የዝቋላ ደን ቃጠሎ ተጨማሪ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ተገለጠ፡፡
መጋቢት 11/2004 ዓ.ም
በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ
የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ደን ቃጠሎ ተጨማሪ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ተገለጠ፡፡
በቦታው የተገኙት የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም እንደገለጡልን በቦታው በርካታ ምእመናን ተገኝተው እሳቱን ለማጥፋት ጥረት ቢያደርጉም በአስቸጋሪው የአየር ጠባይ የተነሣ ፍህሙ እየተነሳ እንደገና እንዲያገረሽ ስለሚያደርገው ከፍ ያለ እርዳታ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ከመንገዱ አስቸጋሪነት እና ከፀሐዩ ግለት አንፃር ከእሳቱ ቃጠሎ ጋር ለሚታገሉ ምእመናንም የጥም ማስታገሻ የሚሆን ውሃ በመኪና ለማድረስ እንዳልተቻለ ከስፍራው የደወሉልን ምእመናን ገልጠውልናል፡፡
በአሁኑ ወቅት የእሳት አደጋው አርብ ረቡዕ በሚባለው ቦታ እየነደደ እንደሆነና የገዳሙን ደን የምሥራቁን ክፍል እየጨረሰ ወደ ደቡብ አቅጣጫ እየዞረ እንደሆነ ታውቋል፡፡ በአካባቢው ያለው ማኅበረሰብ ትብብር አነስተኛ እንደሆነባቸው ያልሸሸጉት ምእመናኑ፣ ለእርዳታ የሚመጡ ምእመናንም በተቻላቸው አቅም መጥረቢያ፣ አካፋና መቆፈሪያ ይዘው ቢመጡና ምእመናኑም እሳቱን ለማጥፋት አቅም ያላቸው ቢሆኑ ይመረጣል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በቅርብ ሰዓት በደረሰን መረጃ መሠረት፣ ከሌሊቱ 8፡00 አካባቢ እሳት ወደሚነድበት አካባቢ ለቅኝት የተጓዙ ምእመናን መሬት ላይ ያለው ፍሕም ነፋሱ በመራው አቅጣጫ እየተነሳ እንደሚያቀጣጥል መመልከታቸውንና ከቦታው አስቸጋሪነት አንፃር ምንም ማድረግ እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡
ለእርዳታ የተጓዘውን ምእመን የማስተናገድ ሸክም በገዳሙ ጫንቃ ላይ እንደወደቀ መነኮሳቱ የተናገሩ ሲሆን፣ ከጊዜ በኋላ ከዐቅም በላይ ሊሆን ስለሚችል ስንቅ በማቅረብ በኩልም ቢሆን ሊተባበሩ የሚችሉ ምእመናንን እርዳታ እንደሚሹ ገልጠዋል፡፡
አምላክ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በይቅርታው ይታደገን!!!