የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፫
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
ሚያዝያ ፲፫ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም
፩.፩ የጋብቻ ክቡርነት እና ምሥጢር
እግዚአብሔር አምላካችን በብሉይ ኪዳን የአዳምንና የሔዋንን፤ የሌሎችንም አባቶች እና እናቶች ጋብቻ ባርኳል፡፡ በሐዲስ ኪዳንም በዶኪማስ ቤት ተገኝቶ፣ ውኃውን ወደ ወይን ቀይሮ ቤቱን በበረከት ሞልቶለታል፡፡ ይህም ጋብቻ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደና የከበረ ምሥጢር መኾኑን አመላካች ነው፡፡ ምክንያቱም አምላካችን ያልፈቀደዉን ሕይወት ባርኮ አይሰጥምና ነው፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ባልና ሚስት አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፡፡ እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው” በማለት ማስተማሩም ጋብቻ የአንድነት ውጤትና ታላቅ ሥርዓት መኾኑን ያስረዳል (ማቴ. ፲፱፥፮፤ ዮሐ. ፪፥፩-፲፩)፡፡
በዚህም ሥርዓት በብሉይ ኪዳን፡- አዳምና ሔዋን፣ አብርሃምና ሣራ፣ ይስሐቅና ርብቃ፣ ያዕቆብና ራሔልን የመሰሉ፤ በሐዲስ ኪዳን፡- ኢያቄምና ሐና (የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ወላጆች)፣ ጸጋ ዘአብና እግዚእ ኀረያ (የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ወላ ጆች)፣ ኖኅና ታቦትን (የቅዱስ መርቆሬዎስ ወላጆች) የመሰሉ ደጋግ አባቶች ልጆችን አፍርተውበታል፤ ተጠቅመውበታልም፡፡ ለዚህም ነው “ጋብቻ በዂሉ ዘንድ ክቡር ነው፤ ለመኝታቸውም ርኵሰት የለበትም” ተብሎ የተነገረው (ዕብ. ፲፫፥፬)፡፡ በሥርዓት ከኖሩበት የሚያስከብር ሕይወት ነውና፡፡
ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ “… ማርያም ድንግል ከብካብ ንጹሕ ወመርዓ ቅዱስ፤ ድንግል ማርያም ሙሽራዋ ንጹሕ የኾነ የሰርግ ቤት ናት፤” በማለት እመቤታችንን አመስግኗታል፡፡ ሊቁ እመቤታችንን በሰርግ ቤት መመሰሉ ጋብቻ ንጹሕ ሥርዓት መኾኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ይህም ምሥጢራዊ ትርጕም አለው፤ በሰርግ ቤት ደስታ፣ ጨዋታ፣ መብልና መጠጥ፣ የሙሽራውና የሙሽሪት አንድነት ይከናወንበታል፤ የሙሽራውና የሙሽሪት ዘመዶች አንድ ይኾኑበታል፡፡ መብልና መጠጡ የትምህርተ ወንጌል (የሥጋ ወደሙ)፤ ደስታና ጨዋታው የተአምራት፤ የሙሽራውና የሙሽሪት ተዋሕዶ የትስብእትና የመለኮት አንድነት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በሰርግ የሙሽራውና የሙሽሪት ዘመዶች አንድ እንደሚኾኑባት ዂሉ፣ በድንግል ማርያምም ሰውና መላእክት፣ ሰውና እግዚአብሔር፣ ነፍስና ሥጋ፣ ሕዝብና አሕዛብ አንድ ኾነውባታል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችንን ‹‹ሙሽራዋ ንጹሕ የሚኾን የሰርግ ቤት›› ይላታል (የረቡዕ ውዳሴ ማርያም፣ አንድምታ ትርጓሜ)፡፡
ቅዱስ ኤፍሬም ዳግመኛም “ከመ ከብካብ ዘአልቦ ጥልቀት መንፈስ ቅዱስ ኀደረ ላዕሌኪ፤ እንደ ሰርግ ቤት አደፍ፣ ጉድፍ የሌለብሽ ኾነሽ ቢያገኝሽ መንፈስ ቅዱስ አድሮብሻል” በማለት እመቤታችንን ጋብቻ በሚፈጸምበት ንጹሕ የሰርግ ቤት መስሎ አመስግኗታል፡፡ ይህም በተመሳሳይ መልኩ የጋብቻን ክቡርነት የሚያመለክት ነው (ውዳሴ ዘቀዳሚት)፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ “ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፤ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ” በማለት ጋብቻ የክርስቶስና የቤተ ክርስቲያን ተዋሕዶ ምሳሌ መኾኑን ያመሠጠረልን (ኤፌ. ፭፥፴፪)፡፡ በአጠቃላይ ጋብቻ፣ ይከብርበትና በጋራ ይኖርበት ዘንድ እንደዚሁም ራሱን ከኃጢአት ይጠብቅበት ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ ለሰው ልጅ ያዘጋጀው መንፈሳዊ ሥርዓት ነው፡፡
፩.፪ የጋብቻ አስፈላጊነትና ዓላማዎቹ
ሰው ኾነን የመፈጠራችን ዓላማው የእግዚአብሔርን ስም ለመቀደስ (ለማመስገን)፣ ክብሩን (መንግሥቱን) ለመውረስ እንደ ኾነው ዂሉ ጋብቻንም አምላካችን በዓላማ አዘጋጅቶልናል፡፡ የጋብቻ አስፈላጊነቱ ወይም ዓላማው እጅግ የጎላ ነው፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያን እንደ ተገለጸው ጋብቻን የሚያሹ (የሚያስፈልጉ) ፈቃዳት ሦስት ናቸው፤ እሊህም ጠቢብ፣ ልዑል ከኾነው ከእግዚአብሔር የተሰጡ፤ እንደዚሁም ከአብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ የተወረሱ ግብራት ናቸው፡፡ ከሦስቱ ዓላማዎች የተለየ የጋብቻ ጥቅም (አስፈላጊነት) አይኖርም፡፡ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን “ከነቢያት ከሐዋርያት አንዱ ስንኳ ‹ጋብቻ ለዝሙት ትኹን› ብሎ ያስተማረ የለም፡፡ ልጅ ለመውለድ ብቻ ነው እንጂ” በማለት የጋብቻን ዓላማዎች ያስረዳሉ (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፳፬፣ ቍ. ፷)፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት በማድረግ ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው ጋብቻ የሚከተሉት ሦስት መሠረታውያን ዓላማዎች አሉት፤
ሀ. መረዳዳት
ከጋብቻ ዓላማዎች አንደኛው እርስበርስ መረዳዳት ነው፡፡ መረዳዳት ማለት መተጋገዝ፣ መተሳሰብ፣ መደጋገፍ፣ መጠያየቅ፣ ለራሳችን ሊደረግልን የምንፈልገውን መልካም ነገር ዂሉ ለሌሎችም ማድረግ ማለት ነው፡፡ ጋብቻ ሁለት ጥንዶች በአንድነት የሚኖሩበትና እርስበርስ የሚረዳዱበት ሕይወት ነው፡፡ በጋብቻ ውስጥ የሚደረግ መረዳዳት በማኅ በራዊ፣ በሥነ ልቡና፣ በምጣኔ ሀብትና በቤተሰብ አስተዳደር መተጋገዝን፣ መተሳሰብን፣ በአንተ ይብስ፤ በአንቺ ይብስ መባባልን እንደዚሁም በስሜት መተዋወቅን ያጠቃልላል፡፡
በጋብቻ ሊኖር ስለሚገባው የመረዳዳት ዓላማ መነሻው “ሰው ብቻውን ይኾን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት” የሚለው አምላካዊ ቃል ነው (ዘፍ. ፪፥፲፰)፡፡ ስለዚህም በተቻላቸው አቅም ዂሉ ባል ለሚስቱ የሚገባትን፣ ሚስትም ለባሏ የሚገባውን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ጋብቻ የአንድነት ሕይወት በመኾኑ ሚስት በራሷ፣ ባልም በራሱ ሥልጣን እንደሌላቸው ቅዱስ ጳውሎስ ይናገራል፡፡ አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ማዘዝ እንደሚችሉም ያስረዳል፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም አንድ አካል ናቸውና (፩ኛ ቆሮ. ፯፥፴፬)፡፡ በመኾኑም ባልና ሚስት እንደ ዓይን ብሌን ሊጠባበቁ፣ ሊከባበሩና አንዳቸው ለአንዳቸው ሊታዘዙ ይገባቸዋል፡፡ መረዳዳት ማለት አንዱ የሌላውን ስሜት መጠበቅ ነውና፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስም በጋብቻ ሕይወት ውስጥ መኖር ስለሚገባው የመደጋገፍና የመረዳዳት ዓላማ ሲያስረዳ “እናንተ ባሎች ሆይ፥ ደካማ ፍጥረት ስለ ኾኑ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤ ጸሎታችሁ እንዳይከለከል አብረው ደግሞ የሕይወትን ጸጋ እንደሚወርሱ አድርጋችሁ አክብሩአቸው፡፡ በመጨረሻው ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ፤ የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ፤ እንደ ወንድሞች ተዋደዱ፤ ርኅሩኆችና ትሑታን ኹኑ፡፡ ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ፤ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፡፡ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታች ኋልና” ሲል በአጽንዖት አስተምሯል (፩ኛ ጴጥ. ፫፥፩-፱)፡፡
በዚህ ኃይለ ቃል ውስጥ ‹‹ደካማ ፍጥረት ስለ ኾኑ›› የሚለው ሐረግ ሴቶች በዕውቀት ወይም በዓቅም ዝቅተኛ ናቸው ለማለት አይደለም፡፡ በትዳር አጋሮቻቸው በሚደርስባቸው ጫና፣ ከውጪ በሚገጥማቸው ልዩ ልዩ ፈተና በቀላሉ የሚሰናከሉ መኾናቸዉን የመሚጠቁም ነው እንጂ፡፡ ለዚህም ማስረጃ የሚኾነን የሔዋን ጠባይዕ ነው፡፡ አዳምና ሔዋን በገነት በነበሩበት ወቅት የሰይጣን የማሰሳሳት ጥረት የተሳካው በሔዋን የመታለል ጠባይዕ ነበር፡፡ የሔዋን ውዳሴ ከንቱ (የማይጠቅም ምስጋና) የመውደድና በቀላሉ የመሸነፍ ስሜት አሁንም ድረስ በሴቶች ላይ ይስተዋላል፡፡ ሐዋርያው ድክመት ያለውም ይህንን ዓይነት የሴቶችን ጠባይዕ ነው እንጂ በተፈጥሮማ ሴቶችም በሥላሴ አርአያና አምሳል ነው የተፈጠሩት፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ በባልና በሚስት መካከል ሊኖር ስለሚገባው መልካም ግንኙነትና መተሳሰብ ሲያስረዳ ሣራ፣ አብርሃምን ትታዘዘው፤ ‹‹ጌታዬ›› ትለው እንደ ነበረው፤ በበጐ ሥራ ፍጹማን የኾኑ ልጆችን ይወልዱ ዘንድ ወንዶች ሚስቶቻቸውን እንዲያከብሩ ይመክራል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም በዲድስቅልያ “አእምራ አንስት ከመ ብእሲት እንተ ታፈቅር ምታ ትረክብ ክብረ በኀበ እግዚአብሔር፤ ሴቶች ሆይ፥ ባሏን የምትወድ ሚስት በእግዚአብሔር ዘንድ ክብርን እንደምታገኝ ዕወቁ” በማለት በባልና በሚስት መካከል ሊኖር ስለሚገባው መከባበርና መተጋገዝ፤ እንደዚሁም መከባበር ስለሚያስገኘው ጸጋ አስተምረዋል (ዲድስቅልያ፣ አን. ፫፣ ቍ. ፳፭)፡፡ በተአምረ ማርያምም “ከእናንተ ወገን ሚስት ያለችው ሰው ቢኖር እንደ ዓይን ብሌን ይጠብቃት፤ እግዚአብሔር ያስጠበቀው አደራ ናትና” ተብሎ ተጽፏል (፲፩ኛ ተአምር፣ ቍ. ፳፮)፡፡
በጋብቻ ሕይወት ውስጥ ሊኖር ስለሚገባው መረዳዳት ቅዱሳት መጻሕፍት የሚናገሩትን ኃይለ ቃል ጠቅለል ስናደርገው ባልና ሚስት በመካከላቸው የራስ ወዳድነትና የትዕቢት መንፈስን በማስወገድ እንደ ዓይን ብሌን ሊጠባበቁ፣ ሊከባበሩና እርስበርስ ሊከባበሩ እንደሚገባቸው እንገነዘባለን፡፡ በየትኛውም ዓይነት ሕይወት ውስጥ መረዳዳት መኖሩ ተገቢ ነው፡፡ በጋብቻ ሕይወት ግን መረዳዳት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ጋብቻ ሁለት ሰዎች በአንድ ጣሪያ ሥር በአንድነት የሚኖሩበት ሕይወት ከመኾኑም ባሻገር ኑሮንም ስሜትንም በጋራ የሚመሩበት የአንድነት ተቋም ነውና፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የጋብቻን ሕይወት፣ ‹‹በቤት ውስጥ ያለች ትንሿ ቤተ ክርስቲያን›› በማለት የሚገልጸው፡፡
ይቆየን