ከመሆናቸው አንጻር እንዲህ ዐይነቱ የውይይት መርሐ ግብር እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ መሆኑን ተሳታፊዎች ገልጠዋል፡፡ “አንድ በግ ከሚመራቸው አንድ መቶ አናብስት ይልቅ አንድ አንበሳ የሚመራቸውን አንድ መቶ በጎችን እፈራለሁ” እንደሚባለው፡፡ ጌታ በወንጌል በጎቼን ጠብቅ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ፣ ግልግሎቼን ጠብቅ ብሎ አደራ የሰጠው ለካህናቱ በመሆኑ የጠባቂነት አደራቸውን እንዲወጡ ሴሚናሩ አስገንዝቧል፡፡ ካህናቱ የልጆቻቸውን ሥነ ልቡና ከመረዳት አኳያ ተፈላጊውን ክብካቤ የሚያደርጉበትን መንገድ ማሰብ እንዳለባቸው ሴሚናሩን ያቀረቡት ሊቃውንት አብራርተዋል፡፡

ለሦስት ተከታታይ ዕለታት የዘለቀው ሴሚናር በብሔራዊ ሙዚየም ጉብኝት ከተከናወነ በኋላ ተጠናቅቋል፡፡