ከመንግስተአብ
ስም ለፈጣሪም ሆነ ለፍጡራን ለመጠሪያነት ያገለግላል፡፡ ይህም ስም አንዱን ከሌላው ለይቶ የሚያሳውቅ የፍቅር መግለጫ ነው፡፡ በጽሑፍም ሆነ በቃል ማስተላለፍ የሚቻለው በስም አማካኝነት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ለሚወዳቸውና ለመረጣቸው ሰዎች ስም ያወጣ እንደ ነበር ሁሉ፤ ሰዎችም ያወጡ መጠሪያ ይሰጡ ነበር፡፡ ይህም ስም የሚሰየመው ወይም መጠሪያ ሆኖ የሚሰጠው እንዲሁ በዘፈቀደ ሳይሆን መሠረታዊ ምሥጢርና ትርጉም አለው፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን «እስመ ስሙ ይመርህ ኀበ ግብሩ» በማለት ስም ግብርን ሁኔታን እንደሚገልጽ መሥክረዋል፡፡
የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች ምስክርነት ከስም አጠራሯ በመጀመር ለስመ ድንግል ማርያም ዘርፍ /ቅጽል/ አልያም ምትክ አድርገን የምንጠቀምባቸው ምሥጢራዊና ትርጉም ያላቸው ንጽሕናዋን፣ ቅድስናዋን፣ ድንግልናዋን፣ ወዘተ የሚመሰክሩ በርካታ ስሞች አሏት፡፡ ስለ እመቤታችን ስሞች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ካላቸው ፍቅር የተነሣ አብዝተው፣ አምልተው፣ አስፍተው፣ አመስጥረው ከተረጐሙት ጥቂቱን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
ምልዕተ ጸጋ፡- መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ይህን ቃል ከእመቤታችን በቀር ለማንም እንዳልተነገረ እንረዳለን፡፡ አዳም ከፍጥረት ሁሉ አልቆ አግንኖ በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረው ፍጥረት ነበር፡፡ ነገር ግን በኃጢአት ምክንያት የተሰጠው ጸጋ ተገፈፈ፡፡ አብርሃም ወዳጁ ነበር፡፡ ዳዊትም እንደልቤ ያለው ነው ሙሴንም ከ570 ጊዜ በላይ ቃል በቃል አነጋግሮታል፡፡ በዘመነ ሐዲስም ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስን «አንተ ብፁዕ ነህ» ብሎ መስክሮለታል ይሁን እንጂ እንዲህ ባለው ቃል እንደ እመቤታችን «ጸጋ የሞላብህ» «ጸጋ የሞላብሽ» የተባሉ ሌሎች አልተገኙም፡፡ እመቤታችን ከፍጥረት ሁሉ ተመርጣ ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ እግዚአብሔር የጠበቃት፣ ያደረባት «የከተመባት ረቂቅ ከተማ» መሆኗን መልአኩ በመሰከረበት ቃል «ምልዕተ ጸጋ» እያልን እንጠራታለን፡፡ ሉቃ.1-26፡፡ እመቤታችን የተለየች ናትና «ጸጋ የሞላብሽ» /የጸጋ ግምጃ ቤት/ ተብላለች፡፡
እምነ /«ም» ጠብቆ ይነበብ/ ጽዮን፡- እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስን አባት «አባታችን ሆይ» ብለን እንደምንጠራው ሁሉ ወላዲተ አምላክንም እናታችን ብለን እንጠራታለን፡፡ ማቴ.6-9፡፡ ቅዱስ ዳዊትም «እምነ ጽዮን ይብል ሰብእ፡ ሰው ሁሉ እናታችን ጽዮን ይላል» በማለት እመቤታችን አማናዊት ጽዮን መሆኗን አስረድቷል፡፡ መዝ.86-5፡፡ እምነ ጽዮን ማለት እናታችን ጽዮን ማለት ነው፡፡ በመጀመሪያይቱ የሰው ልጆች ሁሉ እናት ሔዋን አማካኝነት ከርስታችን ወጥተን መጠጊያ አጥተን ነበር በዳግማዊቱ ሔዋን በድንግል ማርያም ደግሞ ወደ ርስታችን ተመልሰናልና እናታችን ጽዮን እንላታለን፡፡ ጽዮን ማለት አንባ መጠጊያ ማለት ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስም ድንግል ማርያምን ጽዮን በማለት ይጠራታል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት «እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታልና ማደሪያውም ትሆን ዘንድ ወድዶአታልና እንዲህ ብሎ ይህች የዘላለም ማደሪያዬ ናትና በዚህች አድራለሁ፡፡» መዝ.131-13፡፡ በማለት የተናገረው ትንቢት ፍጻሜ ልዑል እግዚአብሔር ከሴቶች ሁሉ ለይቶ ድንግል ማርያምን ለእናትነት የመረጣት መሆኑንና ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ የወደዳት መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ መዝ.47-12፤86-5፡፡
መድኃኒታችን በዕለተ ዓርብ በቀራንዮ በመስቀሉ ላይ ሳለ ለፍቁረ እግዚእ ዮሐንስ «እነኋት እናትህ» በማለት በደቀ መዝሙሩ አማካኝነት እናቱን ድንግል ማርያምን ሥጋውን ለቆረሰላቸው ደሙን ላፈሰሰላቸው ምእመናን እናት ትሆን ዘንድ ሰጥቷታልና ከላይ እንዳየነው ጽዮን የድንግል ማርያም ስም ነውና ጌታችን እናት አድርጎ የሰጠንን እመቤት እምነ ጽዮን /እናታችን ጽዮን/ እንለታለን፡፡
እመ ብርሃን፡- እመ ብርሃን ማለት የብርሃን እናት ማለት ነው፡፡ «እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ» ያለውን ብርሃነ ዓለም /የዓለም ብርሃን/ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስን የወለደች ናትና የብርሃን እናቱ /እመ ብርሃን/ ትባላለች፡፡ ዮሐ.8-22፡፡ ጌታውን ይወድድ የነበረና ጌታውም ይወደው የነበረ የከበረ ደቀ መዝሙር ቅዱስ ዮሐንስ «ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር፡፡» በማለት የመሰከረለትን ጌታ በብሥራተ መልአክ በግብረ መንፈስ ቅዱስ አማናዊውን /እውነተኛውን/ ብርሃን ጌታችንን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ጸንሳ የወለደች በመሆኗ እመ ብርሃን እንላታለን፡፡ ሊቁ «እመ ብርሃን አንቲ ነዓብየኪ በስብሐት ወበውዳሴ፡- አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ የብርሃን እናት ነሽና አንቺን በክብር በምስጋና እናገንሻለን» በማለት እንዳመሰገናት፡፡
ሰአሊተ ምሕረት፡- ሰዓሊተ ምሕረት ማለት ምሕረትን የምትለምን ማለት ነው፡፡ በቅዱስ ገብርኤል ምስክርነት እንደምናገኘው ድንግል ማርያም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ያገኘች እመቤት ናትና ልመናዋ /ምልጃ ጸሎቷ/ ይሰማል የእናት ልመና አንገት አያስቀልስ ፊት አያስመልስ ነውና፡፡ ሉቃ.1-30፡፡
በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ያገኙ ቅዱሳን ምሕረት ቸርነትን ለምነው አግኝተዋል፡፡ ዘፍ.18-3፣ 23-32፡፡ እግዚአብሔር ሙሴን በፊቴ ሞገስን ስላገኘህ በስምህ ስላወቅሁህ ስለ ሕዝቡ የለመንኸኝን ሁሉ አደርጋለሁ ብሎታል፡፡ ዘጸ.33-12-20፡፡ «ስለ ሙሴ ቃልም ዘወትር ለሕዝቡ ይራራላቸው ነበር» ዘጸ.32-11-14፡፡ ሙሴ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ በማግኘቱ በለመነ ጊዜ እግዚአብሔር እንደ ቃልህ ይቅር አልሁ ይለው ነበር፡፡ ዘኁ.14-20፡፡ በመልአከ ብሥራት በቅዱስ ገብርኤል «በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝተሻል» ተብሎ የተመሰከረላት ድንግል ማርያም የተሰጣት ሞገስ እንደ እናትነቷ ከሁሉ የበለጠ በመሆኑ አጠያያቂ አይደለምና ሰአሊተ ምሕረት እንላታለን፡፡ ማርያም ንጽሕት ድንግል ወላዲተ አምላክ ዠማዕምንት ሰአሊተ ምህረት ለውሉደ ሰብእ፡- ንጽሕት ድንግል ማርያም የታመነች አምላክን የወለደች ናት ለሰዎች ልጆችም የምሕረት አማላጅ ናት» /ውዳሴ ማርያም ዘዓርብ አንቀጽ 6/
እመቤታችን፡- እመቤት ማለት በአንድ ቤተሰብ መካከል አስተዳዳሪና ሓላፊ የሆነች ታላቅ ሴት ማለት ነው፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን «ማርያም» የሚለውን በምሥጢራዊ ዘይቤ ሲተረጉሙ እግዝእተ ብዙኃን /የብዙኀን እመቤት/ ብለው ተርጉመውልናል፡፡
በአዳምና በሄዋን አማካኝነት ወደ ዓለም የገባውን መርገም የሻረ ጌታ እግዚአብሔር ከእርስዋ በመወለዱ እምቤታችን /የብዙዎች እመቤት/ ትባላለች፡፡ ሮሜ.5-6-11፡፡ እንዲሁም ዓለም ሁሉ በዳነበት በክርስቶስ የማዳን ሥራ ያመን ክርስቲያኖች ሁሉ በክርስቶስ አንድ ቤተሰብ በመሆናችን ቅድስት እናቱ ድንግል ማርያም እመቤታችን ናት፡፡ ዮሐ.19-26፡፡ ልጇ ጌታችን ነውና እርሷም እመቤታችን ናት፡፡ ሉቃ.1-43፡፡
ቤዛዊተ ዓለም፡- የዓለም መድኃኒት ማለት ነው ድንግል ማርያም የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስን ያስገኘችልን በመሆኗ ቤዛዊተ ዓለም እንላታለን በልጇ ቤዛነት ድነናልና፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም /ለድኅነተ ዓለም/ በቀራንዮ ኮረብታ የቆረሰው ሥጋ ያፈሰሰው ደም ከድንግል ማርያም የነሣው በመሆኑ ቤዛዊተ ዓለም ትባላለች፡፡ ዕብ.9-22፡፡ የሕያዋን ሁሉ እናት ድንግል ማርያም ለሔዋን ካሣዋ እንደሆነች ሁሉ ለአንስተ ዓለም ሁሉ ካሣ ቤዛ ናት ስድበ አንስትን ወቀሳ ከሰሳ አንስትን አስቀርታለችና፡፡ እንዲሁም ለዓለሙ ሁሉ የምታማልድ በልመናዋ ፍጥረትን የምታስምርና መንግሥተ ሰማያት መርታ የምታስገባ በመሆኗ ቤዛዊተ ዓለም እንላታለን፡፡
ወላዲተ አምላክ፡- ወላዲተ አምላክ ማለት አምላክን የወለደች ማለት ነው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል «ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፡፡» በማለት የጌታችንን አምላክ ወልደ አምላክነት የድንግል ማርያምን እመ አምላክ ወላዲተ አምላክነት አስረድቶአል፡፡ ሉቃ.1-35 ቅድስት አልሳቤጥም «የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?» ሉቃ.1-44 በማለት እንዳስረዳችው ድንግል ማርያም ጌታችንን የወለደች የጌታችን እናት ናትና ወላዲተ አምላክ እንላታለን፡፡ ድንግል ማርያም «ወላዲተ አምላክ» «አምላክን የወለደች» ተብላ እንድትጠራ ለመጀመሪያ ጊዜ በ431 ዓ.ም በኤፌሶን ከተማ በ200 ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አማካኝነት ተዘጋጅቶ በቅዱስ ቄርሎስ አፈ ጉባኤነት የተመራው 3ኛው ዓለም አቀፋዊ የቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ነው፡፡ በዚህ ጉባኤ የቀረበው የንስጥሮስ የክህደት ትምህርት «ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ ልትባል አይገባትም» የሚል ሲሆን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ንስጥሮሳዊውን ትምህርት አውግዘው ድንግል ማርያም ቅድመ ዓለም የነበረውን አምላክ ለዘመን በሥጋ ስለወለደችው በእውነት አምላክን የወለደች /ወላዲተ አምላክ/ ናት በማለት ትምህርተ ሐዋርያትን አጽንተዋል፡፡
በቤተ ልሔም በከብቶች ግርግም ከድንግል የተወለደው የዓለም ፈጣሪ እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህ ድንግል ማርያም ፣ እመ እግዚአብሔር ፣ ወላዲተ አምላክ ተብላ ትጠራለች፡፡ 1ዮሐ.5-20፤ ቲቶ.2-13፡፡
ኪዳነ ምሕረት፡- የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር መዓቱን በምህረት ቁጣውን በትዕግሥት በመመለስ የሰውን ሕይወት ለዘለዓለሙ ለመጠበቅ በመጀመሪያ ከስህተቱ በንስሐ ከተመለሰው ከአዳም፣ ቀጥሎም ከጻድቁ ከኖኅ፣ ከዚያም በእምነትና በምግባሩ ቀናነት የእግዚአብሔር ወዳጅ ተብሎ ከተሰየመው ከአብርሃም…. ከሌሎችም ቅዱሳን ጋር ለመላው የሰው ዘር የሚሆን የምህረትና የበረከት ቃል ኪዳን ገብቷል፡፡
«ከመረጥሁት ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ» መዝ.88-3 በማለት በተናገረው መሠረት ከምርጦቹ ጋር ቃል ኪዳን የሚያደርግ ልዑል አምላክ ከተመረጡ የተመጠረች በመሆኗ /ዋ/ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር የካቲት 16 ቀን ቃል ኪዳን ሰጥቷታልና ወር በገባ በ16 ቀን ወርኃዊ በዓሏን እናከብራለን፡፡
ይህንንም ለማመልከት ኪዳነ ምሕረት /የምሕረት ቃል ኪዳን የተቀበለች/ ትባላለች፡፡ በዚህም ምክንያት፡-
በእንተ ማርያም መሐረነ ክርስቶስ
ቅድስት ሆይ ለምኝልን
በእንተ ስማ ለማርያም ወዘተ
በማለት የተሰጣትን ቃል ኪዳን መማጸኛ በማድረግ እንጠራታለን፡፡ ምሳሌዋ የሆነች ሐመረ ኖኅ /የኖኅ መርከብ/ በተሰጣት ቃል ኪዳን ከማየ አይኅ /ከጥፋት ውኃ/ ነፍሳትን እንደ አዳነች ቅድስት ድንግል ማርያምም በተሰጣት ቃል ኪዳን ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ታድነናለችና ኪዳነ ምሕረት /የምሕረት ቃል ኪዳን/ የተሰጠሽ እንላታለን፡፡
ቅድስተ ቅዱሳን፡- ይህ ስም ከፍጡራን በላይ ከፈጣሪ በታች ለሆነች ቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሕናና ቅድስና መገለጫ ሆኖ የተሰጣት ልዩ ስም ነው፡፡ ቅድስተ ቅዱሳን ማለት ከተለዩ የተለየች ከተመረጡ የተመረጠች፣ ከተከበሩ የተከበረች ማለት ነው፡፡ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ድንግል ማርያምን ባመሰገነበት ክፍል ተሰመይኪ ፍቅርተ ኦ ቡርክት እምአንስት አንቲ ውእቱ ዳግሚት ቀመር እንተ ትሰመይ ቅድስተ ቅዱሳን፡- ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ የተባረክሽ ሆይ የተወደድሽ ተባልሽ ከተለዩ የተለየሽ» በማለት ቅድስናዋን መስክሯል /የእሑድ ውዳሴ ማርያም አንቀጽ 1/
ከአንስተ ዓለም ተለይተው ቅድስናን ገንዘብ ያደረጉ በርካታ ሴቶች ቢኖሩም ድንግል ማርያም ግን የነዚህ ሁሉ ፊት አውራሪ /ግንባር ቀደም/ እና ከሌሎች አንስት የተለየች ቅድስት /ቅድስተ ቅዱሳን/ ትባላለች፡፡ «አንቺ ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ» በማለት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል መስክሮላታል፡፡ ሉቃ.1-28፡፡ ከዚህም ጋር በተግባረ ቃል ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴው «የዐቢ ክብራ ለማርያም እምኲሎሙ ቅዱሳን፡- ከቅዱሳን ክብር የማርያም ክብር ይበልጣል» / ዘረቡዕ ውዳሴ ማርያም አንቀጽ .7/ በማለት የድንግል ማርያምን ቅድስና መስክሯል፤ ከዚህም የተነሳ በከበረ ስሟ ቅድስተ ቅዱሳን እያልን እንጠራታለን፡፡
ንጽሕተ ንጹሐን፡- ነጽሐ ነጻ ካለው ግሥ የወጣ ሲሆን ንጽሕት ማለትም የነጻች የጠራች ማለት ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት ስለ ንጽሕና «ዘንጹሕ ልቡ ወንጹሕ እደዊሁ፡- እጆቹም ልቡም ንጹሕ የሆነ»፣ «ብፁዓን ንጹሓነ ልብ ወይለብሱ ንጹሐ፡- ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው ንጽሕናን ይለብሳሉ»፣ «ሕያዋት ወንጹሓት፡- ሕያዋንና ንጹሓን»፣ «ንጽሕት ወብርህት፡- የነጻች የምታበራ» በማለት የንጽሕናን ሁኔታ ያስረዳሉ፡፡ መዝ.23፣ ማቴ.5-8፣ ራእ.15፣ ዘሌ.14-4፡፡ ውዳሴ ማርያም ዘአርብ፡፡
በዚህ ዓለም ከሚኖሩ ሴቶች የልማደ አንስት ኃጢአት ሰውነታቸውን ያላጐደፋቸው ወይም ያላረከሳቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ይሁንና ከገቢረ ኃጢአት ንጹሓን ይሁኑ እንጂ ከነቢብና ከሐልዮ ኃጢአት /በመናገርና በማሰብ ከሚሠራ ኃጢአት/ አልነጹም፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ከገቢር ከነቢብ ከሐልዮ ኃጢአት ንጽሕት ስለሆነች ንጽሕተ ንጹሐን እንላታለን፡፡
ወትረ ድንግል /ዘላለማዊት ድንግል/፡- ቅድስተ ቅዱሳን ወላዲተ አምላክ ማርያም ጌታን ከመጽነሷ በፊት፤ ጌታን በጸነሰች ጊዜ፤ ከጸነሰችም በኋላ፤ ከመውለዷ በፊት፤ በወለደች ጊዜ፣ ከወለደች በኋላ ድንግል ናት ከዚህም የተነሳ ድንግል ዘላለም እንላታለን፡፡ ክህነትን ከነቢይነት ጋር አስተባብሮ የያዘው ሕዝቅኤል ዘላለማዊ ድንግልናዋን መስክሯል፡፡ ሕዝ.44-1-2፡፡
የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ሳዊሮስ ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ዘላለማዊ ድንግልና በተናገረበት ክፍል «አምላክን የወለደች ማርያም ለዘለዓለሙ ድንግል እንደሆነች መውለዷም የማይመረመር ድንቅ እንደሆነ ከወለደችም በኋላ በድንግልና ጸንታ እንደኖረች አስረዳን» በማለት ስለ ዘላለማዊ ድንግልናዋ መስክሯል፡፡ ኢሳ.7.14፤ ሉቃ.1.27፡፡
ድንግል በክልኤ፡- በሁለት ወገን ድንግል ማለት ነው፡፡ በሁለት ወገን በሥጋም በነፍስም በሐልዮ /በሐሳብ/ በገቢር /በመሥራት/ በውስጥ በአፍአ ድንግል መሆኗን ያመለክተናል፡፡
ሌሎች ሰዎች ከገቢር ከነቢብ ቢጠበቁ ከሐልዮ /ከሃሳብ/ ኃጢአት መጠበቅ ግን አይቻላቸውም፡፡ ድንግል ማርያም ግን በሁለት ወገን ንጽሕት ቅድስት ናት ስለዚህ ድንግል በክልኤ /በሁለት ወገን ድንግል/ ትባላለች፡፡
ድንግል ወእም፡- እናትም ድንግልም ማለት ነው፡፡ እናትነትን ከድንግልና ጋር አስተባብሮ መገኘት ለፍጥረታዊ ሰው የማይቻል ቢሆንም ድንግል ማርያም ግን ሁለቱንም አስተባብራ ይዛለችና ድንግል ወእም ትባላለች፡፡
ሴቶች በልጅ ጸጋ ከከበሩ ድንግልናቸውን ያጣሉ በድንግልና ተወስነው ጸጋ እግዚአብሔርን ለማግኘት ከወሰኑ ደግሞ ከልጅ ጸጋ ይለያሉ፡፡ ሁለቱንም አስተባብረው ይዘው መገኘት አይሆንላቸውም፡፡ ድንግል ማርያም ግን ድንግልናን ከእናትነት እናትንትን ከድንግልና ጋር አስተባብራ ይዛ የተገኘች በመሆንዋ ድንግል ወእም እናትም ድንግልም ሆናለች፡፡ ሉቃ.1-26-38፡፡
ልጇ ክርስቶስም አምላክ ወሰብእ /ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው/ ሲባል እንዲኖር እርሷም ድንግል ወእም ስትባል ትኖራለች ስትወልደው ማኅተመ ድነግልናዋ እንዳልተለወጠ ሁሉ ባሕርየ መለኮቱ አልተለወጠም «እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም» እንዳለ፡፡ ሚል.3-6፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ሁሉም ምሥጢራዊና ትርጉም ያላቸው የእመቤታችን ስሞች የተገለጹት /የተነገሩት/ በራሱ በልዑል እግዚአብሔር እንዲሁም በቅዱሳን ነቢያት፣ በቅዱሳን ሐዋርያት፣ በቅዱሳን ጻድቃን ሰማዕታትና በሌሎችም ቅዱሳን አባቶች ነው፡፡
ይህም ምሥጢር የትምህርተ ሃይማኖት አንዱ አካል ሲሆን እኛም በቅዱሳን የተገለጸውን የእመቤታችንን ምሥጢራዊና ትርጉም ያላቸው ስሞች ተረድተን የትምህርተ ሃይማኖት ዕውቀታችንን ልናሳድግ ቅድስት ድንግል ማርያምንም ልናከብር እንዲገባን መገንዘብ አለብን፡፡ የቅዱሳንም አስተምህሮት ይህ ነውና፡፡
ስም አጠራሯ የከበረ ቅድስተ ቅዱሳን፣ እመ ብርሃን፣ ሰአሊተ ምሕረት፣ ድንግል ወእም፣ ወላዲተ አምላክ፣ እየተባለች የምትጠራ ድንግል ማርያም ረድኤትና በረከቷ አማላጅነቷ አይለየን፡፡ አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔ