የዶዶላ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን አሁንም የጸጥታ ሥጋት እንዳለባቸው ተናገሩ
በካሣሁን ለምለሙ
በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን ዶዶላ ከተማ የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን የፀጥታ ሥጋት እንዳለባቸው ለዝግጅት ክፍላችን ተናገሩ፡፡
ከዚህ ቀደም አቶ ጀዋር መሐመድ በተባለው ግለሰብ በተጠራው የተከብቤአለሁ ጥሪና የአርቲስት አጫሉ ሁንዴሳን ድንገተኛ ሞት ሽፋን በማድረግ አክሪራ እስላሞች በዶዶላ ሕዝበ ክርስቲያን ላይ ከፍተኛ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ምእመናኑ አሁንም ድረስ ለከፍተኛ የፀጥታ ሥጋት እንደተዳረጉ አስታውቀዋል፡፡
በያዘነው ሳምንት አክራሪ እስላሞች በተደጋጋሚ በእያንዳንዱ ኦርቶዶክሳዊ ቤት በተለይም የሸዋ ኦሮሞ ኦርቶዶክሳውያን ቤት ደረስ በመሄድ ‹‹ሀገራችንን ለቃችሁ ውጡ›› የሚል መልእክት የያዘ ወረቀት እየበተኑ እንደሆነ የተናገሩት የአካባቢው ምእመናን ከዚህ ቀደም ምእመናንን በተናጠል ለማጥቃት እንዲያመቻቸው በብሔር የመከፋፈል ሥራ ሲሠሩ እንደቆዩም ገልጸዋል፡፡
የአካባቢው ፀጥታ ኃይሎችም ሆኑ ሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት ከላይ እስከታች ድረስ የአንድ ሃይማኖትና ጎሳ ሥሪት በመሆናቸው አክራሪ እስላሞች ጥቃት ሲፈጽሙ ከለላ ከመስጠት ባሻገር የስንቅና ትጥቅ አቅርቦት እንደሚያደርጉላቸውም ምእመናኑ ተናግረዋል፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ አሁን ባለው የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት መዋቅር እንደማይተማመኑ ገልጠው አደረጃጀቱ ተከታትሎ ፍትሐዊና አሳታፊ ሆኖ እንደ አዲስ እንዲዋቀር ጠይቀዋል፡፡
በዶዶላ ከተማ ጥቅምት ወር !)፲፪ ዓ.ም በአክራሪ እስላሞች ከተፈጸመው ኦርቶዶክሳዊ ጭፍጨፋ በኋላ በድጋሚ በንብረትና በሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰ የሚታወቅ ቢሆንም ችግሩ ይፋ እንዳይሆንና የሚዲያ ሸፋን እንዳያገኝ የአካባቢው የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው ምንም ችግር እንዳልተፈጠረ በማስመሰል ሆን ብሎ በተደጋጋሚ መግለጫዎችን እያወጣ ሕዝብ ሲያደናግር እንደቆየ ምእመናኑ አስረድተዋል፡፡
ሀገሪቱን የሚመራው መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅና ወጥቶ የመግባት ዋስትናን ሊያረጋግጥ እንደሚገባ ያነሱት ምእመናኑ በአክራሪ እስላሞች የተፈጸመውን የኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያኖች ጭፍጨፋ ተከትሎ መንግሥት በአጥፊዎች ላይ ርምጃ እየወሰድኩ ነው ቢልም በዶዶለ ከተማ ኦርቶዶክሳውያንን ያረዱና ንብረት ያወደሙ ግለሰቦች እስካሁን ድረስ በነፃነት በከተማዋ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ምእመናኑ ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡
ሕዝበ ክርስቲያኑ ከምንጊዜውም በተሻለ አንድነቱን አጠናክሮ እንዲሁም ወጣቱ ኃይል ተደራጅቶ ዘላቂ ሰላምን ማምጣት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ምእመናኑ አባቶችም ቀን ሲያልፍ እንዳያፍሩበት ዝምታቸውን ሰብረው ምእመናንና ቤተ ክርስቲያንን ከአክራሪ እስላሞች ጥቃት ሊታደጉ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ምእመናኑ አያይዘውም በዚህ ሰዓት ወጣቱ ለቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ በመሆኑ ከወጣቱ ጎን በመቆም ጠንካራ አደረጃጀት ፈጥሮ በቅዱሳን አባቶቻችን ደም የቆመችውን ቤተ ክርስቲያን ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ሰላምን ከመንግሥት ብቻ ከመጠበቅ ቤተ ክርስቲያን መዋቅሯን ተጠቅማ ደኅንነቷን ልታረጋግጥ እንደሚገባ የገለጡት ምእመናኑ ቤተ ክርስቲያን ካላት ተከታይ ብዛትና ተደማጭነት አንጻር የተሻለ የደኅንነት ሥራ ካልሠራች በአክራሪ እስላሞች የሽብር ጥቃት ለወደፊትም እንደምትፈተን ስጋታቸውን ገልጠዋል፡፡
የዶዶላ ከተማ ፖሊስ አባል ሳጅን ገመቹ በበኩላቸው በዶዶላና አካባቢው ምንም ዓይነት የፀጥታ ሥጋት ባለመኖሩ ምእመናኑ በሰላም ወጥተው በሰላም እየገቡ እንደሆነ ገልጠው ለወደፊትም የፀጥታ ሥጋት እንዳይኖር ከማኅበረሰቡ ጋር እየሠሩ እንደሆነ ለዝግጅት ክፍላችን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ሀገራችንን ለቃችሁ ውጡ›› የሚል መልእክት ያለው ወረቀት ዶዶላ ከተማ ላይ እንዳልተበተነ የገለጡት ሳጅን ገመቹ “ወረቀት እንደተበተነ አስመስለው የሚያወሩ አካላት የሀገርን ሰላምና መረጋጋት የማይፈልጉ ናቸው” ብለዋል፡፡ በከተማው ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች በመኖራቸው ለወደፊቱ ምንም ዓይነት የፀጥታ ሥጋት እንደማይኖር ሳጅን ገመቹ አክለው ገልጸዋል፡፡
ከኅብረተሰቡ ጎን ሆነው በአጥፊዎች ላይ ርምጃ እየወሰዱ እንደሆነ የገለጡት ሳጅን ገመቹ “ወንጀል ፈጽመዋል ብለን በጥርጣሬ የያዝናቸውን ተጠርጣሪዎች በሕግ ጥላ ሥር አውለን ጉዳያቸው በሕግ አግባብ እየታየ ነው” ብለዋል፡፡
ሳጅን ገመቹ ይህንን ይበሉ እንጂ በዶዶላ በሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ላይ አክራሪ እስላሞች አሁንም ከፍተኛ የፀጥታ ሥጋት እየፈጠሩባቸው እንደሆነ ከምእመናን ባገኘነው ተጨባጭ መረጃ ዝግጅት ክፍላችን ማረጋገጥ ችሏል፡፡