የወልደ ነጎድጓድ ልጆች እንቅስቃሴ
ሥርዓተ ትምህርት በመቅረጽ ለምዕመናን ጥሪ በማድረግ የሚያስተምረው ሰንበት ትምህርት ቤቱ በዓመት ሁለት መርሐ ግብሮች አሉት፣ በበጋና በክረምት የሚከናወኑ፡፡ ከሰኞ እስከ አርብ በማታው መርሐ ግብር እንዲሁም ቅዳሜና እሑድ ደግሞ በቀን መርሐ ግብር ለምእመናን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ያስተምራል፡፡ የተማሪዎችንም የክረምት እረፍት ተከትሎ ተጠናክሮ ይካሄዳል፡፡
በእድሜ ክልል በመክፈል ቀዳማይ፣ ካልዓይና ሣልሳይ በማለት የአንድ ዓመት ኮርሶችን ያስተምራል፡፡ ትምህርተ ሃይማኖት፣ ክርቲያናዊ ሥነ ምግባር፣ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ለዓለም መድረክና በኢትዮጵያ፣ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም የዮሐንስ ወንጌል አንድምታ ከሚሰጡት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡
ከጥሩ ተሞክሮዎቹ
ይህን ያህል የገነነ ተሞክሮ የለንም በማለት በትሕትና የሚገልጡት የሰንበት ትምህርት ቤቱ ሰብሳቢ አቶ አበበ ሥዩም ጥቂቶቹን ይገልጻሉ፡፡
ከአዲስ አበባ ወጣ ካሉ ሰንበት ትምህርት ቤት ጋር ጥሩ ግንኙነት እንደመሠረቱ የሚገልጡት አቶ አበበ ኪናዊ የሆነ ሥራዎችን በማዋስ፣ ልምድ ለማካፈል እንደሚያግዟቸው ይናገራሉ፡፡
በቤተ ክርስቲያንና በሰንበት ትምህርት ቤቱ ላይ ፈተና ሲመጣ መባ ይዞ በመሄድ ወይም በመላክ በጸሎት እንዲያስቡ ያደርጋሉ ሰንበት ትምህርት ቤቱ በራሱም የጸሎትና የጉባኤ መርሐ ግብር በማዘጋጀት በቂ ግንዛቤ ያስጨብጣል፡፡ አብዛኛው ምእመን ሱባኤ በመያዝ በየገዳማቱና የገጠር አብያተ ክርስቲያናት በሚያሳልፍበት በጳጉሜን ወር ትምህርት ጸሎትና ምክረ አበው በማዘጋጀት እንዲያሳልፍ ያደርጋል፡፡ ይሄም የሚናፈቅ እንደሆነ የሰንበት ትምህርት ቤቱ አባላት ይገልጻሉ፡፡
የአብነት ትምህርትን በማስተማር በኩል ሊጠቀስ የሚችል ሥራ ሠርቷል፣ ሰንበት ትምህርት ቤቱ እንደ ዲያቆን ወሳኙ ገለጻ ሰንበት ትምህርት ቤቱ የአብነት ትምህርት ማስተማር ከጀመረ ወደ ሰባት ዓመት አስቶጥሯል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ወደ 20 የሚጠጉ ዲያቆናት አፍርቷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በደብሩም ውስጥ የሚያገለግሉ አሉ፡፡ ቢሆንም የሚጠበቅበትን ያህል እየሄደ እንዳልሆነ የሚገልጹት ዲያቆን ወሳኙ ከዚህ በፊት የነበሩት አንድ መምህር ብቻ መሆናቸውና እርሳቸውም ደጅ ጠኚ ሆነው በትራንስፖርት /በመጓጓዣ/ አበል ብቻ ያስተምሩ እንደነበር ነው፡፡ ትምህርቱም ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾለት አለመሰጠቱ ሌላው ችግር ነው፡፡ ይህም የተፈለገውን ያህል ለማስፋፋት እንዳላስቻለ ይገልጻሉ ዲ/ን ወሳኙ፡፡
ሰንበት ትምህርት ቤቱ ለአብነት ትምህርቱ ምእመናን እንዲሳተፉ ቅስቀሳ የሚካሄደው የደብረ ታቦር ዕለት ነው፡፡ የቆሎ ትምህርት ቤትን ገጽታ የሚያሳይ ኪናዊ ሥራ በማሳየት አውደ ምሕረት ላይ ቅስቀሳ ይደረጋል፡፡ ምንም እንኳን በርካታ ወጣቶች ቢመዘገቡም፤ ጥቂቶች ብቻ ለውጤት እንደሚበቁ ይገልጻሉ ዲ/ን ወሳኙ፡፡ አሁን ግን ቤተ ክርስቲያኗ የአብነት መምህር በመቅጠሯ የተሻለ የመማር እድል አለ፡፡
የወደፊት እቅድ
በጅምር ላይ ያለው የሰንበት ትምህርት ቤቱ አዳራሽ ሲያልቅ በውስጡ የእደ ጥበብ ሥራዎችን በማምረት ያከፋፍላል፣ ይሸጣል፣ ከሌሎች ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ማኅበራት ጋር በመቀናጀት ሙያዊ ሥልጠናዎችን፣ ተሞክሮዎችንና ድጋፍ ካገኘ በኋላ የልማት ሥራዎችን ይሠራል፡፡
በመጪዎቹ አሥር ዓመታት ውስጥ የአብነት ትምህርት ቤቱን በማጠናከር አብነት መር የሆነ ሰንበት ትምህርት ቤት ለመፍጠር እቅድ አለ፡፡ ይህንንም ለመፈጸም ጥናቱን አጠናቆ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል ዲ/ን ወሳኙ፡፡
ሁሉም ሰንበት ትምህርት ቤቶች እጅ ለእጅ ተያይዘን አንዲት ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ቆርጠን መነሣት አለብን በማለት የሚያሳስቡት የሰንበት ትምህርት ቤቱ አቶ አበበ ስዩም በአሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን የገጠማትን ከበድ ያለ ወቅታዊ ፈተና ያነሣሉ፡፡
በቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ምድር ቤት ፊት ለፊት ደረጃው ሥር ባሉ ክፍሎች በመሰባሰብ የተጀመረው ሰንበት ትምህርት ቤቱ፣ ቀጥሎም በክርስትና ቤት፤ የአባላት ቁጥር ሲጨምርም ትልቅ የቆርቆሮ ቤት በመሥራት እንዲቀጥል ሆኗል፡፡ በእግዚአብሔር ፈቃድ የያኔው ተክል እያበበ እያፈራ 43 ዓመቱን ያከበረው ባለፈው ከግንቦት 19 እስከ 21 ቀን 2003 ዓ.ም ለሦስት ቀናት በተዘጋጀ መርሐ ግብር ነበር፡፡ የሰንበት ትምህርት ቤቱ የኪነ ጥበብ ክፍል ከላሊበላ አርቲስቶች ጋር በመተባበር “ተዋሕዶ” በሚል ርዕስ ያዘጋጁትን ድራማ ለምእመናን አቅርበዋል፡፡ በሦስቱ ቀን መርሐ ግብር የልማትና የጸሎት ክፍል የጸሎት መርሐ ግብር አዘጋጅቶ ነበር፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ጉዳይና አጽራረ ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተም በጉባኤው ላይ ለታደሙት ምእመናንና ተጋባዥ እንግዶች መረጃ እንደደረሰ ዲ/ን ወሳኙ ዘውዴና አቶ አበበ ስዩም ገልጸዋል፡፡