የጅማ ማእከል የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር አካሄደ
ግንቦት 25 ቀን 2007 ዓ.ም.
ጅማ ማእከል
በማኅበረ ቅዱሳን የጅማ ማእከል ያዘጋጀው ሁለተኛው የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ግንቦት 22 ቀን 2007 ዓ.ም. በኮሳ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተካሄደ፡፡
የጉዞውን መነሻ በጅማ ሀገረ ስብከት ሁለገብ( አቡነ እስጢፋኖስ) ሕንፃ በማድረግ ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ ከ800 በላይ ምእመናንን በማሳተፍ በሊሙ ኮሳ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥር ወደምትገኘው ኮሳ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አድርጓል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ ከ2000 በላይ የሚሆኑ የአጥቢያው ምእመናን፣የሀገረ ስብከቱ ስራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ስለሺ አስፋው፣የወረዳው ቤተ ክህነት ሊቀ ካህን ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ መሰረት፣ ሌሎች የሀገረ ስብከቱ የሥራ ሓላፊዎች፣ በጅማ ከተማ የሚገኙ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ፣ የአጎራባች ወረዳ ማእከላትና የግንኙነት ጣቢያ አባላት፣ የጅማ ማእከል አባላት፣ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ መንፈሳዊ ማኅበራት እና በጎ አድራጊ ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ክፍል አንድ ትምህርት ወንጌል በመጋቤ ሐዲስ ቀሲስ መንግስቱ አማረ፤ የጥንታዊቷና ታሪካዊቷ ቤተክርስቲያን የ200 መቶ ዓመት ታሪክ በሰበካ ጉባኤ ተወካይ ፡ እንዲሁም የማኀበረ ቅዱሳን የአገልግሎት እንቅስቃሴና መልእክት በአቶ ቡሩክ ወልደ ሚካኤል ቀርበዋል፡፡
ከምእመናን ለቀረቡ ጥያቄዎች ምክረ አበው መርሐ ግብር በሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መልአክ እና በመጋቤ ሐዲስ ቀሲስ መንግስቱ አማረ ማብራርያ ተሰጥቷል፡፡በመቀጠል ክፍል ሁለት የወንጌል ትምህርት በሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መልአክ ተሰጥቷል፡፡
የትምህርት መርሐ ግብሩ እንደተጠናቀቀ ቤተክርስቲያኗን በአዲስ መልክ ለመሥራት የተጀመረውን ጥረት የሚያግዝ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር የተካሄደ ሲሆን ከ130,000(አንድ መቶ ሰላሳ ሺህ )በላይ በጥሬ እና በቁሳቁስ ለማሰባሰብ ተችሏል፡፡
በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ ስራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ስለሺ ስለነበረው መርሐ ግብር እና አስፈላጊነት ሰፊ ማብራርያና ግንዛቤ ለምዕመናን የሰጡ ሲሆን ይህንን የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ያዘጋጀውን የጅማ ማዕከልን አመስግነዋል፡፡በማስከተልም ማኀበረ ቅዱሳን የቤተክርስቲያንን አገልግሎት ለማገዝ እየፈጸመ ያለውን አገልግሎት አድንቀው ምእመናንም ይህንን የማኀበሩን አገልግሎት ከጎን በመሆን ማገዝና መረዳት እንደሚገባ በማስገንዘብ መርሐግብሩ በጸሎት ተዘግቷል፡፡
ከመርሐግብሩ መጠናቀቅ በኃላ የምእመናንን አስተያየት የተሰበሰበ ሲሆን በመርሐግብሩ መደሰታቸውንና ለወደፊቱም እንደዚህ አይነት መርሐግብር በአመት ሁለት እና ሦስት ጊዜ መዘጋጀት እንዳለበት ገልጸው፤ ስለቤተክርስቲያን ወቅታዊ ሁኔታና የማኀበሩን አገልግሎት ለማወቅ እንደረዳቸው ገልጸዋል ፡፡