የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፪
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
ሚያዝያ ፲፪ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም
ቅዱስ ጳውሎስ ጋብቻ የፈቃድ ሕግ መኾኑን ሲያስተምር ራሳቸውን መጠበቅ ለሚችሉ አለማግባት ቢቻልም ሰውነትን ለመጠበቅ ከአልተቻለ ግን ማግባት እንደሚሻል አስገንዝቧል፡፡ ሐዋርያው እንዳስተማረው ከሴት ጋር አለመገናኘት (ጋብቻ አለመምሥረት) ለሰው መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ወንድ አንድ ሚስት ሊኖረው፤ ለእያንዳንዲቱ ሴት ደግሞ አንድ ባል ሊኖራት ይገባል፡፡ ነገር ግን ሰው ዂሉ እግዚአብሔር እንዳደለው (እንደ ፈቀደለት) ይኑር፡፡
ላላገቡና ለመበለቶች ደግሞ የሚከተለዉን ትምህርት ሰጥቷል፤ “ላላገቡና ለመበለቶች ግን እላለሁ፤ እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ራሳቸውን መግዛት ባይችሉ ያግቡ፤ በምኞት ከመቃጠል መጋባት ይሻላልና፡፡” ይኸውም “ሚስት የሌላቸው ወንዶች፣ ባል የሌላቸው ሴቶች እንደ እኔ ከሴት (ከወንድ) ርቆ፣ ንጽሕ ጠብቆ መኖር ይሻላቸዋል፡፡ ንጽሕ ጠብቆ፣ ከሴት (ከወንድ) ርቆ መኖር ባይቻላቸው አግብተው ይኑሩ፡፡ አንዲት ሴት (ባል) አግብታችሁ፣ በሕግ ተወስናችሁ ኑሩ ማለቴ ንጽሕ ጠብቆ፣ ከሴት ርቆ መኖር ለማይቻላቸው ሰዎች ነው፡፡ ‹እንደ እኔ ንጽሕ ጠብቃችሁ፣ ከሴት ርቃችሁ ኑሩ› ብዬ አላስገድዳችሁም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር እንዳደላችሁ ኑሩ፤” ማለቱ ነው (፩ኛ ቆሮ. ፯፥፩-፱፣ አንድምታ ትርጓሜ)፡፡
ሐዋርያው፣ ቈነጃጅት ባል አግብተው፣ ልጆች ወልደው፣ ቤት፣ ንብረት ይዘው ቢኖሩ መልካም መኾኑን ጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም ሳይናወጥ በልቡ የጸና ግን የማግባት ግዴታ እንደደሌለበትና የወደደውን ማድረግ እንደ ተፈቀደለት ማለትም ድንግልናውን ጠብቆ መኖር ከፈለገ በምንኵስና፤ ማግባት ከፈለገም በጋብቻ ሕይወት ጸንቶ መኖር እንደሚችል አስረድቷል፡፡ ትምህርቱም ወንዶችን ብቻ ሳይኾን ሴቶችንም የሚመለከት ነው (፩ኛ ቆሮ. ፯፥፴፯-፴፰)፡፡ ይህም ጋብቻ የፈቃድ እንጂ የግዴታ ሕግ አለመኾኑን ያመለክታል፡፡
ከትምህርቱ እንደምንረዳው ጋብቻ በሰው ፍላጎት ብቻ ሳይኾን በእግዚአሔር ፈቃድና ዕቅድ የተመሠረተ መንፈሳዊ ሥርዓት ነው፡፡ ሕይወቱ ከምድራዊ አንድነት ባሻገር ለምሥጢረ ተዋሕዶም ምሳሌ ኾኖ ይጠቀሳል፡፡ “ዐቢይ ውእቱ ዝ ነገር አንሰ እብሎ ላዕለ ክርስቶስ ወላዕለ ቤተ ክርስቲያኑ፤ ይህም ምሥጢር ታላቅ ነው፤ እኔም ይህንኑ ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያኑ እናገረዋለሁ፤” እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ (ኤፌ. ፭፥፴፪)፡፡
የጋብቻ ክቡርነትና ምሥጢር ይህ ኾኖ ሳለ አንዳንዶቻችን ለጋብቻ የምንሰጠው ትርጕም ግን ዝቅ ያለ ይመስላል፡፡ በስውር ከጋብቻ ውጪ ፈቃዳቸዉን የሚፈጽሙ ምእመናን መኖራቸውም ከዚህ አመለካከት የመነጨ ነው፡፡ ከዚህ የተሳሳተ ግንዛቤ በመውጣትና ንጽሕናን በመጠበቅ አንድም ጋብቻ መመሥረት፤ ካለዚያም ራስን ጠብቆ በድንግልና ጸንቶ መኖር ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ ግዴታ ነው፡፡ ስለ ጋብቻ ሕይወት ሲነገር ከጋብቻ ዓላማዎች አንደኛው ከዝሙት ጠንቅ ለመሸሽ ነው፡፡ ይህም በሕጋዊ ሥርዓት ሩካቤ ሥጋን ለመፈጸም ያስችላል፡፡
ሩካቤ ሥጋ የተለየ ዓላማና ምሥጢር አለው፡፡ አፈጻጸሙም በሥርዓተ ተክሊል ወይም በሥርዓተ ቍርባን ይጸናል፡፡ በሕጋዊ ጋብቻ ተወስነን ካልኾነ በቀር ከጋብቻ በፊትም ኾነ በኋላ ካገኘነው ዂሉ ጋር ፆታዊ ግንኙነት መፈጸም ክቡራን ኾነን ተፈጥረን ሳለ በግብራችን ግን ከእንስሳት ጋር እንድንመሳሰል ያደርገናል፡፡ ቅዱስ ዳዊት “ሰብእሰ እንዘ ክቡር ውእቱ ኢያእመረ ወኮነ ከመ እንስሳ ዘአልቦ ልብ ወተመሰሎሙ፤ ሰውስ ክቡር ኾኖ ሳለ አላወቀም፤ ልብ እንደሌላቸው እንስሳትም መሰለ” በማለት እንደ ተናገረው (መዝ. ፵፰፥፲፪)፡፡
በዓለማችን ላይ እንደምንሰማውና እንደምናስተውለው የሰው ልጅ ራሱን ከሚጥልባቸው መንገዶች አንደኛው ዝሙት ነው፡፡ ለዚህም ነው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች አስጸያፊ ፆታዊ ድርጊቶች ማለትም ከአንድ በላይ የትዳር አጋር መያዝ፣ ሴት አዳሪነት ብሎም የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ምእመናንን ሳይቀር እየተፈታተነ የሚገኘው፡፡ ይህም በሰው ልጆች ዘንድ የመንፈስ ዝለትና የዝሙት ስሜትን የመቈጣጠር ስንፍናን አመላካች ነው፡፡ ከእንደዚህ ዓይነት አጸያፊ የዝሙት ሥራ ራሳችንን እንድንጠብቅ ለማስጠንቀቅ፣ ጋብቻችንንም በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ብቻ እንድንፈጽም ለመጠቆም እንደዚሁም ሩካቤ ሥጋ በሥርዓትና በሕግ እንደሚፈጸም ለማስገንዘብ ‹‹የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት›› በሚል ርእስ ይህን ትምህርት አዘጋጅተናል፡፡ በድጋሜ መልካም ንባብ!
፩. የጋብቻ ምንነትና አመሠራረት
ከቃሉ ትርጓሜ ስንጀምር ጋብቻ፡- መጣመር፣ መዋሐድ (አንድ መኾን)፣ በአንድ ጎጆ ውስጥ መኖር ማለት ነው፡፡ ቃሉ፣ የትዳር ሕይወትን ለመመሥረት የሚያስችል የሁለት ተቃራኒ ወይም ተፈላላጊ ፆታዎችን (ጥንዶችን) ዘላቂ ጥምረት (ግንኙነት) ያመለክታል፡፡ ‹ትዳር› የሚለው ቃልም ከጋብቻ ጋር በአቻነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ይኸውም ባልና ሚስት በአንድ ጎጆ ጥላ ሥር የሚያከናውኑት ቤተሰብኣዊ ኑሮ ነው “በአንድ ልብ በእግዚአብሔር ቤት ተራመድን” በማለት ቅዱስ ዳዊት እንደ ተናገረው (መዝ. ፶፬፥፲፬)፡፡ ትዳር፣ ሁለቱም (ብልና ሚስት) በመስማማትና በመተሳሰብ በአንድነት መኖራቸውን ያመለክታል፡፡ ስለዚህ ጋብቻ ወይም ትዳር ማለት በሁለት የማይተዋወቁና ባዕድ ተቃራኒ ጥንዶች (ፆታ) የሚመሠርቱት የአንድነት ሕይወት ነው፡፡
አመሠራረቱን ስንመለከት ጋብቻ የተመሠረተው በእግዚአብሔር ፈቃድ፣ በአዳምና ሔዋን አማካይነት ነው፡፡ ከአዳም በፊት የተፈጠሩ አራዊት፣ እንስሳትና አዕዋፍ በዝተው፣ ተባዝተው ይኖሩ ዘንድ የተፈጠሩት ጥንድ ጥንድ (ሴትና ወንድ) ኾነው ነበር፡፡ ለአዳም ግን ገና ሔዋን አልተሰጠችውም ነበር፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለአራዊት፣ ለእንስሳትና ለአዕዋፍ ስም ያወጣላቸው ዘንድ ወደ አዳም በላካቸው ጊዜ እንስሳቱ ተባዕትና አንስት ኾነው መፈጠራቸዉን አዳም ተመልክቶ “ከእኔ በቀር ብቻውን የተፈጠረ የለም” ብሎ ማዘኑን የቤተ ክርስቲያን መተርጕማን ይናገራሉ፡፡ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር አምላካችን፣ “ኢኮነ ሠናየ ለእጓለ እመሕያው ይንበር ባሕቲቶ፤ አላ ንግበር ሎቱ ቢጸ ዘትረድኦ፤ ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለም፤ የምትረዳውን ጓደኛ እንፍጠርለት እንጂ” አለ፡፡
ከዚህ በኋላ አዳም እንዲያንቀላፋ አደረገ፡፡ ከጎኑም አንድ አጥንት ነሥቶ (ወስዶ)፣ መልክ ከደም ግባት አስተባብራ የያዘችና ውብ አድርጎ፤ ዓይን፣ አፍንጫ፣ እጅ፣ እግር አውጥቶ፤ የሴት አካል ሰጥቶ ሔዋንን ፈጠረለት፡፡ ሔዋን ከአዳም ጎድን መፈጠሯም ባልና ሚስት ተከባብረው፣ ተቻችለውና ተመካክረው በእኩልነት እንዲኖሩ የሚያመለክት ምሥጢር አለው፡፡ ከዚህ ላይ የእግዚአብሔር ዓላማ ሴትንና ወንድን ማበላለጥ አለመኾኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ እንደዚያ ቢኾን ኖሮ ሔዋንን አንድም ዝቅ ብሎ ከአዳም እግር፤ አንድም ከፍ ብሎ ከራሱ ሊፈጥራት ይችል እንደ ነበር መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ሔዋን ከአዳም ጎን መፈጠሯ ባልና ሚስት እርስበርስ በመተጋገዝ፣ በመተሳሰብና በመደጋገፍ መኖር እንደሚገባቸው ያመላክታልና፡፡
አዳምም ከእንቅልፉ ሲነቃ ከጎኑ ሔዋንን በአገኘ ጊዜ “ይህቺ አጥንት የአጥንቴ ፍላጭ፣ ይህቺ ሥጋ የሥጋዬ ቁራጭ ናትና፤ ከኔ ከባሏ ተገኝታለችና ሚስት ትኹነኝ” በማለት ለሚስትነት እንደ ተሰጠችው አረጋግጦ ተናግሯል፡፡ ስለዚህም ወንድ አባትና እናቱን ትቶ ሚስቱን ተከትሎ ይሔዳል፡፡ ቈላ ብትወርድ፣ ደጋ ብትወጣ አብሯት ይወርዳል፤ ይወጣል፡፡ አንድ ክብር በመውረስና በመልበስ፤ እንደዚሁም በግብር (በሩካቤ ሥጋ) ሁለቱም አንድ አካል ይኾናሉ፡፡ ወንድ ቢወለድ ‹‹ያንተ ነው፤›› ሴት ብትወለድ ‹‹ያንቺ ናት›› አይባባሉምና፡፡ ዳግመኛም ሁለት ኾነው አንድ ልጅ ያስገኛሉና፤ እንደዚሁም ከእናት ደም፣ ከአባት ዘር ተከፍሎ አንድ ሰው እንዲወለድ ምክንያት ናቸውና እግዚአብሔር ‹‹አንድ አካል ይኾናሉ›› አለ (ዘፍ. ፩፥፳፰፤ ፪፥፳-፳፬)፡፡
ይቆየን