‹‹የወይን ግንድ ይቆረጣል›› (ተአምረ ማርያም)

መምህር ቢትወደድ ወርቁ
ሚያዝያ፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም

እውነተኛው የወይን ግንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራውን ይፈጽም፣ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል መፀነሡን ያበስር ዘንድ ወደ እመቤታችን በተላከ ጊዜ የተነገረ ቃል ነው፡፡ ቅዱስ ገብርኤል ብሥራትን ይናገር ዘንድ ወደ እመቤታችን በተላከ ጊዜ በግንባሩ ተደፍቶ ልዑል እግዚአብሔርን ‹‹ጌታ ሆይ! የምትነግረኝ ይደረግ ዘንድ እንደምን ይሆናል?›› አለው፡፡ ጌታም ‹‹የጀመርኩትን ቸርነት ፈጸምኩ፣ የወይን ግንድ ይቆረጣል፤ ወይራም ከበለስ ጋር ይተከላል፤ ቅጽሮችም ይቀጸራሉ (ምግባር ከሃይማኖት ጋር ይሠራል)፤ ገብርኤል ሆይ! ሄደህ ለዳዊት ልጅ ‹‹እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነውና ደስ ይበልሽ›› ብለህ አብሥራት›› አለው፡፡ ‹‹ለዘለዓለም ነግሦ የሚኖረውን እነሆ ትፀንሳለሽ በላት›› አለው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም ይህን ሰምቶ ሰገደ፡፡ ጌታችን ‹‹እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ›› በማለት እንደተናገረው የወይን ግንድ የተባለ እርሱ ነው፡፡ (ዮሐ.፲፭÷፩)

‹‹የወይን ግንድ ይቆረጣል›› የሚለውም ቃል ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ከዘለዓለም ሞት ያድናቸው ዘንድ በፈቃዱ እንደሚሞት የሚያስረዳ ኃይለ ቃል ነው፡፡ ‹‹ወይራም ከበለስ ጋር ይተከላል›› የሚለውም ቃል ቅዱስ መስቀል ድኅነተ ዓለም ይፈጸም ዘንድ፣ ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና መላእክት፣ ነፍስና ሥጋ፣ ሰማይና ምድር፣ ሕዝብና አሕዛብ ይታረቁም ዘንድ በቀራንዮ አደባባይ እንደሚተከል ያስረዳናል፡፡ (ቆላ.፩÷፳፣ ኤፌ.፪÷፲፪-፲፭) ‹‹ቅጽሮችም ይቀጸራሉ›› ማለትም በጌታችን ሕማምና ሞት ሃይማኖት ከምግባር በአንድነት እንደሚሠራ ያጠይቃል፡፡ (ያዕ.፪÷፩-፳፭) ይህን መሠረት እናድርግና ጥቂት ኃይለ ቃላትን ዘርዝረን እንመልከት፡-

‹‹የዓለም መድኃኒት (መድኃኔ ዓለም) እንደሆነ እናውቃለን!›› (ዮሐ ፬:፵፪)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እርሱ ብቻ የማይሞት ነው ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል›› ብሎ እንደመሰከረው አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በባሕርዩ ሞት በመንግሥቱ ሽረት በህልውናው ኅልፈት የሌለበት አምላክ ነው። (፩ጢሞ.፮፥፲፮፣ ሮሜ ፱፥፭፣ ኢሳ.፱፥፮፣ ፩ኛዮሐ.፭፥፳) እርሱ ፍጥረታትን ያለድካም የፈጠረ ፈጣሪ ነው፡፡ እርሱ መድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ ሞትን የቀመሰበትን ምክንያት ቅዱሳን ነቢያት ሐዋርያት ሊቃውንትም በልዩ ልዩ መንገድ ገልጠውታል፡፡

ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር ስለእኛ ተሰቀለ

ኃያላን ነን የሚሉትን በኃይሉ የሚመረምር ሊቃነ መላእክት ሠራዊተ መላእክት የሚታዘዙለት እርሱ ክርስቶስ ለምን እንደሞተ ቅዱስ ጴጥሮስ ሲመሰክር ‹‹ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት (በመስቀል) ላይ ተሸከመ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ›› ይላል። (፩ኛ ጴጥ.፪፥፳፬) ጌታ ስለ እኛ የሞተው ስለ ሁለት ምክንያት ነው፡፡ ለኃጢአት እንድንሞትና ለጽድቅ በጽድቅ እንድንኖር፡፡ ዓለሙ ክርስቶስ የሞተለት ለዚህ ቢሆንም ጉዞው ግን በተቃራኒው ሆኗል፡፡ በኃጢአት እየሞተ ጽድቅን ንቆና ጠቅጥቆ ለኃጢአት እየኖረ ነው፡፡ ዛሬስ እኛ ለምን እየኖርን ነው? ለጽድቅ ወይስ ለኃጢአት? ለእውነት ወይስ ለሐሰት? ለእንቢተኝነት ወይስ ለንስሐ?

ሞትን ይሽረው ዘንድ በመስቀል ተሰቅሎ ሞተ

ሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ በሰው ልጆች ላይ ሠልጥኖ ነበር፡፡ ሰዎችንም ለዘመናት ሲያስጨንቅና ሲገዛ ሲያስፈራቸውም ኖሯል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በቅዳሴው እንደተናገረው ጌታችን በሞቱ ሞትን ሻረው፡፡ ሞት በጌታችን ሞት በመሻሩም በዘመነ ሐዲስ የማያስፈራና ይልቁንም የሚናፈቅ ሆነ። ‹‹ልሔድ ከክርስቶስ ጋር ልኖር እናፍቃለሁ ይህ ከሁሉ የተሻለ ነውና›› እንዳለ ሐዋርያው፡፡ (ፊልጽ.፩፥፳፫)

የሰይጣንን ማሰሪያ ይበጥስ ዘንድ ሞተ

ሰው በሰይጣን ግዛት ማሰሪያ ታስሮ ይኖር የነበረ ፍጥረት እንደነበር መጻሕፍት ይመሠክራሉ፡፡ የታሰርን የነበርን በመሆናችንም ጌታችን በአህያና በውርንጫይቱ ምሳሌነት ደቀ መዛሙርቱን ‹‹የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ ፈታችሁ አምጡልኝ›› በማለት ከእስር የምንፈታበት ጊዜ እንደደረሰ ነግሮን በሞቱ ከእስራት ፈትቶናል፡፡ (ዕብ.፪፥፲፬፣ ማቴ.፳፩:፪)

ሲኦልን ይረግጥ ዘንድ ሞተ

ሲኦል የኃጥኣን ነፍሳት ታስረው ይኖሩበት የነበረና የሚኖሩበት የነፍሳት ወኅኒ የሰይጣንም ቤት ነው፡፡ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞቱ አስቀድሞ ሰይጣንን ‹‹ኃይለኛ›› ሲኦልን ‹‹የኃይለኛው ቤት›› ብሎ ጠርቶት ራሱ መድኃኒተ ዓለም ክርስቶስ ወደ ኃይለኛው ቤት ወደ ሲኦል ወርዶ ባዶ እንደሚያስቀረው አስተምሯል። (ማቴ.፲፪፥፴፫) ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችን በሥጋ ሞቶ በመለኮቱም ሕያው ሆኖ ወደ ወኅኒ ሲዖል ወርዶ ለነፍሳት ነፃነትን እንደሰበከላቸው መስክሯል። (፩ኛ ጴጥ.፫፥፲፱)

ነጻ ከወጣን በኋላ ዳግመኛ በባርነት ቀንበር አንያዝ

ሐዋርያው ‹‹በነጻነት ልንኖር (በጽድቅ በሕገ ወንጌል በንስሐ በፈቃደ እግዚአብሔር ልንኖር ክርስቶስ ነጻ አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ ዳግመኛም በባርነት ቀንበር አትያዙ›› ይለናል፡፡ (ገላ.፭:፩) በኑፋቄ በሥጋ ፈቃድ በሰይጣን ፈቃድ በዓለም ፈቃድ በዘረኝነት በጎጠኝነት በትዕቢት በትምክሕትና ሌሎችን በመናቅ መኖር በእውነት ታላቅ ባርነት ነው፡፡ ሰው ክርስቶስ በወርቅ ደሙ የዋጀው የገዛው በመሆኑ የራሱ ሳይሆን የክርስቶስ መሆኑን ቅዱሳኑ ነግረውናል። (፩ኛ ቆሮ.፮፥፲፱-፳)

በክርስቶስ ክርስቲያን ተብለን መንግሥተ ሰማያትን እንወርስ ዘንድ መከራ መስቀሉን እንቀበል!

የአምላካችን እግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን አማላጅነት አይለየን!