የእግር ጉዞው ምዝገባ ሊጠናቀቅ ቀናት ቀሩት
ግንቦት 16/2004 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
{gallery count=1 width=350 height=300 counter=1 links=0 alignment=center animation=3000}yeger guzo{/gallery}
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የማኅበረ ቅዱሳን 20ኛ ዓመት ምሥረታን ምክንያት በማድረግ “ለሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት አብረን እንሥራ” በሚል መሪ ቃል ግንቦት 26 ቀን 2004 ዓ.ም. የእግር ጉዞ መዘጋጀቱ ይታወቃል፡፡ የመርሐ ግብሩ ዐቢይ ኮሚቴ አስተባባሪ ዲ/ን ዋሲሁን በላይ የእግር ጉዞው ምዝገባ በፍጥነት እየተካሔደ መሆኑንና በርካታ ቲኬቶችና ካናቴራዎች በመሠራጨት ላይ እንደሚገኙ እንዲሁም ሊጠናቀቅ ቀናት እንደ ቀሩት ገልጸዋል፡፡
ዲ/ን ዋሲሁን በላይ ለምእመናን ባስተላለፉት መልእክት፡- “ዋናው የጉዞው ዓላማ የማኅበራችን 20ኛ ዓመት ምሥረታ ነው፡፡ በ20 ዓመታት ውስጥ ማኅበረ ቅዱሳን ብቻውን የፈጸመው የቤተ ክርስቲያን አገለግሎት የለም፡፡ ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከቤተ ክርስቲያኒቱ የተለያዩ አካላትና ጽ/ቤቶች፣ ከሠራተኛ ጉባኤያት ከሰንበት ትምህርት ቤቶች በተለይም ከምእመናን ጋር በኅብረት ሠርተናል፡፡ አብረን ከተጓዝናቸው፣ እስካሁንም ደከመን ሰለቸን ሳይሉ በምክራቸው በጸሎታቸው በእውቀታቸው፣ በገንዘባቸውና በጉልበታቸው እያገለገሉ ካሉ አካላትና ምእመናን ጋር በኅብረት እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት ቀን ነው፡፡ ቀጣይ ጊዜያችን ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ጠንክረን አብረን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከእኛ የምትፈልገውን አገልግሎት የምንፈጽምበት እንዲሆን ቃል የምንገባበት ዕለት ነው፡፡” በማለት የገለጹ ሲሆን ምእመናን የተዘጋጀውን ቲኬት በመግዛት በእግር ጉዞው እንዲሳተፉና የበረከቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አንዳንድ ምእመናን እንደሚገልጹት ጉዞው ማኅበረ ቅዱሳን ከዚህ በኋላ ላሉት የአገልግሎት ዘመናት ዘመኑን የዋጅና እየመጣ ያለውን የትውልዱን አስተሳሰብና የአኗኗር ለውጥ ማዕከል ያደረገ አገልግሎት እንዲያበረክት ድልድይ እንደሚሆነው ይገልጻሉ፡፡