የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፩

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሚያዝያ ፲፩ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

መግቢያ

በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ከዕለተ ትንሣኤ እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ ድረስ ያለው ጊዜ ‹በዓለ ኀምሳ› ይባላል፡፡ ይኸውም ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ ተቀብሎ አዳምንና ልጆቹን ከሲኦል ነጻ ማውጣቱ፤ በሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱ፤ ከትንሣኤው በኋላ በልዩ ልዩ መንገድ ለደቀ መዛሙርቱ መገለጡ፤ መጽሐፈ ኪዳንን ለሐዋርያት እያስተማረ፣ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እያደረገ ዐርባ ቀን በምድር ቆይቶ ወደ ሰማይ ማረጉ፤ ባረገ በዐሥረኛው ቀን መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት መላኩ፤ እንደዚሁም ዳግም ለፍርድ በግርማ የሚመጣ መኾኑ በስፋት የሚነገርበት ወቅት ነው፡፡ እኛ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን፣ እግዚአብሔር ያደረገልንን ውለታ በማሰብ ይህን ሰሙን በመንፈሳዊ ደስታ ልናከብረው እንደሚገባ የቤተ ክርስቲያን መምህራን ሥርዓት ሠርተውልናል፡፡

ከዚህ ላይ መደሰት ማለት ሥርዓት በሌለው መልኩ ከመጠን በላይ መብላት መጠጣት ማለት አለመኾኑን ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ቸርነት እያሰቡ በመጠን እየተመገቡ፣ ነዳያንንም እያሰቡ፣ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን እየተቀበሉ መደሰት የክርስትና መገለጫ ነው፡፡ በዚህ ወቅት እያንዳንዱ ምእመን ሊጠብቀው የሚገባም ይህንኑ ሥርዓት ነው፡፡ ወቅቱ የደስታና የነጻነት ማለትም በክርስቶስ ቤዛነት የሰው ልጆች (ምእመናን) ከሰይጣን ባርነት ነጻ መውጣታችንን የምናስብበት ወቅት ነውና በዘመነ መርዓዊ እንደሚደረገው ዂሉ በዚህ ሰሙን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ጋብቻ የሚፈጽሙ ምእመናን በርካቶች ናቸው፡፡ ዕቅዱ ላላቸውና ለተፈቀደላቸው ሰዎች ጋብቻ ከብቸኝነት ኑሮ ነጻ የሚወጡበት፣ የዝሙት ፆርን የሚከላከሉበት ሕይወት በመኾኑ በዚህ በነጻነት ወቅት (በበዓለ ኀምሳ) ይፈጸማል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ የጋብቻን ታላቅነትና ልዩ ምሥጢር ባስተማረበት መልእክቱ “ይህም ምሥጢር ታላቅ ነው፤ እኔም ይህንኑ ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያኑ እናገረዋለሁ፤” በማለት የባልና የሚስት ጥምረት ወይም አንድነት የክርስቶስና የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ መኾኑን ይናገራል (ኤፌ. ፭፥፴፪)፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ጋብቻ የመለኮት እና የትስብእት (የሰውነት) ምሳሌ መኾኑን መምህራነ ቤተ ክርስቲያን ያስተምራሉ፡፡ በዓለ ኀምሳ፣ ቤተ ክርስቲያንን በደሙ የመሠረታት የመድኀኒታችን ክርስቶስ ትንሣኤ የሚታሰብበት፣ ምሥጢረ ሥጋዌና ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን በስፋት የሚሰበክበት ወቅት ከመኾኑ አኳያ በእርግጥም በዚህ የደስታ ሰሙን የተዋሕዶ ምሳሌ የኾነውን ጋብቻን በቤተ ክርስቲያን መፈጸም ለምሥጢር የተመቸ መልእክት አለው፡፡

የዛሬዉን ትምህርታዊ ጽሑፍ በጋብቻ ዙርያ ያደረግነው ወቅቱን ለመዋጀት በማሰብ ነው፡፡ በእርግጥ ስለ ጋብቻ በልዩ ልዩ መንገድ ብዙ ጊዜ ተምረናል፡፡ ኾኖም ጉዳዩ የሕይወት ጉዳይ ነውና ደጋግመን መማማሩ ይጠቅመናል፡፡ አንዳዶቹ በማወቅም፣ ባለማወቅም ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጪ ጋብቻቸውን ሲፈጽሙ ይስተዋላል፡፡ ስለ ጋብቻ በተደጋጋሚ መማማራችንም በማወቅ ወይም በግድየለሽነት ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጪ ትዳር የሚመሠርቱ ምእመናንን ለመመለስና ሌሎችም እንዳይስቱ ለመጠቆም ይረዳናል፡፡ ስለዚህም በዚህ ዝግጅት ስለ ጋብቻ አመሠራረት፣ ክቡርነት፣ ምሥጢር እና ዓላማ የሚያትት ተከታታይ ትምህርት ይዘን ቀርበናል፡፡ ትምህርቱን ትከታተሉ ዘንድ መንፈሳዊ ግብዣችንን እናስቀድማለን፡፡

መቅድም

የሰው ልጅ ወደዚህ ዓለም ከመጣ በኋላ ራሱን እስከሚችል ድረስ ሕይወቱ በእናት በአባቱ እጅ የተወሰነ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የወደፊት የኑሮ ዕጣውም በወላጆቹ አኗኗር ላይ የተመሠረተ ሊኾን ይችላል፡፡ በየትኛውም ዓይነት የአስተዳደግ ሥርዓት ብናልፍም ግን ዕድሜያችን እየገፋ ሲሔድ ራሳችንን መፈለግ እንጀምራለን፡፡ አንዳዶቻችን ጳጳስ፣ ቄስ፣ ዲያቆን፣ ሰባኪ፣ ዘማሪ፣ ወዘተ፤ ሌሎቻችን የአገር መሪ፣ አውሮላን አብራሪ፣ ተመራማሪ፣ ደራሲ፣ አርሶ አደር ወይም የተለየ ሰው የመሆን ርዕይ ሊኖረን ይችላል፡፡ ምንም ዓይነት ርዕይ የሌለን ሰዎችም ልንኖር እንችላለን፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ልንሸከመውና ልንወጣው በምንችልበት የኑሮ መስክ ያሰማራናል፡፡

በርዕይ ወይም ያለ ርዕይ ከአገኘነው ሥራ ወይም መዓርግ ባለፈ ሁለት ፈቃዳት ያስፈልጉናል፡፡ አንድም በድንግልና መኖር፤ አንድም በትዳር መወሰን፡፡ ሦስተኛው ግብር ግን ሰይጣናዊ ሲኾን፣ ይኸውም ዘማዊነት ነው፡፡ “ኦ ዘትቤ ንግበር ሎቱ፡፡ ለዕጓለ እመሕያው ቢጸ ከመ ኢይንበር ባሕቲቱ፡፡ እግዚአብሔር መጋቢ ወሠራዔ ዓለም በበሥርዓቱ፡፡ ሥርዐኒ ኀበ ፈቃድከ እምፆታ ፈቃዳት ክልኤቱ፡፡ ሣልሳዊሰ ግብር እምሰይጣን ውእቱ፤ ‹የሰው ልጅ (አዳም) ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለም› በማለት የተናገርህ፤ ዓለምን በየሥርዓቱ ፈጥረህ የምትመግበው (የምታኖረው) እግዚአብሔር ሆይ፣ ከሁለቱ ፈቃዶች ውስጥ አንተ ወደ ወደድኸው ፈቃድ ምራኝ፡፡ ሦስተኛው ግብር (ሥራ) ግን ከሰይጣን የመጣ ነው፤” እንዳለ ደራሲ (ጠቢበ ጠቢባን)፡፡

ከሦስተኛው ፈቃድ ነጻ በመውጣት በምንኵስና ወይም በጋብቻ ለመኖርም ዋነኛውና መሠረታዊው ጉዳይ የእግዚአብሔር ፈቃድ ቢኾንም ከእርሱ ቀጥሎ የእያንዳንዳችን ፈቃድም ወሳኝነት አለው፡፡ ለመመንኰስም ትዳር ለመመሥረትም የሰውነታችንን ፈቃድ በትክክል መረዳት ይኖርብናልና፡፡ እንኳን ከገቡ ለማይወጡበት ለምንኵስና ሕይወት በልዩ ልዩ ምክንያት ሊቋረጥ ለሚችለው ለጋብቻ እንኳን ፈቃደኝነት ያስፈልጋል፡፡ የሁለቱ ጥንዶች የጋራ ስምምነት ደግሞ ሌላው ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ሁለቱ ተጋቢዎች ሳይስማሙ ማጋባት ተገቢ አይደለም፡፡

ምክንያቱም ሳይዋደዱ ከተጋቡ ኑሯቸው ጭቅጭቅና ጥርጣሬ የተሞላበት ሊኾን ይችላልና ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ጋብቻ ሕይወት ከመግባታችን በፊት ከአጋራችን ጋር በሙሉ ልብ መተማመንና መስማማት ይገባል፡፡ “ወኢይኩን ተዋስቦ ዘእንበለ በሥምረተ ክልኤሆሙ እለ ይትዋሰቡ ወበሥምረተ እሉ እሙንቱ ታሕተ ምግብናሆሙ ወዝንቱኒ ይከልእ እምአውስቦ …፤ በባልና ሚስት ፈቃድ ነው እንጂ ያለ ሁለቱ ፈቃድ ጋብቻ አይጸናም፤ አይፈጸምም፡፡ ወላጅ፣ ወይም አሳዳጊ ሳይፈቅድ ማጋባት አይገባም፤” እንዲል ፍትሐ ነገሥት (አን. ፳፬፣ ክፍል ፲፭)፡፡

በጋብቻ የመወሰን ፈቃድ እንደ ተሰጠን ዂሉ ፈቃደ ሥጋችንን ማሸነፍ እንደምንችል እርግጠኞች ከኾንን አለማግባትም ማለትም በድንግልና (በምንኵስና) መኖር እንችላለን፡፡ ለዚህም እግዚአብሔር አምላክ የዝሙትን ፆር አርቆላቸው ከሴት ርቀው፣ ንጽሕ ጠብቀው በድንግልና (በምንኵስና) የሚኖሩ አባቶች እና እናቶች አብነቶቻችን ናቸው፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባልና ሚስት ያለ ምክንያት መፋታት አመንዝራነት እንደ ኾነ ሲያስተምር ቅዱሳን ሐዋርያት “የባልና የሚስት ሥርዓት እንዲህ ከኾነስ ማግባት መልካም አይደለም” አሉ። ጌታችንም “ይህ ነገር ለተሰጣቸው ነው እንጂ ለዂሉ የሚቻል አይደለም፡፡ ከእናታቸው ማኅፀን እንዲሁ የተወለዱ፤ ሰዎች የሰለቧቸው፤ ስለ መንግሥተ ሰማያትም ራሳቸውን የሰለቡ ዣንደረቦች አሉ፡፡ መታገሥ የሚችልስ ይታገሥ” በማለት ስለ ጋብቻ እና ድንግልና ሕይወት አስረድቷቸዋል (ማቴ. ፲፱፥፲፩)፡፡ ይህ ኃይለ ቃል፣ ጋብቻም ኾነ ድንግልና በእግዚአብሔር ፈቃድ የሚመሠረት ሕይወት መኾኑን ያመላክታል፡፡

ይቆየን