የእመቤታችን በዓለ ዕርገት
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያረገችበት ዕለት ነሐሴ ዐሥራ ስድስት ቀን በቤተ ክርስቲያናችን ይከበራልና እኛም ስለዕርገቷ እንዲህ እንዘክራለን፤…
ሐዋርያት ከእመቤታችን ድንግል ማርያም ዕረፍት በኋላ ከእነርሱ በመለየቷ ባዘኑበት ወቅት የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠላቸው፤ እርሷን በሥጋ ያዩ ዘንድም ተስፋ ሰጣቸው፡፡
በዚያን ጊዜ ወንጌላዊ ዮሐንስ እስያ በሚባል አገር እያስተማረ በነበረበት በነሐሴ ወር ዐሥራ ስድስተኛ ቀን ተድላ ደስታ ወደአለባት ገነት በመንፈስ ቅዱስ ተነጠቀ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ካለበት ከዕፀ ሕይወት ዘንድ ተቀምጦ አየው፡፡ የንጽሕት እናቱንም ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው፤ እነርሱም ‹‹የንጽሕት እናቱን ሥጋ ታወጪ ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል›› አሏት፡፡ ያን ጊዜም ከዕፀ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ወጣ፡፡ ጌታችንም እንዲህ እያለ አረጋጋት፤ ‹‹የተወደድሽ የወለድሽኝ እናቴ ሆይ! ዘላለማዊ ወደ ሆነ መንግሥተ ሰማያት አሳርግሽ ዘንድ ነዪ፡፡›› ከዚያም በገነት ያሉ ዕፅዋት ሁሉም አዘነበሉ፤ መላእክት፣ የመላእክት አለቆች፣ ጻድቃን ሰማዕታትም እየሰገዱላትና ፈጽሞ እያመሰገኗት አሳረጓት፡፡ ቅዱስ ዳዊትም ‹‹ንግሥት እመቤታችን! ወርቀ ዘቦ ለብሳ ደርባ ደራርባ በቀኝህ ትቀመጣለች›› እያለ በበገና አመሰገናት፡፡
በኪሩቤል ሠረገላ ተቀምጣ ከዐረገች በኃላም በልጆችዋና በፈጣሪዋ ቀኝ በታላቅ ክብር ተቀመጠች፡፡ በዚህን ጊዜ ወንጌላዊ ዮሐንስ ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ ከሰገደላት በኋላ ተመልሶ ወደ ምድር ወረደ፤ ሐዋርያትንም ተሰብስበው ስለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋ ፈጽሞ ሲያዝኑና ሲተክዙ አገኛቸው፡፡ እርሱም እንዳየ፣ እንደሰማና ሥጋዋንም በታላቅ ክብር በምስጋና እንዳሳረጓት ነገራቸው፡፡ ሐዋርያትም ይህን በሰሙ ጊዜ ዮሐንስ እንዳየና እንደሰማ ባለማየታቸውና ባለመስማታቸው እጅግ አዘኑ፡፡ ከዚያም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ ‹‹የፍቅር የአንድነት ልጆች፤ ሰላም ይሁንላችሁ! ስለ እናቴ ማርያም ሥጋ ለምን ታዝናላችሁ፡፡ እነሆ እኔ እርስዋን በሥጋ ላሳያችሁ፤ ልባችሁም ደስ ሊለው ይገባዋል›› ብሏቸው ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡
ሐዋርያትም ለዓመት ከቆዩ በኋላ የነሐሴ ወር በባተ ቀን ዮሐንስ ለሐዋርያቱ እንዲህ አላቸው፤ ‹‹አምላክን የወለደች የእመቤታችንን ሥጋዋን ለማየት የተዘጋጀን አድርጎ ያሳየን ዘንድ ኑ! ይህን ሁለት ሱባዔ በጾም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንለምነው፤ በልጅዋ በወዳጅዋ ቀኝ ተቀምጣ አይተን በእርሷ ደስ እንዲለን፡፡›› ዮሐንስም እንዳላቸው በጾም በጸሎት ሱባዔ ያዙ፤ በነሐሴ ዐሥራ ስድስትም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉንም ሐዋርያት ወደ ሰማይ አወጣቸው፡፡ በታላቅ ክብር በተወደደ ልጇ ቀኝ ተቀምጣ፣ ከሥጋዋ ተዋሕዳ፣ ተነሥታ እመቤታችን ማርያምን አዩዋት፡፡ እጆቿንም ዘርግታ የከበሩ ሐዋርያትን ባረከቻቸው፤ በልባቸውም እጅግ ደስ አላቸው፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በከበረ ሥጋውና ደሙ ላይ ሠራዔ ካህን ሆነ፡፡ እስጢፋኖስም አዘጋጀ፤ ዮሐንስም በመፍራት ቁሙ አለ፡፡ ሁሉም ሐዋርያት በመሰዊያው ዙሪያ ቆሙ፤ በዚያን ጊዜ ከቶ እንደርሱ ሆኖ የማያውቅ ታላቅ ደስታ ሆነ፡፡ ጌታችንም የቅዳሴውን ሥርዓት በፈጸመ ጊዜ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው፡፡
ከዚያም በኪሩቤልና በሱራፌል ሠረገላ ተቀምጣ በምታርግ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ እመቤታችን ማርያምን እንዲህ አላት፡፡ ‹‹በዚች ቀን የሆነ የዕርገትሽን መታሰቢያ በዓለም ውስጥ እንዲሰበኩ ልጆችሽ ሐዋርያትን እዘዣቸው፡፡ መታሰቢያሽን የሚያደርገውን ሁሉ ተጠብቆም በዚች ቀን ቅዱስ ቁርባን የሚቀበለውን ኃጢአቱን እደመስስለታለሁ፡፡ የእሳትን ሥቃይ ከቶ አያያትም፤ መታሰቢያሽን ለሚያደርግ ሁሉ፣ በዚች ቀን ለድኆች በስምሽ ለሚመጸውትም ቸርነቴ ትገናኘዋለች፤ ይህም ሥጋሽ ወደ ሰማይ ያረገበት ነው፡፡›› እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ክብር ይግባውና ጌታችንን እንዲህ አለቸው ‹‹ልጄ ሆይ! እነሆ በዓይኖቻቸውም አዩ፤ በጆሮዎቻቸውም ሰሙ፤ በእጆቻቸው ያዙ፤ ሌሎችም ታላላቅ ድንቆች ሥራዎችን አዩ፡፡›› እመቤታችንም ይህን ስትናገር ጌታችን ሰላምታ ሰጥቷቸው በታላቅ ደስታ ወደ ደብረ ዘይት ተመለሱ፡፡
የክርስቲያን ወገኖች ሆይ! እኛም በፍጹም ደስታ መታሰቢያዋን እናደርግ ዘንድ ይገባናል፡፡ እርሷ ስለ እኛ ወደተወደደ ልጅዋ ሁልጊዜ ትማልዳለችና፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ይምረን ዘንድ ፈቃዱ ይሁንልን! አሜን፡፡
ምንጭ፡-ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ