የእመቤታችን በዓለ ልደት ተከበረ፡፡

ግንቦት 2/2004 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኖአምላክ

በየዓመቱ ግንቦት አንድ ቀን በልዩ መንፈሳዊ ድምቀት የሚከበረው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የልደት በዓል ትናንት በመላው ዓለም በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ተከብሮ ዋለ፡፡

 

በማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማዕከል አስተባባሪነት በማኅበሩ ሕንፃ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ አዳራሽ በተከናወነው የእመቤታችን የልደት በዓል መርሐ ግብር ከስድስት መቶ በላይ የሚሆኑ የማኅበሩ አባላትና ሌሎች ተጋባዥ ምእመናንም ተገኝተዋል፡፡ የእመቤታችንን በዓል ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀውን መልእክት የአዲስ አበባ ማዕከል ሰብሳቢ ዲ/ን አንዱ ዓለም ኀይሉ አቅርበዋል፡፡

“የእመቤታችንን በዓል መንፈሳዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በማክበር ከእመቤታችን በረከተ ረድኤትን ለማግኘት፣ ለመማማር ለመመካከርና አገልግሎታችንም የተቃና እንዲሆን በጸሎት ለማሳሰብ እንዲረዳን ጭምር ነው፡- በዓለ ልደታን እንዲህ ባለ መልኩ ያከበርነው” ሲሉ የገለጹት የአዲስ አበባ ማዕከል ጸሓፊ አቶ ካሳሁን ኀይሌ ናቸው፡፡

 

በጸሎተ ኪዳንና በመዝሙረ ዳዊት በተከፈተው ጉባኤ ላይ ትምህርት፣ የግንቦት ልደታን እንዴት እናክብር? በሚል ምክርና ማኅበሩ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ከአገልግሎት ባልተለዩ  አባላት አማካኝነት የሕይወት ተሞክሮ የቀረበ ሲሆን በዓሉን ምክንያት በማድረግ በእመቤታችን ስም የተዘከረ ጸበል ጸዲቅ ቀርቧል፡፡

 

የማኅበረ ቅዱሳንን ሃያኛ ዓመት ምሥረታና የእመቤታችንን በዓል በጋራ እያከበርን በምንገኝበት በዚህ ወቅት ለአባላት የሚያስተላልፉት መልእክት ምንድር ነው? የሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው አቶ ካሳሁን፡- የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮና መንፈሳዊ ይዘቱን የጠበቀ የበዓል አከባበር እሴታችንን በመጠበቅ ወደፊትም ማዕከሉ ተመሳሳይ መርሐ ግብራትን እንደሚያዘጋጅ ገልጸው፥ ምእመናንም በያሉበት ይህንኑ በጎ ትውፊት እንዲጠብቁ አሳስበዋል፡፡