የዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ምርጫ አስመልክቶ የቅዱስ ሲኖደስ ጽ/ቤት መግለጫ ሰጠ፡፡

ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

{gallery count=1 width=350 height=300 counter=1 links=0 alignment=center animation=3000}synodos{/gallery}

ብፁዕ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳሳ ዘአክሱም፣ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ፕሬዚዳንት ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ በመለየታቸው ቅዱስ ሲኖዶስ በዛሬው ዕለት ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ መረጠ፡፡

 

መግለጫውን የሰጡት ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የከፋ ሸካ ቤንችና ማጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ ሲሆኑ “በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ አንቀጽ 17 መሠረት ቀደምትነት ካላቸው ብፁዓን አባቶች መካከል በመምረጥ ዋናው የፓትርያርክ ምርጫ እስከሚከናወን ድረስ ብፁዕ አቡነ ናትኤል የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ሆነው እየሠሩ እንዲቆዩ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተወስኗል” በማለት ገልጸዋል፡፡

 

“የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊም ሆነ ማኅበራዊ ተግባር ዘርፈ ብዙ በመሆኑ ይህንኑ ከፍጻሜ ለማድረስ ቋሚ ሲኖዶሱን ማጠናከር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል” ያሉት ብፁዕነታቸው የዋናው ፓትርያርክ ምርጫ እስከ ሚከናወን ድረስ ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩና ከቋሚ ሲኖዶስ ጋር አብረው የሚሠሩ ሰባት አባላት መመረጣቸውን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

 

በዚህም መሠረት፡-

  1. ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊ

  2. ብፁዕ አቡነ ገብርኤል የሲዳማና ጌዴዎ አማሮ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

  3. ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

  4. ብፁዕ አቡነ ሉቃስ በክልል ትግራይ የምዕራብ ሴቲት ሁመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

  5. ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ

  6. ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የወላይታና ዳውሮ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

  7. ብፁዕ አቡነ አብርሃም የምሥራቅ ሀረርጌና የኦጋዴን አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተመርጠዋል፡፡

ሰሞኑን የዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ምርጫ ከቅዱስ ፓትርያርኩ ሥርዓተ ቀብር በኋላ እንደሚሆን የተገለጸ ቢሆንም ቅዱስ ሲኖዶስ ባደረገው ውይይት ዐቃቤ መንበር መምረጡ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ በመግለጫው ተወስቷል፡፡ እንደ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ገለጻ  “መንበሩ ያለ ሓላፊ መቆየት የሌለበት በመሆኑና ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የሚመጡ እንግዶችን ተቀብሎ የሚያሰናብት አባት መኖር አስፈላጊ ስለሆነ ቅድሚያ ተሰጥቶታል፡፡”

 

synodos akabi meneber

picture2