መልእከተ ቅዱስ ፓትርያርክ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
-ብፁዕ አቤነ ያሬድ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ
-የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
-ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና
የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
-ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣
– በአጠቃላይ በዚህ ዓመታዊ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የተገኛችሁ ሁሉ፤
በየተሰማራንበት ሁሉ እግዚአብሔር እየረዳን መንፈሳዊና ማኀበራዊ ሥራችንን እየተወጣን ከቆየንበት ሀገረ ስብከት በሰላም አምጥቶና አንድ ላይ አሰባስቦ ስለ ሃይማታችንና ስለሀገራችን ለመወያየት የሰበሰብን እግዚአብሔር አምላክችን ስሙ የተመሰገነ ይሁን፡፡
‹‹ትግሁ ወጸልዩ ከመ ኢትባኡ ውስተ መንሱት፤ወደፈታና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ›› (ማቴ.፳፮፥፵፩)፡፡ ፈጣሬ ፍጥረታት እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚወድ ብቻ ሳይሆን ከሕዝቡ መለየት የማይፈልግ አምላክ ነው፤ የእግዚአብሔር መኖሪያ በሰው እጅ በተሠራው ቁሳዊ ነገር ሳይሆን እርሱ እራሱ በሠራው በሰው ልቡና ስለሆነ፣ ከሰው ጋር መገናኘት የሚፈልገው በዋናነት በዚሁ ስፍራ እንደሆነ እርሱ እራሱ ነግሮናል፤ ታዲያ እግዚአብሔር ከሰው ልቡና መለየት እንደማይፈልግ ሁሉ ሰውም ምንም ደካማ ቢሆንም ከፈጣሪው ከእግዚአብሔር መለየት አይፈልግም፡፡ ይህም የጋራ ፍላጎት ሊከናወን የሚችለው በእምነትና በጸሎት ነው፡፡ ይህ ግንኙነት የደጋፊና ተደጋፊ ዓላማ ያለው ግንኙነት ነው፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን በዚህ መልኩ በጸሎት ስንቀርብ በቀላሉ እንደምናገኘው እናምናለን፤ ‹‹ወሀቦለልዑል ጸሎተከ ትጼውዓኒ በዕለተ ምንዳቤከ አድኀነከ ወተአኵተኒ፤ ጸሎትህን ለልዑል እግዚአብሔር አቅርብ፤ በመከራህ ቀን ትጠራኛለህ፤ እኔም አድንሀለሁ፤ አንተም ታመሰግነኛለህ›› ሲል ቃል ገብቶልናል፡፡
ይህ ወቅት በመላ ክፍለ ዓለም ተሰራጭቶ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ በሽታ ፍጥረተ ሰብእን በጠቅላላ ከባድ ሥጋት ላይ የጣለበት ወቅት ነው፡፡ ‹‹ በእንቅርት ላይ….›› እንደሚባለው ሀገራችን በሌሎች ውስብስብ ነገሮች በተወጠረችበት ወቅት ይህ ዓይነቱ መድኃኒት የለሽ በሽታ መከሠቱ በሀገራችን ላይ ሥጋት እንዲበዛ አድርጓል፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
ይህ ወቅት ለሀገራችንም ለቤተ ክርስቲያኖችንም ለሕዝባችንም ከባድ የፈተና ወቅት ነው፡ በዚህ ጊዜ እንደ ትናንቱ የመሰለ አካሔድና አስተሳሰብ ጭራሽ የሚስኬድ አይሆንም፤ እኛ ሊቃነ ጳጳሳት የሕዝብ እግዚአብሔር እረኞች ሆነን እዚህ ላይ የተሰበሰበውን ሕዝቡን ለሁለንተናዊ ሕይወቱ ከፈተና ለመጠበቅ መሆኑን በውል የምንገነዘበው ነው፡፡
ይህ ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ በብዙ መልኩ እየተፈተነ ነው፤ ሕዝቡ በሰላም እጦት የኀሊና ጭንቀት ላይ ነው፤ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በቀጣዮቹ ዓመታት በእጅጉ ሊጎዳ እንደሚችል የበሽታው ተጽዕኖ ምልክት እያሳየ ነው፡፡ የተከሠተው በሽታ መቼ ሊወገድ እንደሚችል የሚታወቅ ነገር የለም፤ ስለሆነም በዚህ ሁሉ ፈተና ተጎጂው ማን ነው? ሲባል እኛ እረኛ የሆንለት ሰፊው ሕዝብ በተለይም በዝቅተኛ ኑሮ የሚኖር ድሀው ሕዝባችን ነው፡፡
ይህ ሕዝብ እየታዩ ባሉት ችግሮች በመከራ ቢለበለብ በእግዚአብሔር ዘንድ ያስጠይቀናል፤ ሕዝቡም ይታዘበናል፤ ይህም እንዳይሆን በተቻለ አቅም በጸሎትም፣ በትምህርትም፣ በምክርም፣ በማስታረቅም ሰፊ የማግባባትና የሕዝብ አድን ሥራ መሥራት አለብን፡፡ አሁን ያለው ጥያቄ ሀገርንና ሕዝብን ከፈተና የመታደግ ጥያቄ ነው፤ ይህን ፈተና መሸጋገር የምንችለው በአንድነት ሆነን ስንቆም ብቻ ነው፡፡ አንድነትን ለማምጣት ደግሞ የማግባባት ሥራ የግድ መሥራት አለብን፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ይህ ጉባዔ በጥልቀትና በአጽንዖት ተወያይቶ ወደ ተጨባጭ ሥራ እንዲገባ ያስፈልጋል፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
ሕዝባችን በውስጣዊና አካባቢያዊ የአስተሳሰብ ልዮነት ምክንያት ብዙ ውጣ ውረድ ባለበት ወቅት ተጨማሪ ሸክም ሆኖ የመጣብንን የኮሮና በሽታም በአጭር ታጥቀን ሕዝቡን በማስተማር፣ በጸሎትም በመትጋት ክፉውን ቀን በሰላም እንድናሸጋግረው ጠንክረን መሥራት አለብን፡፡ እስከ አሁን ድረስ ቤተ ክርስቲያናችን፣ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት፣ መንግሥትና ሕዝብ፣ እንደዚሁም የተለያዩ የሚዲያ አውታሮች በጋራ ሆነው በሠሩት ሥራ ቢያንስ የወረርሽኙ በሽታ የከፋ አደጋ እንዳያደርስ በመከላከላቸው በዚህ አጋጣሚ ሳናመሰግን አናልፍም፡፡ ለወደፊቱም በዚሁ እንዲቀጥል በጋራ እየተባበሩ መሥራቱን ማጠናከር ይገባል፡፡
በመጨረሻም
ሁላችንም እንደምናየውና እንደምንገነዘበው በሀገራችን እየተከሠቱ ያሉት የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች ሁሉ መንግሥትና የፖለቲካ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እግዚአብሔርና ታሪክ የጣለባችሁን አደራ በላቀ አስተውሎት ነገሩን በማጤን ሀገርንና ሕዝብን በሰላም፣ በጤና እና በአንድነት የማሻገር ከፍተኛ ኃላፊነት በእጃችሁ እንዳለ አውቃችሁ ይህንን ሕዝብና ሀገር ወደ ተሻለ አስተማማኝ ሰላም፣ ጤንነትና ዕድገት በፍቅርና በአንድነት ሆናችሁ እንድታሸጋግሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አደራ ትላችኋለች፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምን ጊዜም ከሕዝቡ ጎን መሆኑን እየገለጽን የሁለት ሺ አሥራ ሁለት ዓመተ ምሕረት የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ በዛሬው ዕለት መከፈቱን እናበሥራለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ግንቦት ፭ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ