የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ደን ቃጠሎ መጥፋቱ ተገለጠ፡፡
መጋቢት 20/2004 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
- ገዳሙ አሁንም ድጋፍን ይሻል፡፡
የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ተከስቶ የነበረው ቃጠሎ መጥፋቱን የገዳሙ አበምኔት አባ ኢሳይያስ ገለጹ፡፡ ገዳሙም ተጨማሪ ርዳታና ድጋፍ እንደሚያስፈልገው አሳስበዋል፡፡
ረቡዕ ጠዋት መጋቢት 12 ቀን 2004 ዓ.ም የቅዱሳን ከተማ በሚባለው የመናንያን መናኸሪያ ጭስ ይታይ የነበር ሲሆን፣ በምእመናን፣ በፌደራል ፓሊስና በኦሮሚያ ፓሊስ አባላት ጥረት በቁጥጥር ሥር እንደዋለ በቦታው የነበሩት ምእመናን ገልጸውልናል፡፡ ሁለቱ ቀናት ረቡዕና ሐሙስ በተደረገው ርብርብ በገዳሙ አንደኛው አቅጣጫ ያለው የእሳቱ መንስኤ ለዘለቄታው ሊጠፋ እንደቻለ ከቦታው የደረሰን መረጃ ያስረዳል፡፡ በቅዱሳን ከተማ ያለውን እሳት የማጥፋት ጥረት ከጠዋቱ 12፡00 የጀመረ ሲሆን ወደ 9፡30 አካባቢ ሙሉ ለሙሉ ሊጠፋ ችሏል፡፡
እሳቱን ለማጥፋት ጥረት በሚደረግበት ጊዜ፣ አንድ የኦሮሚያ ፖሊስ አባልና አንድ ምእመን እሳቱ ላይ በመውደቃቸው ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፤ ወዲያውኑ ወደ ሕክምና እንደተወሰዱ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የፖሊስ አባሉ አደጋ እጁ ላይ ሲደርስበት ከቢሾፍቱ የመጣው ምእመን እግሩ ላይ ጉዳት ደርሶበታል፡፡
በተያያዘም የገዳሙን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከሚመለከታቸው ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተወካዮችና ከመስተዳድር አካላት ጋር በገደሙ አጠቃላይ ችግሮች ዙሪያ በስፋት መነጋገራቸውን አባ ኢሳይያስ ተናግረዋል፡፡
የመንገድና የውሃ ችግር በገዳሙ ላይ ጎልተው የሚታዩ ፈተናዎች መሆናቸውንና ይህንንም ለመፍታት የሁሉም ርብርብ እንደሚጠይቅ ያሳሰቡት አበምኔቱ ገዳሙ ያለውን የምግብ ፍጆታ በቃጠሎው ለተሳተፉ ምእመናን በማዋሉ ሊሟጠጥ ችሏል፡፡ በዚህም መሠረት ለመነኮሳቱ የሚሆን ቀለብ ባለመኖሩና ጊዜያዊ ችግር እንዳይገጥማቸው በማሰብ በማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል አማካይነት ከበጎ አድራጊ ምእመናን ያገኘውን የበሶ፣ የስኳርና የውኃ ልገሳ በትላንትናው ዕለት ወደ ገዳሙ በመውሰድ ለሚመለከታቸው አባቶች አስረክቧል፡፡
በቢሾፍቱ የማኅበረ ቅዱሳን ማእከል አባላት፣ በቢሾፍቱ ደብረ መዊእ ቅዱስ ሚካኤልና በቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያንም ገዳሙ ያለበትን ጊዜያዊ የውኃ ችግር ለመቅረፍ እንዲቻል ምእመናንን በማስተባበር ብዛት ያላቸው የውኃ ጀሪካኖችን በመሰብሰብ ውኃ በመሙላት ወደ ገዳሙ በማመላለስ ላይ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም በጎ አድራጊ ምእመናን ገንዘብ በማሰባሰብ ለሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ጥራጥሬና እህል በመግዛት ወደ ገዳሙ ለመውሰድ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት፣ የፌደራል ፓሊስ፣ የኦሮሚያ ፓሊስ፣ የአየር ኀይል፣ ማኅበራትና ምእመናን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፍቅር አስገድዷቸው ከሩቅም፣ ከቅርብም ወደ ገዳሙ በመገስገስ ቃጠሎውን ለማጥፋት ላደረጉት ከፍተኛ ርብርብ አበምኔቱ ምስጋናቸውን በራሳቸውና በማኅበረ መነኮሳቱ ስም አቅርበዋል፡፡