የኢትዮጵያ ዘመን አቈጣጠር
በዲያቆን ኃይለ ኢየሱስ ቢያ
መስከረም ፮ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም
የዘመን አቈጣጠር ዓመታትን፣ ወራትን፣ ሳምንታትን፣ ዕለታትን፣ ደቂቃን እና ድቁቅ ሰዓታትን በየሥፍራቸው (በየመጠናቸው) የሚገልጽ፤ የሚተነትን፤ የሚለካ የቤተ ክርስቲያን የቍጥር ትምህርት ነው፡፡ እነዚህ ዅሉ ተመርምረው፣ ተመዝነው፣ ተቈጥረው ሲያበቁ ምድብና ቀመር ተሰጥቷቸው የሚገኙበትን ውሳኔና ድንጋጌ የሚያሳውቅ የዘመን አቈጣጠር – ‹ሐሳበ ዘመን› ይባላል፡፡ ዓመታት፣ ወራት፣ ሳምንታት፣ ዕለታትና ሰዓታት የሚለኩት (የሚሠፈሩት፣ የሚቈጠሩት) በሰባቱ መሥፈሪያና በሰባቱ አዕዋዳት ነው፡፡ ሰባቱ መሥፈርታት የሚባሉትም፡- ሳድሲት፣ ኃምሲት፣ ራብዒት፣ ሣልሲት፣ ካልዒት፣ ኬክሮስ እና ዕለት ሲኾኑ ሰባቱ አዕዋዳት ደግሞ፡- ዐውደ ዕለት፣ ዐውደ ወርኅ፣ ዐውደ ዓመት፣ ዐውደ ፀሐይ፣ ዐውደ አበቅቴ፣ ዐውደ ማኅተም እና ዐውደ ቀመር ናቸው፡፡
- ዐውደ ዕለት – ከእሑድ እስከ ቅዳሜ ያሉት ሰባቱ ዕለታት ሲኾኑ፤ አውራኅን (ወራትን) ለማስገኘት በዚህ ሲመላለሱ ይኖራሉ፡፡
- ዐውደ ወርኅ – በፀሐይ ፴ ዕለታት፣ በጨረቃ ፳፱ ወይም ፴ ዕለታት ናቸው፤ ዓመታትን ለማስገኘት በዚህ ሲመላለሱ ይኖራሉ፡፡
- ዐውደ ዓመት – በፀሐይ ቀን አቈጣጠር ፫፻፷፭ ቀን ከ፲፭ ኬክሮስ፤ በጨረቃ አቈጣጠር ፫፻፶፬ ቀን ከ፳፪ ኬክሮስ ነው፡፡ እነዚህ ሦስቱ በዕለት፤ አራቱ ደግሞ በዓመት ይቈጠራሉ፡፡ ዘመናትን ለማስገኘት በዚህ ሲመላለሱ ይኖራሉ፡፡
- ዐውደ ፀሐይ – ፳፰ ዓመት ነው፤ በዚህ ዕለትና ወንጌላዊ ይገናኙበታል፡፡
- ዐውደ አበቅቴ – ፲፱ ዓመት ነው፤ በዚህ ፀሐይና ጨረቃ ይገናኙበታል፡፡
- ዐውደ ማኅተም – ፸፮ ዓመት ነው፤ በዚህ አበቅቴና ወንጌላዊ ይገናኙበታል፡፡
- ዐውደ ቀመር – ፭፻፴፪ ዓመት ነው፤ በዚህ ዕለትና ወንጌላዊ፣ አበቅቴም ይገናኙበታል፡፡
የዘመናት (የጊዜያት) ክፍል እና መጠን
አንድ ዓመት በፀሐይ ፫፻፷፭ ቀን ከ፲፭ ኬክሮስ፤ በጨረቃ ፫፻፶፬ ቀን ከ፳፪ ኬክሮስ ነው፡፡ አንድ ወር በፀሐይ ፴ ዕለታት አሉት፤ በጨረቃ ፳፱ ወይም ፴ ዕለታት አሉት፡፡ አንድ ዕለት ፳፬ ሰዓት፤ አንድ ቀን ፲፪ ሰዓት፤ አንድ ሰዓት ፷ ደቂቃ ነው፡፡ አንድ ደቂቃ ፷ ካልዒት፤ አንድ ካልዒት ፩ ቅጽበት ነው፡፡ ኬክሮስ ማለት የክፍለ ዕለት ሳምንት (የዕለት ፩/፷ ወይም ፩/፳፬ኛ ሰዓት) ነው፡፡ አንድ ዕለት ፳፬ ሰዓት ወይም ፷ ኬክሮስ ነው፡፡
ክፍላተ ዓመት (የዓመት ክፍሎች)
የዓመት ክፍሎች፡- መጸው፣ በጋ፣ ፀደይ እና ክረምት ናቸው፡፡
- ከመስከረም ፳፮ እስከ ታኅሣሥ ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ክፍለ ዓመት መጸው ይባላል፡፡ በዚህ ክፍለ ዓመት ሌሊቱ ረጅም፣ ቀኑ አጭር ነው፡፡
- ከታኅሣሥ ፳፮ እስከ መጋቢት ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ክፍለ ዓመት በጋ ይባላል፡፡ በዚህ ክፍለ ዓመት የቀኑና የሌሊቱ ርዝመት እኩል ነው፡፡
- ከመጋቢት ፳፮ እስከ ሰኔ ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ወቅት ፀደይ ይባላል፡፡ በዚህ ክፍለ ዓመት ቀኑ ይረዝማል፤ ሌሊቱ ያጥራል፡፡
- ከሰኔ ፳፮ እስከ መስከረም ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ክረምት ይባላል፡፡ በዚህ ክፍለ ዓመት የቀኑና የሌሊቱ ርዝመት እኩል ነው፡፡
የዘመናት አከፋፈል በአራቱ ወንጌላውያን እና ዘመን የሚለወጥበት ሰዓት
- ማቴዎስ ዘመኑን ከምሽቱ ፩ ሰዓት ጀምሮ በዓመቱ ከሌሊቱ ፮ ሰዓት ይፈጽማል፡፡
- ማርቆስ ዘመኑን ከሌሊቱ ፯ ሰዓት ጀምሮ በዓመቱ ከጠዋቱ ፲፪ ሰዓት ይፈጽማል፡፡
- ሉቃስ ዘመኑን ከጠዋቱ ፩ ሰዓት ጀምሮ በዓመቱ ከቀኑ ፮ ሰዓት (በቀትር) ይፈጽማል፡፡
- ዮሐንስ ዘመኑን ከቀኑ ፯ ሰዓት ጀምሮ በዓመቱ ከቀትር በኋላ ከምሽቱ ፲፪ ሰዓት ይፈጽማል፡፡
የወራት፣ የሌሊትና የቀን ሥፍረ ሰዓት
- መስከረም – ሌሊቱ ፲፪፤ መዓልቱም (ቀኑ) ፲፪ ሰዓት ነው፡፡
- ጥቅምት – ሌሊቱ ፲፫፤ መዓልቱ ፲፩ ሰዓት ነው፡፡
- ኅዳር – ሌሊቱ ፲፬፤ መዓልቱ ፲ ሰዓት ነው፡፡
- ታኅሣሥ – ሌሊቱ ፲፭፤ መዓልቱ ፱ ሰዓት ነው፡፡
- ጥር – ሌሊቱ ፲፬፤ መዓልቱ ፲ ሰዓት ነው፡፡
- የካቲት – ሌሊቱ ፲፫፤ መዓልቱ ፲፩ ሰዓት ነው፡፡
- መጋቢት – ሌሊቱ ፲፪፤ መዓልቱ ፲፪ ሰዓት ነው፡፡
- ሚያዝያ – ሌሊቱ ፲፩፤ መዓልቱ ፲፫ ሰዓት ነው፡፡
- ግንቦት – ሌሊቱ ፲፤ መዓልቱ ፲፬ ሰዓት ነው፡፡
- ሰኔ – ሌሊቱ ፲፱፤ መዓልቱ ፲፭ ሰዓት ነው፡፡
- ሐምሌ – ሌሊቱ ፲፤ መዓልቱ ፲፬ ሰዓት ነው፡፡
- ነሐሴ – ሌሊቱ ፲፩፤ መዓልቱ ፲፫ ሰዓት ነው፡፡
የበዓላት እና አጽዋማት ኢየዐርግ እና ኢይወርድ (ከፍታ እና ዝቅታ)
- ጾመ ነነዌ ከጥር ፲፯ ቀን በታች፤ ከየካቲት ፳፩ ቀን በላይ አይውልም፡፡
- ዐቢይ ጾም ከየካቲት ፩ ቀን በታች፤ ከመጋቢት ፭ ቀን በላይ አይውልም፡፡
- ደብረ ዘይት ከየካቲት ፳፰ ቀን በታች፤ ከሚያዝያ ፪ ቀን በላይ አይውልም፡፡
- በዓለ ሆሣዕና ከመጋቢት ፲፱ ቀን በታች፤ ከሚያዝያ ፳፫ ቀን በላይ አይውልም፡፡
- በዓለ ስቅለት ከመጋቢት ፳፬ ቀን በታች፤ ከሚያዝያ ፳፰ ቀን በላይ አይውልም፡፡
- በዓለ ትንሣኤ ከመጋቢት ፳፮ ቀን በታች፤ ከሚያዝያ ፴ ቀን በላይ አይውልም፡፡
- ርክበ ካህናት ከሚያዝያ ፳ ቀን በታች፤ ከግንቦት ፳፬ ቀን በላይ አይውልም፡፡
- በዓለ ዕርገት ከግንቦት ፭ ቀን በታች፤ ከሰኔ ፲፱ ቀን በላይ አይውልም፡፡
- ጾመ ሐዋርያት ከግንቦት ፲፮ ቀን በታች፤ ከሰኔ ፳ ቀን በላይ አይውልም፡፡
- ጾመ ድኅነት ከግንቦት ፲፰ ቀን በታች፤ ከሰኔ ፳፪ ቀን በላይ አይውልም፡፡
የተውሳክ አወጣጥ
፩. የዕለት ተውሳክ
የዕለት ተውሳክ በቅዳሜ ይጀምራል፡፡ የቅዳሜ ተውሳክ ፰፤ የእሑድ ተውሳክ ፯፤ የሰኞ ተውሳክ ፮፤ የማክሰኞ ተውሳክ ፭፤ የረቡዕ ተውሳክ ፬፤ የሐሙስ ተውሳክ ፫፤ የዓርብ ተውሳክ ፪ ነው፡፡
፪. የአጽዋማትና የበዓላት ተውሳክ
የነነዌ ተውሳክ አልቦ (ባዶ)፤ የዐቢይ ጾም ተውሳክ ፲፬፤ የደብረ ዘይት ተውሳክ ፩፤ የሆሣዕና ተውሳክ ፪፤ የስቅለት ተውሳክ ፯፤ የትንሣኤ ተውሳክ ፱፤ የርክበ ካህናት ተውሳክ ፫፤ የዕርገት ተውሳክ ፲፰፤ የጰራቅሊጦስ ፳፰፤ የጾመ ሐዋርያት ተውሳክ ፳፱፤ የጾመ ድኅነት ተውሳክ ፩ ነው፡፡
በዓላት እና አጽዋማት የሚውሉባቸው ዕለታት
- ጾመ ነነዌ፣ ዐቢይ ጾም እና ጾመ ሐዋርያት – ሰኞ፡፡
- ደብረ ዘይት፣ ሆሣዕና፣ ትንሣኤ እና ጰራቅሊጦስ – እሑድ፡፡
- ስቅለት – ዓርብ፡፡
- ርክበ ካህናት እና ጾመ ድኅነት – ረቡዕ፡፡
- ዕርገት – ሐሙስ ቀን ይውላል፡፡
መጥቅዕ እና አበቅቴ
መጥቅዕ እና አበቅቴ ከየት መጣ ቢሉ፣
የመጀመሪያው – የፀሐይና የጨረቃ ቀን አቈጣጠር ልዩነት ነው፡፡ አንድ ዓመት በፀሐይ ፫፻፷፭ ቀን ከ፲፭ ኬክሮስ፤ በጨረቃ ፫፻፶፬ ቀን ከ፳፪ ኬክሮስ ነው፡፡ የሁለቱ ልዩነት (፫፻፷፭ – ፫፻፶፬ = ፲፩) አበቅቴ ይባላል፡፡
ሁለተኛው – የቅዱስ ድሜጥሮስ ሱባዔ ውጤት ነው፡፡ ቅዱስ ድሜጥሮስ በዓላትና አጽዋማት የሚውሉበት ቀን በጥንተ ዕለቱ እንዲውል ለማድረግ ይመኝ ነበርና ከሌሊቱ ፳፫ ሱባዔ፤ ከቀኑ ፯ ሱባዔ ገብቷል፡፡ ፳፫×፯ = ፻፷፩ ይኾናል፡፡ ፻፷፩ ለ፴ ሲካፈል ፭ ይደርስና ፲፩ ይተርፋል፤ ይህን ቀሪ አበቅቴ አለው፡፡ ፯ በሰባት ሲባዛ ፵፱ ይኾናል (፯×፯ = ፵፱)፡፡ ፵፱ ለ፴ ሲካፈል (፵፱÷፴) ፩ ደርሶ ፲፱ ይቀራል፤ ይህን ቀሪ መጥቅዕ አለው፡፡
ዓመተ ዓለምን፣ ወንጌላዊን፣ ዕለትን፣ ወንበርን፣ አበቅቴን፣ መጥቅዕን፣ መባጃ ሐመርን፣ አጽዋማትን እና በዓላትን ለይቶ ለማወቅ ሒሳባዊ ሰሌቱ እንዲሚከተለው ነው፤
ዓመተ ዓለምን ለማግኘት ስሌቱ ዓመተ ኵነኔ ሲደመር ዓመተ ምሕረት ሲኾን፣ ውጤቱ ዓመተ ዓለም ይባላል፡፡ ለምሳሌ ፶፭፻ + ፳፻፲ = ፸፭፻፲ (5500 + 2010 = 7510)፤ ፸፭፻፲ (7510) ዓመተ ዓለም ይባላል፡፡
ወንጌላዊን ለማግኘት ስሌቱ ዓመተ ዓለምን ለአራት ማካፈል ነው፡፡ ዓመተ ዓለሙ ለአራት ተካፍሎ ፩ ሲቀር ዘመኑ ማቴዎስ፤ ፪ ሲቀር ማርቆስ፤ ፫ ሲቀር ሉቃስ፤ ያለ ቀሪ ሲካፈል ዮሐንስ ይኾናል፡፡
ዕለቱን (ለምሳሌ መስከረም ፩ ቀንን) ለማግኘት ስሌቱ ዓመተ ዓለም ሲደመር መጠነ ራብዒት (ለአንድ ወንጌላዊ የደረሰው) ሲካፈል ለሰባት ነው፡፡ ዓመተ ዓለም እና መጠነ ራብዒት ተደምሮ ለሰባት ተካፍሎ ፩ ሲቀር ማክሰኞ፤ ፪ ሲቀር ረቡዕ፤ ፫ ሲቀር ሐሙስ፤ ፬ ሲቀር ዓርብ፤ ፭ ሲቀር ቅዳሜ፤ ፮ ሲቀር እሑድ፤ ያለ ቀሪ እኩል ሲካፈል ሰኞ ይኾናል፡፡
ተረፈ ዘመኑን (ወንበሩን) ለማግኘት ዓመተ ዓለም ለሰባት ተካፍሎ የሚገኘው ቀሪ ተረፈ ዘመን (ወንበር) ይባላል፡፡ ከቀሪው ላይ ስለ ተጀመረ ተቈጠረ፤ ስላልተፈጸመ ታተተ (ተቀነሰ) ብሎ አንድ መቀነስ ስሌቱ ሲኾን ቀሪው ወንበር ይባላል፡፡
አበቅቴን ለማግኘት ወንበር ሲባዛ በጥንተ አበቅቴ (፲፩) ሲካፈል ለ፴ ኾኖ ቀሪው አበቅቴ ይባላል፡፡ መጥቅዕን ለማግኘት ወንበር ሲባዛ በጥንተ መጥቅዕ (፲፱) ሲካፈል ለ፴ ኾኖ ቀሪው መጥቅዕ ይባላል፡፡
ከዚህ ላይ አዋጁን (መመሪያውን) እንመልከት፤ አዋጁም መጥቅዕ ከ፲፬ በላይ ከኾነ መጥቅዕ በመስከረም ይውላል፤ የመስከረም ማግስት (ሳኒታ) የካቲት ይኾናል፡፡ ፲፬ ራሱ መጥቅዕ መኾን አይችልም፡፡ መጥቅዕ ከ፲፬ በታች ከኾነ በጥቅምት ይውላል፤ የጥቅምት ማግስት (ሳኒታ) ጥር ነው፡፡ መጥቅዕ ሲደመር አበቅቴ ውጤቱ ዅልጊዜ ፴ ነው፡፡ መጥቅዕ አልቦ (ዜሮ) ሲኾን መስከረም ፴ የዋለበት የቀኑ ተውሳክ መባጃ ሐመር ይኾናል፡፡
መባጃ ሐመርን ለማግኘት የዕለት ተውሳክ ሲደመር መጥቅዕ ሲካፈል ለሠላሳ ነው (የዕለት ተውሳክ+መጥቅዕ÷፴ = መባጃ ሐመር)፡፡ ቍጥሩ ለሠላሳ መካፈል ካልቻለ እንዳለ ይወሰዳል፡፡
የአጽዋማት እና የበዓላት ተውሳክ አወጣጥ
ጾምን ለማግኘት ስሌቱ መባጃ ሐመር ሲደመር የጾም ተውሳክ ሲካፈል ለሠላሳ ነው (መባጃ ሐመር+የጾም ተውሳክ÷፴ = ጾም)፡፡ ቍጥሩ ለሠላሳ መካፈል ካልቻለ እንዳለ ይወሰዳል፡፡ በዓላትን ለማግኘት ስሌቱ መባጃ ሐመር ሲደመር የበዓል ተውሳክ ሲካፈል ለሠላሳ ነው (መባጃ ሐመር+የበዓል ተውሳክ÷፴ = በዓል)፡፡ ቍጥሩ ለሠላሳ መካፈል ካልቻለ እንዳለ ይወሰዳል፡፡ በዚህ ሒሳብ መሠረት በየዓመቱ የሚመላለሱ በዓላት እና አጽዋማት የሚዉሉበትን ቀን ማወቅ ይቻላል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡