የዐቢይ ጾም ሳምንታት (ለሕፃናት) – ክፍል አምስት
በቴዎድሮስ እሸቱ
መጋቢት ፳፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
፯. ኒቆዲሞስ
እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ደኅና ናችሁ? መልካም! ይኸው ዘወረደ ብለን በመጀመሪያው ሳምንት የጀመርነው ጾም ዛሬ ኒቆዲሞስ ላይ ደርሷል፡፡ ኒቆዲሞስ የሰባተኛው ሳምንት መጠሪያ ነው፡፡ ልጆች! የአይሁድ መምህር የኾነ አንድ ኒቆዲሞስ የሚባል ሰው ነበር፡፡ ይህ የአይሁድ መምህር ማታ ማታ እየመጣ ከጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግር ሥር ቁጭ ብሎ ትምህርት ይማር ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ ማታ ማታ የሚማረው ለምን መሰላችሁ ልጆች?
አንደኛ የአይሁድ መምህር ስለ ኾነ አይሁድ ሲማር እንዳያዩት ነው፡፡ እነርሱ ሲማር ካዩት ገና ሳይማር ነው እንዴ እኛን የሚያስተምረን እንዳይሉት፤ ሁለተኛ አይሁድ በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎችን ከአገራቸው ያባርሩ ስለ ነበር እንዳይባረር በመፍራቱ፤ ሦስተኛ ሌሊት ምንም የሚረብሽና ዐሳብን የሚሰርቅ ጫጫታ ስለሌለ ትምህርቱ እንዲገባው ነበር፡፡ እናንተስ በሌሊት ትምህርታችሁን የምታጠኑት እንዲገባችሁ አይደል ልጆች? በሌሊት ዐሳባችሁ አይበተንም፡፡
ታዲያ አንድ ቀን ማታ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በስተቀር የእግዚአብሔር መንግሥት ሊወርስ አይችልም›› ብሎ ለኒቆዲሞስ ስለ ጥምቀት አስተማረው፡፡ ኒቆዲሞስም ‹‹ሰው ከሸመገለ ካረጀ በኋላ እንዴት በድጋሜ ሊወለድ ይችላል?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ ጌታችንም ዳግም ልደት ማለት ሰው በጥምቀት የሚያገኘው የእግዚአብሔር ልጅነት እንደ ኾነ፣ ሰው ተጠምቆ የእግዚአብሔር ልጅ ካልኾነ መንግሥተ ሰማያትን እንደማይወርስ አስተማረው፡፡ ኒቆዲሞስም ስለ ጥምቀት በሚገባ ተረዳ፡፡
ልጆች! በዚህ ሳምንት ከሚነገረው ከዚህ ታሪክ ዅል ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል መማር እንዳለብን፤ ያልገባን ነገር ካለ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ጠይቀን መረዳት እንደሚገባን እንማራለን፡፡ እናንተም እንደ ኒቆዲሞስ ቃለ እግዚአብሔር በመማር እና ስለ እምነታችሁ ያልገባሁን በመጠየቅ በቂ ዕውቀት ልትቀስሙ ይገባችኋል፡፡ ልጆች! ለዛሬ በዚህ ይበቃናል፤ ደኅና ሰንብቱ፡፡