የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ግፍ እየተፈጸመባቸው መሆኑ ተገለጸ
በሕይወት ሳልለው
በአለፉት ሳምንታት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ተማሪዎችን ከሚማሩበት ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች በማሳደድ እና የተወሰኑትን እንዳይወጡ በማገድ ሙሉ በሙሉ ከትምህርት ማፈናቀል የጀመሩት የጥፋት ኃይሎች በመቱና ቦንጋም ተመሳሳይ ድርጊት እየፈጸሙ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ይህም በዋነኛነት በመቱ ዪኒቨርስቲ እንደተባባሰ የገለጹት የዪኒቨርስቲው ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር ኦልቀባ አሰፋ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ተማሪዎች ከአዳራሽ ውስጥ መውጣት በማይችሉበት ደረጃና ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡ ተማሪዎቹ ለሃይማኖታቸው መሥዋዕት በመክፈላቸው ዛቻና ማስፈራሪያም ተደርጎባቸዋል፤ ካሉበት ቦታ መውጣት አለመቻላቸውም ታውቋል፡፡
ቦንጋ ውስጥ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓትን ማለትም ነጠላ የመልበስና በጾም ጊዜም የጾም ምግብ የመመገብ መብታቸውን እንዲያስጠብቁላቸው የጠየቁት ስድስት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ተማሪዎች ከዪኒቨርስቲው ተባረዋል፡፡ ይህንም ያብራሩት የተማሪዎቹ ኅብረት ተዋካዮች የዪኒቨርስቲውን አስተዳደሮች መብታቸውን እንዲጠብቁላቸው ቢጠይቁም ሁለት ተወካይ ተማሪዎችን በመላክ ጥያቄያቸውን እንዲያቀርቡ አሳወቋቸው፡፡ ሆኖም ተማሪዎቹ ያንን ባለመቀበል ጥያቄዎቹን ያነሱትም ሆነ ችግራቸውን የሚፈቱት በአንድነት እንደሆነ በማሳወቅ በአቋማቸው በመጽናታቸው ለተለያዩ ችግሮች እንደተጋለጡ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም በኋላ በሌሎች ተማሪዎች ችግር እንደፈጠሩባቸው አያይዘው ገልጸዋል፡፡ ስሜታቸውን ለመጉዳትም አስከፊ ንግግሮችንና ዘለፋዎችን በመጠቀም ተስፋ ሊያስቆርጧቸው እየሞከሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በተያያዘም ፳፮ የሚሆኑ ተማሪዎች የተባራሪ ስም ዝርዝር ውስጥ መመዝገባቸውን ተማሪዎቹ አስታውቀዋል፡፡
በዚህም ጉዳይ ዙሪያ የዩኒቨርስቲውን አስተዳደሮች ለማነጋገር ተሞክሮ ሐሳባቸውን የሰጡ ቢሆንም ምንም ችግር እንደሌለና አሉባልታ ወሬ መሆኑን ማስተባበላቸው ታውቋል፡፡ ሆኖም እነዚህ ተማሪዎች ያሉበትን ሁኔታና ችግር የተለያዩ ምንጮች የሚያመለክቱት አስከፊ መሆኑን ነው፡፡
የዚህ ጥቃት ሰለባ ላለመሆን ከሰባት እስከ ስምንት መቶ የሚደርሱ ተማሪዎች ምዕራብ ሐረርጌ ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ አብዛኛዎቹ ተማሪዎችም በተፈጠረው ረብሻ የተነሳ ትምህርታቸውን በማቋረጥ ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በግለሰብ ቤቶች ውስጥ ሲጠጉ እንዲሁ ጤና ጣቢያም ተጠልለው እንደሚገኙ ምንጮቹ ጨምረው ገልጸዋል፤ በሐረማያ ከተማ ሃያ የሚሆኑ ተማሪዎች በገጀራና በዱላ መደብደባቸውም ታውቋል፤ ለዚህም ረብሻውን ራሳቸው የጥፋት ኃይሎቹ ከጀመሩ በኋላ አራት ግለሰቦችን ያለጥፋታቸው በአዳማ ክስ በመመሥረት በፍርድ ቤት የአራት ዓመት እስር አስፈርደውባቸዋል፤ በዚህም ሳያቆሙ በድሬድዋ ሁለት ሰዎችን እንደገደሉና ሴቶችን እየደፈሩ መሆኑን ዘገባዎች ያስረዳሉ፡፡
በሐረር ከተማ አክራሪ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ክርስቲያኖችን ለማጥፋት እያደረጉ ባለው እገታና ጭፍጨፋ የተነሳ ተሰደው ለሚገኙ ተማሪዎች የምግብም ሆነ የሕክምና አቅርቦት መስጠት አልተቻለም፡፡ በዚህም የታማሚው ቊጥር በየቀኑ በመጨመሩና ችግሩም በመባባሱ በድሬድዋ የሚገኙ ወጣቶች በመደራጀት ለተወሰኑ ተማሪዎች እርዳታ ያቀረቡ ቢኖሩም አሁንም በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች እንደሁም ምእመናን በእገታና ችግር ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ይህ ችግር ሁሉንም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮችን ይመለከታልና የተቻለውን ትብብር ለማድረግ መረባረብ ያስፈልጋል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዳለው ‹‹እውነት እላችኋለሁ÷ በእኔ ከአመኑ ከነዚህ ከታናናሾች ወንድሞቼ ለአንዱ የአደረጋችሁትን ሁሉ ለእኔ አደረጋችሁት››፡፡ (ማቴ. ፳፭፥፵)
በክርስቶስ ፍቅር ክርስቲያኖች እንሆንም ዘንድ ‹‹በእኛና በአንተ መካከል ያለውን ፍቅርና አንድነትን ይቅርታህን አድርግልን›› ተብሎም እንደሚጸለየውም (የረቡዕ ሊጦን) ይህን ጥቃት በመቃወም የተቸገሩትን በመርዳት፤ የታሰሩትን በመጠየቅ እንዲሁም መንፈሳዊ ድጋፍ በመለገስ ልንታደጋቸውና ልናግዛቸው ይገባል፡፡ ‹‹ተርቤ አብልታችሁኛልና÷ ተጠምቼም አጠጥታችሁኛልና÷ እንግዳም ሆኜ ተቀብላችሁኛልና÷ታርዤ አልብሳችሁኛልና÷ ታምሜ ጎብኝታችሁኛልና÷ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና›› (ማቴ. ፳፭፥ ፴፭) ይለን ዘንድም ወገኖቻችንን እንርዳ!