‹‹የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል›› (ዮሐ.፲፮፥፲፫)
ዲያቆን ሚክያስ አስረስ
ይህች ዓለም ከእውነት የራቀች መኖሪያዋን በሐሰት መንደር ያደረገች መሆኗ ይታወቃል፡፡ ሰው ማንነቱን አጥቶ በበደል ምክንያት በሐሰት ኖሯል፡፡ ሰው በፈቃዱ ጥፋት ምክንያት ከሚፈጽማቸው በደሎች ትልቁ በደል ውሸት ነው፡፡ ውሸት ተሸንፎ ይወድቃል፤ ከሕይወት ይርቃል፡፡ የኀጣአን ሁሉ ራስ ሐሰት ናት፡፡ ክፋትን ከራሱ አንቅቶ የበደለ ዲያብሎስ ‹‹አቡሃ ለሐሰት፤ የሐሰት አባት›› የተባለው ለዚህ ነው (ዮሐ.፰፥፵፬)፡፡
አዳም እና ሔዋንን ለሞት የተዳረጉት ያልሆኑትን፤ ሊሆኑ የማይችሉትን እንሆናለን ብለው ከሐሰት ጋር መተባበራቸው ነው፡፡ ሐሰት የሆኑትንና የተሰጣቸውን እንዲዘነጉ አድርጎ ማግኘት የማይችሉትን የባሕርይ አምላክነትን አስመኛቸው፡፡ እነርሡ በበደል ወድቀው፤ ከገነት ርቀው ልጆችን በመውለድ ሲባዙ ሐሰት ግዛቷን አስፍታ በኃይል በርትታ እውነት እስኪገለጥ ድረስ ቆየች፡፡ እውነት እግዚአብሔር በሰው ባሕርይ ሲገለጥ የእውነት መንገድን (ሃይማኖትን) ዳግመኛ ሰጠ፡፡ የዓለም መድኃኒት ክርስቶስ የፈጸመውን ድኅነት ለማግኘት ሰው ሐሰት ከተባሉ አምልኮ ጣዖት፣ ራስ ወዳድነት እና ሴሰኝነት ርቆ በእውነት ሊኖር የግድ ነው፡፡ እርሡ ሁሉ እንዲድኑ እውነትንም እንዲያውቁት ይወዳልና፡፡(፩ ጢሞ. ፪፥፬) እንደተባለ ሰውም ቢሆን በእውነት ጸንቶ ለመኖር በመፍቀድ ከእግዚአብሔር ጋር በፈቃድ አንድ መሆን አለበት፡፡
የአንድነትና ሦስትነት ምሥጢር የተገለጠው አምላክ ሰው በመሆኑ ነው፡፡ ይልቁንም ሰው ወደዚህ እውነት እንዲመጣ የሚያደርገው መንፈስ ቅዱስ ወደ ደቀመዛሙርት የወረደው ሰው የሆነ አምላክ ክብሩን በመስቀል ሞት ሲገልጽ ነው፡፡ ክርስቶስ ስለእኛ ብሎ በመስቀል ላይ ባይሞት መንፈስ ቅዱስ አይወርድም ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አባቱ መንፈስ ቅዱስ እንደሚመጣ ለቤተ ክርስቲያንም ሕይወት እንደሚሆናት የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል (ዮሐ. ፲፮፥፲፫) በማለት አስቀድሞ ተናገረ፡፡ መንፈስ ቅዱስ መምጣቱ አምላክ ሰው ሆኖ የፈጸመውን ለመረዳት እና ለማመን ለማስቻል ነው፡፡ ክርስቶስን በመድኃኒትነቱ ለመግለጽም ነው፡፡ ለዚህ ነው የተወደደ ሐዋርያ ዮሐንስ መነሻ ያደረግነውን ኃይለ ቃል ከተናገረ በኋላ ‹‹ወውእቱ ኪያየ ይሴብሕ፤ እርሱ እኔን ይገልጻል፡፡›› (ዮሐ.፲፮፥፲፬) ያለው፡፡ እንዲሁ አዳም በበደል ከወደቀ በኋላም በሥላሴ ፈቃድ በወልድ ሰው መሆንና በመንፈስ ቅዱስ መሠጠት ከወደቀበት ተነሥቶ ድኅነት (ሁለተኛ ተፈጥሮ) ተፈጸመለት፡፡ እርሱ ሲፈጠር መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ እንደከበረ (ዘፍ.፪፥፩) እንዲሁ ይኸው መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል ለክርስቶስ ደቀመዛሙርት ወረደ፤ ጸጋ ሆኖ ተሠጣቸው፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት መንፈስ ቅዱስን ደጅ እንዲጸኑ ይኸንንም በኢየሩሳሌም በአንድነት በመቆየት እንዲያደርጉ አዘዛቸው፡፡ (ሉቃ.፳፬፥፵፱) ደቀ መዛሙርቱም መቶ ሃያ ሆነው በኢየሩሳሌም በማርቆስ እናት ቤት አስቀድሞ ምሥጢረ ቁርባን በተመሠረተበት ቦታ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እናት እመቤታችንን በመሐል አድርገው በጸሎት በአንድነት በኢየሩሳሌም ቆዩ፡፡ (ሐዋ.፩፥፲፬)፡፡ እመቤታችን ባለችበት መንፈስ ቅዱስ ይወርዳልና፤ አስቀድሞ በወንጌል ቅድስት ኤልሳቤጥ እመቤታችን ወደ እርሷ ስትሄድ ኤልሳቤጥ ላይ መንፈስ ቅዱስ ሞላባት (ሉቃ.፩፥፵፩) ተብሎ እንደተነገረላት፡፡ ከዚያም ረቂቅነቱን እና ኃያልነቱን ሲያጠይቅ መንፈስ ቅዱስ ከወደ ሰማይ እንደ ዐውሎ ነፋስ ባለ ድምፅ መጣ፡፡ ደቀመዛሙርት ባሉበት ቤት ገብቶ ሲመላው የተከፋፈሉ የእሳት ልሳኖች ሆኖ ታያቸው፤ በሁሉም አደረባቸው (ሐዋ.፪፥፫) ሁሉም ኃይልን ዕውቀትን አገኙ፤ በሀገራትም ሁሉ ቋንቋዎች ተናገሩ፡፡ ስለ እውነት ደፋሮች ሆኑ፡፡ በነቢይ እሰውጥ እምነ መንፈስየ ዲበ ኩሉ ዘሥጋ፤ በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ (አዩ. ፫፥፩) ተብሎ የተነገረው ዛሬ ተፈጸመ፡፡
አንዲት ቤተክርስቲያንን በአንድነቷ ለዘለዓለም የሚያኖራት እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ እንዲህ ስንል አብን እና ወልድን በመተው አይደለም፡፡ የሦስቱም ማደርያ ትሆናለች እንጂ፡፡ ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ምሥጢራትን ይገልጥልን ዘንድ አለ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን›› (፩ቆሮ.፪፥፲፮) እንዳለው የክርስቶስ ልብ የሆነ እግዚአብሔር አብ በክርስቶስ ክርስቲያን በተባልን በቤተ ክርስቲያን አለ ማለቱ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተለየ አካሉ ሰው ሆኖ በሕማሙ እና በሞቱ፤ በትንሣኤውና በዕርገቱ ድኅነትን ፈጸመ፡፡ አሁንም በቤተ ክርስቲያን እርሱ ሊቀ ካህናት ኢየሱሰ ክርስቶስ በአባቶች ካህናት ላይ በረድኤት አድሮ ምሥጢራትን ይፈጽማል፡፡ ‹‹….ኦ እግዚኦ በከመ አሜሃ ዘንተ ኅብሰተ ባርክ ወቀድስ ወወሃብ፤ አቤቱ እንደዚያን ጊዜ ይህን ኅብስት ባርከው ሥጋህን አድርገው ቁረሰው እንዲሁ ስጥ›› (ቅዳሴ ማርያም) የተባለውን ማስተዋል በቂ ነው፤ መንፈስ ቅዱስ የአንድነት መንፈስ ነውና፡፡
ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የሚያደርጉንን ምሥጢራት ራሱ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ያከናውናቸዋል፡፡ ካህኑ ውኃውን ሲባርኩት በዕለት ዓርብ ከጌታ ጎን የፈሰሰውን ውሃ ያደርግላቸዋል በዚያ ማየገቦ (የጎን ውሃ) አዲስ አማኝ ተጠምቆ የእግዚአብሔርን ልጅነት አግኝቶ ከእርሱ ጋር አንድ ይሆናል፡፡ ካህናቱ የከበረውን የቅዳሴ ጸሎት ሲጀምሩ ያቀረቡትን ኅብስት እና ወይን እንዲህ ነው በማይባል አኳኋን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ እና ደም የሚያደርገው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ከእርሱ ጋር አንድነትን እናገኛለን፡፡ ሰው ንስሐ እንዲገባ በበደሉ እንዲጸጸት በሰው ውስጥ ሆኖ የንስሐን ደወል የሚያሰማው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ይህን የንስሐ ጥሪ በእሽታ ቢቀበል ዳግመኛ ከቤተ ክርስቲያን ተደምሮ ከእግዚአብሔር ጋር በአንድነት ይኖራል፡፡ ጥሪውን በእንቢታ አልፎ እስከ ሞት ድረስ በዚህ ቢጸና መንፈስ ቅዱስን ተሳድቧልና ኃጢአቱ አይሠረይለትም፤ ከሞት በኋላ ንስሐ የለምና፡፡ (ማቴ. ፲፪፥፴፪) ለተቀበሉት ግን አሁንም መንፈስ ቅዱስ አንድነትን የሚያድል መሆኑን እናስተውል፡፡ እኛ እርስ በእርስ በአንዲት ሃይማኖት ተባብረን ከአንድ መሥዋዕት ተካፍለን አንድ ርስትን ተስፋ በማድረግ አንድ የሚያደርገን እርሱ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡
በቅዳሴያችን ሀበነ ንኅበር በዘዚአከ መንፈስ ቅዱስ፤ ባንተ ህልውና ባለ መንፈስ ቅዱስ አንድ አድራጊነት አንድ እንሆን ዘንድ አንድ መሆንን ሰጠን፤ በማለት አንድ አድራጊያችን እርሱ እንደሆነ እንመሠክራለን፡፡ አንድ ሆነን በአንድነት ከጸናን እንደ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል የበቃን የተዘጋጀን ስለምንሆን ቀጥለን ፈኑ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ላዕሌነ፤ በእኛ ላይ ጸጋ የሚባል መንፈስ ቅዱስን ላክ በማለት እንለምናለን፡፡ በዚህ በግዙፉ ዓለም ባለች ሰማያዊ መንግሥት በቤተ ክርስቲያን እንደተባበርን በዚያች ለምድራውያን ሰዎች ዓለም ሳይፈጠር በተዘጋጀችው መንግሥት አንድ እንሆናለን፡፡ ሐዋርያው መንግሥተ ሰማያትን የእግዚአብሔር መንግሥት በመንፈስ ቅዱስ የሆነ ደስታ እንጂ መብል መጠጥ አይደለምና (ሮሜ.፲፬፥፲፯) በማለት ይናገርላታል፡፡
መንፈስ ቅዱስ በወረደላቸው ዕለት ደቀ መዛሙርት ምሥክርነታቸውን ማሠማት ጀመሩ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ሕዝቡ በተሰበሰቡበት በዚያን ዕለት መንፈስ ቅዱስ መውረዱና እነርሱ በቋንቋዎች መናገራቸው እንዲሁ እንደ እንግዳ ደርሶ የመጣ ሳይሆን አስቀድሞ በነቢያት ትንቢት የተነገረ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ዳግመኛም ክርስቶስ በነቢያት እንደተነገረለት ሞቶ ከሙታን እንደተነሣ ሰበከላቸው፡፡ የሚሰሙት ሕዝቡ እርሱ የተናገራቸው ከልባቸው ስለገባ ምን እናድርግ አሉ (ሐዋ. ፪፥፴፯)፡፡ ነስሑ ወተጠመቁ ኩልክሙ በስሙ ለኢየሱስ ክርስቶስ፤ ንስሐ ግቡ ሁላችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምናችሁ ተጠመቁ (ሐዋ.፪፥፴፰) ብሎ ቅዱስ ጴጥሮስ መለሰ፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ ነፍሳት ወደ ገነት እየተደመሩ ቤተክርስቲያን ከኢየሩሳሌም እስከ ዓለም ዳርቻ ምሥክርነቷን አደረሠች፡፡ እንዲሁ ሰው የክርስትናን ጥምቀት ተጠምቆ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ገንዘብ ካደረገ ከሚኖርበት ከቤቱ ጀምሮ ምሥክር ሆኖ ወደ ዓለም መውጣት እንዳለበት መገንዘብ ይቻላል፡፡
ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ቸርነት ምእመናን እንዲያገኙና ለዓለሙ ሁሉ ምሥክር እንዲሆኑ ታስተምራቸዋለች፡፡ በዓለም ሲኖሩ በፈቃዱ በመኖር ያገለግሉ ዘንድ ስለእግዚአብሔር ምሕረት በምግባራቸው ለዓለም ይመሠክራሉ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር