የዐቢይ ጾም ሳምንታት
የካቲት 12 ቀን 2007 ዓ.ም.
ቅድስት(የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት)
የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)
ግነዩ ለእግዚአብሔር ወጸውዑ ስሞ ወንግርዎሙ ለአሕዛብ ምግባሮ ሀቡ ስብሐተ ለስሙ አክብሩ
ሰንበተ ተገበሩ ጽድቀ ዝግቡ ለክሙ መዝገበ ዘበሰማያት ኅበ ፃፄ ኢያማስኖ ወኢይረክቦ ሰራቂ ድልዋኒክሙ ንበሩ ዘበላዕሉ ጸልዩ ኀበ ሀሎ ክርስቶስ፡፡
ትርጉም:- ለእግዚአብሔር ተገዙ ስሙንም ጥሩ ሥራውንም ለአሕዛብ ንገሯቸው ለስሙም ምስጋናን ስጡ /አቅርቡ/ ሰንበትን አክብሩ እውነትንም አድርጉ ብል የማያበላሸው ሌባም የማያገኘው በሰማያት ያለ መዝገብን ለእናንተ ሰብስቡ፤ ተዘጋጅታችኹም ተቀመጡ ክርስቶስ ወዳለበት ወደ ላይ አስቡ፡፡
ምንባባት
መልዕክታት
1ኛ ተሰ.4÷1-12:- አሁንም ወንድሞቻችን ሆይ÷ በእኛ ዘንድ እንደ ታዘዛችሁ በሚገባ ትሄዱ ዘንድ÷ እግዚአብሔርንም ደስ ታሰኙ ዘንድ÷ ደግሞ እንደ ሄዳችሁ ከፊት ይልቅ በዚሁ ታበዙና ትጨምሩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እንነግራችኋለን፤ እንማልዳችኋለንም፡፡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም ያዘዝናችሁን ትእዛዝ ታውቃላችሁ፡፡
የእግዚአብሔር ፈቃድ ይህ ነውና፤ እርሱም ከዝሙት ትርቁ ዘንድ መቀደሳችሁ ነው፡፡ ሁሉም እያንዳንዱ ገንዘቡን ይወቅ፤ በንጽሕናና በክብርም ይጠብቀው፡፡ እግዚአብሔርን እንደማያውቁት እንደ አረማውያንም በፍትወት ድል አትነሡ፡፡ ይህንም ለማድረግ አትደፋፈሩ፤ በሁሉም ወንድሞቻችሁን አትበድሉ፤ አስቀድሜ እንደ ነገርኋችሁና እንደ አዳኘሁባችሁ÷ በዚህ ሁሉ እግዚአብሔር የሚበቀል ነውና፡፡ እግዚአብሔር ለቅድስና እንጂ ለርኲሰት አልጠራንምና፡፡ አሁንም የሚክድ÷ መንፈስ ቅዱስን የሰጣችሁን እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን የካደ አይደለም፡፡
ባልንጀሮቻችሁን ስለ መውደድ ግን ልንጽፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤ እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ራሳችሁ በእግዚአብሔር የተማራችሁ ናችሁና፡፡ በመቄዶንያ ሁሉ ካሉት ወንድሞቻችን ሁሉ ጋር እንዲሁ ታደርጋላችሁ፤ ነገር ግን ወንድሞቻችን ሆይ÷ ትበዙና ትጨምሩ ዘንድ÷ ሥራችሁንም ታከናውኑ ዘንድ እንደ አዘዝናችሁም በእጃችሁ ትሠሩ ዘንድ÷ በውጭ ባሉት ሰዎችም ዘንድ ከማንም አንዳች ሳትሹ በሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናችኋለን፡፡
1ኛጴጥ.1÷13:- ፍጻ. ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና ነቅታችሁ ኑሩ፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ፡፡ እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ክፉ ምኞት አትከተሉ፡፡ ነገር ግን የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እንዲሁ እናንተም በአካሄዳችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፡፡ “እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ” የሚል ተጽፎአልና፡፡ ለሰው ፊትም ሳያዳላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርድ አብን የምትጠሩት ከሆነ በሕይወታችሁ ዘመን ሁሉ በፍርሃት ኑሩ፡፡
ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከማይረባና ከማይጠቅም ሥራችሁ የተቤዣችሁ በሚጠፋ በወርቅ ወይም በብር እንዳይደለ ታውቃላችሁ፡፡ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክርስቶስ ክቡር ደም ነው እንጂ፡፡ ዓለም ሳይፈጠር የታወቀ÷ በኋላ ዘመን ስለ እናንተ የተገለጠ፡፡ ከሙታን ለይቶ በአስነሣው÷ ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ቃል ያመናችሁ÷ አሁንም እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሁን፡፡
ሳትጠራጠሩ በፍጹም ልቡናችሁ ወንድሞቻችሁን ትወድዱ ዘንድ÷ ለእውነት በመታዘዝ ሰውነታችሁን አንጹ፤ እርስ በእርሳችሁም ተፋቀሩ፡፡ ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፤ በሕያውና ለዘለዓለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ፡፡
ግብረ ሐዋርያት
የሐዋ.10÷17-29፡- ጴጥሮስም ስለ አየው ራእይ ምን እንደሆነ ሲያወጣና ሲያወርድ ከቆርኔሌዎስ ተልከው የመጡ ሰዎች የስምዖንን ቤት እየጠየቁ በደጅ ቁመው ነበር፡፡
ተጣርተውም፡- ጴጥሮስ የተባለ ስምዖን በእንግድነት በዚያ ይኖር እንደሆነ ጠየቁ፡፡ ጴጥሮስም ስለ ታየው ራእይ ሲያወጣ ሲያወርድ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ አለው÷ “እነሆ÷ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፡፡ ተነሥና ውረድ፤ ምንም ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ፤ እኔ ልኬአቸዋለሁና፡፡” ጴጥሮስም ወደ እነዚያ ሰዎች ወረደና÷ “እነሆ÷ የምትፈልጉኝ እኔ ነኝ፤ ለምን መጥታችኋል?” አላቸው፡፡
እነርሱም÷ “የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ እግዚአብሔርን የሚፈራ ጻድቅ ሰው ነው፤ ቅዱስ መልአክ ተገልጦ አንተን ወደ ቤቱ እንዲጠራህ የምታስተምረውንም እንዲሰማ አዝዞታል፤” አሉት፡፡ እርሱም ተቀብሎ አሳደራቸው፤ በማግሥቱም ተነሥቶ አብሮአቸው ሄደ፤ በኢዮጴ ከተማ ከሚኖሩት ወንድሞችም አብረውት የሄዱ ነበሩ፡፡ በማግሥቱም ወደ ቂሳርያ ከተማ ገባ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ጠርቶ ይጠብቃቸው ነበር፡፡
ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተቀበለው፤ ከእግሩ በታችም ወድቆ ሰገደለት፡፡ ጴጥሮስም÷ “ተነሥ እኔም እንደ አንተው ሰው ነኝ” ብሎ አነሣው፡፡ ከእርሱም ጋር እየተነጋገረ ገባ፤ ወደ እርሱም የመጡ ብዙ ሰዎችን አገኘ፡፡ ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው÷”ለአይሁዳዊ ሰው ሄዶ ከባዕድ ወገን ጋር መቀላቀል እንደማይገባው ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን ከሰው ማንንም ቢሆን እንዳልጸየፍና ርኩስ ነው እንዳልል እግዚአብሔር አሳየኝ፡፡ አሁንም ስለላካችሁብኝ ሳልጠራጠር ወደ እናንተ መጣሁ፤ በምን ምክንያት እንደ ጠራችሁኝ እጠይቃችኋለሁ፡፡”
ምስባክ
መዝ.95÷5 እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ አሚን ወሠናይት ቅድሜሁ ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ
ትርጉም፦ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ ምስጋና ውበት በፊቱ ቅዱሰነትና ግርማ በመቅደሱ ውስጥ ናቸው፡፡
ወንጌል
ማቴ.6÷16-24፡- “በምትጾሙበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ እነርሱ እንደ ጾሙ ለሰው ይታዩ ዘንድ መልካቸውን ይለውጣሉና÷ እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል፡፡ እናንተስ በምትጾሙበት ጊዜ ራሳችሁን ቅቡ፤ ፊታችሁንም ታጠቡ፡፡ በስውር ለሚያይ ለአባታችሁ እንጂ÷ ለሰዎች እንደ ጾማችሁ እንዳትታዩ፤ በስውር የሚያያችሁ አባታችሁም ዋጋችሁን በግልይ ይሰጣችኋል፡፡
“ብልና ነቀዝ በሚያበላሹት÷ ሌቦችም ቈፍረው በሚሰርቁበት በምድር ለእናንተ መዝገብ አትሰብስቡ፡፡ ነገር ግን ብልና ነቀዝ የማያበላሹት÷ ሌቦችም ዘፍረው በማይሰርቁት በሰማይ ለእናንተ መዝገብን ሰብስቡ፡፡ መዝገባችሁ ባለበት ልባችሁ በዚያ ይኖራልና፡፡
“የሰውነትህ መብራቱ ዐይንህ ነው፤ ዐይንህ ብሩህ ቢሆን ሰውነትህ ሁሉ ጨለማ ይሆናል፡፡ ዐይንህ ግን ታማሚ ቢሆን ሰውነትህ ሁሉ ጨለማ ይሆናል፤ በአንተ ላይ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ ጨለማህ እንዴት ይበዛ! ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው አገልጋይ የለም፤ ያለዚያ አንዱን ይወዳል፤ ሁለተኛውንም ይጠላል፤ ወይም ለአንዱ ይታዘዛል፤ለሁለተኛውም አይታዘዝም፤ እንግዲህ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም፡፡
ቅዳሴ
ዘኤጲፋንዮስ
ዐቢይ ውእቱ እግዚአብሔር በዕበዩ ቅዱስ በቅዳሴሁ እኩት በአኮቴቱ ወስቡሕ ስብሐቲሁ . . .
ትርጉም፡- እግዚአብሔር በገናንነቱ ገናና ነው በቅድስናው የተቀደሰ ነው በምስጋናው የተመሰገነ ነው በክብሩም የከበረ ነው. . .