የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዐዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማእከል
ግንቦት ፳፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት፣ አሐቲ፣ ከኹሉ በላይ የኾነች፣ በክርስቶስ ደም የተመሠረተች፣ በቅዱሳን ነቢያት ትንቢት የጸናች፣ በቅዱሳን ሐዋርያት ስብከት የታነፀች፣ በሊቃውንት አስተምህሮ የጸናች፣ በምእመናን ኅብረት የተዋበች ንጽሕት ማኅደረ ሃይማኖት ናት፡፡
የዚህችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ምእመናን ይረዱ ዘንድ ልዩ ልዩ ዘዴዎችን መጠቀም ይገባል፡፡ ከእነዚህ ዘዴዎች አንዱ ከሰሞኑ በማኅበረ ቅዱሳን አማካይነት በአዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማዕከል ለዕይታ ቀርቦ የሰነበተው ዓይነት ዐውደ ርእይ አንዱ ነው፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን አምስተኛውን ዐውደ ርእይ ለምእመናን ሊያቀርብ የነበረው ከመጋቢት ፲፭-፳፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም የነበረ ቢኾንም ዳሩ ግን ዐውደ ርእዩ በሰዓቱ ግልጽ ባልነበረ ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ ታግዶ ከቆየ በኋላ እግዚአብሔር ሥራውን የሚሠራበት ጊዜ ሲደርስ እነሆ ከግንቦት ፲፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ጀምሮ በዐዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማዕከል ለተመልካቾቹ ይፋ ኾነ፡፡
በዚህ ዐውደ ርእይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሠረተ እምነት፣ ዶግማ፣ ቀኖና እና ትውፊት በሰፊው ቀርቦ በምእመናን ሲታይ ሰንብቷል፡፡ በተጨማሪም በአንድነት ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገልና የተቸገሩትን ለመርዳት የጎላ ድርሻ ያላቸው የጽዋ፣ የበጎ አድራጎትና የጉዞ ማኅበራት አገልግሎትም ተዳስሷል፡፡
ሊቃውንቱና ደቀ መዛምርቱ በዐውደ ርእዩ የሚሳተፉትን ጎብኝዎች ለማስደሰት የአገር ርቀት ሳይገድባቸው፣ መንገድ ሳያደክማቸው ከየመኖሪያ ቦታቸው በመምጣት በዐዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማዕከል ለሳምንት ያህል ቆይተዋል፡፡
ዐውደ ርእዩ በአራት ዐበይት አርእስት ማለትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሠረተ እምነት፣ የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልዕኮ፣ የቤተ ክርስቲያን ተጋድሎ እና ምን እናድርግ በሚሉ የተከፋፈለ ሲኾን በእያንዳንዱ ትዕይንት ሥርም በርካታ አርእስት ተካተውበታል፡፡ እያንዳንዳቸው የያዟቸው ጭብጦችም የሚከተሉት ናቸው፤
ትዕይንት አንድ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሠረተ እምነት
ይህ ትዕይንት ሀልዎተ እግዚአብሔር፣ ነገረ ድኅነት፣ ነገረ ማርያም፣ ነገረ ቅዱሳን እና ነገረ ቤተ ክርስቲያን የሚዳሰሱበት ክፍል ሲኾን፣ በውስጡም ሀልዎተ እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር አምላክ በጊዜና በቦታ የማይወሰን፣ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው፣ የፍጥረታት ኹሉ አስገኚና እርሱ በገለጠው መጠን ብቻ የሚታወቅ እንጂ ባሕርዩ ተመርምሮ ሊደረስበት እንደማይቻል እንደዚሁም መልዕልተ ኵሉ (የኹሉ የበላይ) መኾኑን ያስረዳል፡፡
እግዚአብሔር ሲባልም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ማለት እንደኾነ፤ እንደዚሁም እግዚአብሔር አምላክ በሥነ ፍጥረቱ፣ በአምላካዊ መግቦቱ፣ በሕሊና፣ በቅዱሳት መጻሕፍት፣ በዓለም ላይ በሚፈጸሙ ድርጊቶች ምስክርነት፣ ሥጋን በመልበስራሱን ለእኛ እንደገለጠልን በዚህ ትዕይንት ተብራርቷል፡፡
በተጨማሪም ሃይማኖት ማለት እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ልጅ የገለጠበት መንገድ ስለመኾኑና ስለ አብርሃም እግዚአብሔርን ፈልጎ ማግኘት፣ በተጨማሪም በዓለም ላይ ብዙ ሃይማኖቶች ለመኖራቸው ምክንያቱ የሰይጣን ክፉ ሥራና የሰው ልጅ የመረዳት ዓቅም መለያየት ስለመኾኑ ተብራርቶበታል፡፡
ነገረ ድኅነት ደግሞ በአዳምና በሔዋን ምክንያት የዘለዓለም ሞት ተፈርዶበት የነበረው የሰው ልጅ ከሦስቱ አካላት አንዱ በኾነው በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማተ መስቀልና ሞት የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ መቻሉን በማስረዳት እመቤታችን የመልአኩን ብሥራት ከሰማችበት ጊዜ ጀምሮ የጌታችን ፅንሰት፣ ልደት፣ስደት፣ ዕድገት፣ ጥምቀት፣ ትምህርት፣ ተአምራት፣ ሕማማት፣ ሞት፣ ትንሣኤ፣ ዕርገትና ዳግም ምጽአት የነገረ ድኅነት መሠረቶች መኾናቸውን ይተነትናል፡፡
እንደዚሁም እምነት፣ ምግባር እና ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን መፈጸም የሰው ልጆች ለመዳን ሊያሟሏቸው የሚገቡ ቅድመ ኹኔታዎች መኾናቸው በዚህ ርእስ ሥር ተካቷል፡፡
ነገረ ማርያምም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ እናት እንደመኾኗ ከመፅነሷ በፊት፣ በፅንሷ ጊዜም ኾነ ከፀነሰች በኋላ ዘለዓለም ድንግል ስለመኾኗ እንደዚሁም በእግዚአብሔር ፊት ቆማ ለእኛ እንደምታማልድ ያስረዳል፡፡
ነገረ ቅዱሳን ደግሞ ሰማያውያን መላእክትን ጨምሮ ያላቸውን ኹሉ ትተውእግዚአብሔርን ብቻ የተከተሉ፣ መከራ መስቀሉን ተሸክመው ሕይዎታቸውን በሙሉበ ተጋድሎ ያሳለፉ፣ በፍጹም ልቡናቸው ጸንተው እስከ መጨረሻው ድረስ እግዚአብሔርን የተከተሉቅዱሳን አባቶች እና እናቶች ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው ጸጋና ሥልጣን በምድርም በሰማይም እንደሚያማልዱ ያስረዳል፡፡
በነገረ ቤተ ክርስቲያን ሥር ደግሞ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስአካል፣ የምእመናን ኅብረት፣ የሰው ልጆችና የመላእክት፣ በዓለመ ሥጋና በዓለመ ነፍስ ያሉ እንደዚሁም የሥውራንም የገሃዳውያንም (በግልጽ የሚታዩ)ምእመናን አንድነትመኾኗ፣ ይህቺ ቤተ ክርስቲያን በተጋድሎ ብትኖርም ነገር ግን ድል አድራጊ፤ በባሕርዩአም ቅድስት፣ አሐቲ (አንዲት)፣ ሐዋርያዊት፣ ኵላዊት እንደኾነች ተተንትኖበታል፡፡
ትዕይንት ሁለት፡- የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮ
በዚህ ትዕይንት የሐዋርያነትና የሐዋርያዊ አገልግሎት ትርጕም፣ ዓላማና አመሠራረትን ጨምሮ ስብከተ ወንጌል አንዴት እንደ ተስፋፋና እስከ ዛሬ ድረስ በቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሱ ፈተናዎችና መልካም አጋጣሚዎች የተካተቱበት ልዩ ልዩ መረጃና ትምህርት ቀርቦበታል፡፡
የሐዋርያዊ አገልግሎት መጀመርና መስፋፋት በኢትዮጵያ በሚለው የዚህ ትዕይንት ንዑስ ርእስ ሥር ከ፩ኛው እስከ ፯ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ የነበረው ሐዋርያዊ አገልግሎት ተዳሶበታል፡፡ የአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን፣ የቅዱሳን ነገሥታት አብርሀ እና አጽብሀ፣ የዘጠኙ ቅዱሳን፣ የዐፄ ካሌብና የቅዱስ ያሬድ ሐዋርያዊ አገልግሎት ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት ያደረገው አስተዋፅዖ በርእሱ የተገለጡ የታሪክ ክፍሎች ናቸው፡፡
ሁለተኛው ንዑስ ርእስ ደግሞ ከ፰ኛው እስከ ፲ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ በዮዲት ጉዲት ምክንያት ቅዱሳት መጻሕፍትና አብያተ ክርስቲያናት በመቃጠላቸው፣ ሊቃውንቱና ምእመናኑ በመገደላቸውና በመሰደዳቸው በቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ ጉዳት እንደ ደረሰ ያስረዳል፡፡
በሦስተኛ ደረጃ በዮዲት ጉዲት ዘመን በደረሰው በደል ቁጭት ያደረባቸው አባቶች በመነሣታቸው ምክንያት ከዐሥራ ፲፩ኛው እስከ ፲፮ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረውን የሐዋርያዊ ተልዕኮ ትንሣኤ በመግለጽ ለዚህም የአራቱ ቅዱሳን ነገሥታት (ይምርሃነ ክርስቶስ፣ ሐርቤ/ገብረ ማርያም፣ ላሊበላና ነአኵቶ ለአብ) መነሣት፤ የሐይቅ እስጢፋኖስ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ገዳም መመሥረትና እንደ አቡነ ተክል ሃይማኖት ያሉ አባቶች፣ እንደዚሁም በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብና በዘመኑ የነበሩ አበው የስብከተ ወንጌል አገልግሎት፤ በተጨማሪም እንደ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ያሉ ቅዱሳን መጻሕፍትን በማዘጋጀት ያበረከቱትን ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይገልጻል፡፡
በትዕይንት ሁለት በአራተኛ ደረጃ የተቀመጠው ነጥብም ከ፲፯ኛው እስከ ፲፰ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ በነበረው ጊዜ በግራኝ አሕመድ ወረራ ምክንያት ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናትና ቅዱሳት መጻሕፍት በመቃጠላቸው፣ ሊቃውንቱና ምእመናኑ በግፍ በመጨፍጨፋቸው የተነሣ በሐዋርያዊ አገልግሎቱ ላይ የከፋ ጉዳት መድረሱን ይገልጻል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ በዚያ ዘመን ከባዕድ አገር የመጡ የሁለት አካል፣ ሁለት ባሕርይ አማኞች ተፅዕኖ ቢበረታም ተከራክረው መርታት የሚችሉና ለሃይማኖታቸው ሲሉ አንገታቸውን የሚሰጡ አባቶችና እናቶች የተገኙበት ወቅት እንደነበረም ተጠቅሷል፡፡ በዘመነ መሣፍንት በአገራችን ተስፋፍቶ የነበረውን የሁለት አካል ሁለት ባሕርይ አስተሳሰብ ተከትሎ በተፈጠረው የጸጋና የቅብዓት ትምህርት የተከሠተዉን ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት መደረጉም ተገልጿል፡፡
በዚሁ ትዕይንት በአምስተኛ ደረጃ የተቀመጠው ነጥብም ከ ፲፱ኛው እስከ ፳ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ የነበረውን ሐዋርያዊ አገልግሎት የሚያስቃኝ ሲኾን፣ በውስጡም በዘመኑ መጽሐፍ ቅዱስ ከግእዝ ወደ አማርኛ መተርጐሙ፣ በግዳጅ ተይዘው ወደ ሌላ ሃይማኖት ሔደው የነበሩ ምእመናን ወደ ክርስትና መመለሳቸው፣ እንደዚሁም የነመምህር አካለ ወልድ እና መልአከ ሰላም አድማሱ መነሣት ለቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልዕኮ መፋጠን መልካም አጋጣሚ እንደ ነበረ ያስረዳል፡፡
በተጨማሪም ቅዱስ ሲኖዶስ መቋቋሙ፣ የካህናት ማሠልጠኛዎችና መንፈሳውያን ኰሌጆች መመሥረታቸው፣ የሰበካ ጉባኤ መዋቅር መዘርጋቱ፣ ወጣቶች በሰንበት ትምህርት ቤቶችና በማኅበራት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው፣ የምእመናን መንፈሳዊ ተሳትፎ መጨመሩ፣ በውጭዎቹ ክፍላተ ዓለም አብያተ ክርስቲያናት መታነፀቸው እንደዚሁም ቤተ ክርስቲያናችን መገናኛ ብዙኃንና በአፍ መፍቻ ቋንቋ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት መስጠት መጀመሯ በተለይ ፳ኛውን መቶ ክፍለ ዘመን ለሐዋርያዊ ተልዕኮ የተመቸ እንዲኾን ማድረጋቸው ተብራርቶበታል፡፡
በትዕይንት ሁለት የመጨረሻው ርእስ ላይ ደግሞ በአሁኑ ሰዓት የቴሌቭዥንና የሌሎችም መገናኛ ዘዴዎች ሥርጭት አለመኖር፣ በልዩ ቋንቋዎች የሚያስተምሩ ሰባክያንና ካህናት እጥረት እንደዚሁም በየቋንቋው የቅዱሳት መጻሕፍት በበቂ ኹኔታ አለመታተም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት ውሱንነት መገለጫዎች መኾናቸው ተጠቅሷል፡፡
ትዕይንት ሦስት፡- የቤተ ክርስቲያን ተጋድሎ
ይህ ትዕይንት ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ለማስፋፋት ያሳለፈችውን ተጋድሎ፣ የመናፍቃንን ተፅዕኖና የሰማዕታትን ታሪክ፣ የተዋሕዶ ሃይማኖትን አስተምህሮ ለማስጠበቅ የተደረጉ ልዩ ልዩ ዓለም ዓቀፍና አገር ዓቀፍ ጉባኤያትን በዝርዝር የያዘ ሲኾን፣ በኃይል ሃይማኖቱን ለማጥፋት ይተጉ በነበሩ አካላት ምክንያት ቤተ ክርስቲያን ስላደረገችው ተጋድሎ፣ ስለ ቅዱስ እስጢፋኖስ ሰማዕትነትና በዘመነ ሰማዕታት በክርስቲያኖች ላይ ስለደረሰው መከራ፣ እንደዚሁም በርካታ ክርስቲያኖች በሰማዕትነት ስለማለፋቸው፣ በተጨማሪም ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ተነሥቶ ክርስቲያኖች ዕረፍት ስለማግኘታቸው የሚያትት ዐሳብ ይዟል፡፡
ይህ የትዕይንት ክፍል በአገራችን በኢትዮጵያም እንደ ዮዲት ጉዲት፣ ግራኝ አሕመድ፣ ዐፄ ሱስንዮስ፣ ፋሽስት ጣልያን፣ ያሉ ጠላቶች በቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሱት ጉዳት ተጠቅሷል፡፡ ቀጥሎም የዘመናችን ሰማዕታት በሚል ንዑስ ርእስ ሃይማኖታችንን አንክድም፣ ባዕድ አናመልክም ያሉ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም በጂማ ሀገረ ስብከት በበሻሻ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን፤ በቅርቡ በ፳፻፯ ዓ.ም ደግሞ በሊብያ በረሃና በሜዴትራንያን ባሕር ዳርቻ በግፍ የተገደሉ የግብፅ፣ የኢትዮጵያና የሌሎችም አብያተ ክርስቲያናት ሰማዕታትን ይዘክራል፡፡
በቃልም በጽሑፍም በሚበተኑ የሐሰት ትምህርቶች ምክንያት ቤተ ክርስቲያን የፈጸመችውን ተጋድሎ በማውሳት በዚህ የተነሣም ልዩ ልዩ ጉባኤያት መደረጋቸውን ይዘረዝራል፡፡ በዚህ መሠረት ከአይሁድ ወደ ክርስትና ሃይማኖት በመጡትና በቀደሙ ክርስቲያኖች መካከል የልዩነት ትምህርት በመከሠቱ ቅዱሳን ሐዋርያት በ፶ ዓ.ም በኢየሩሳሌም ጉባኤ ማድረጋቸውንና ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ እንደ ተመሠርተ ይገልጻል፡፡
በማያያዝም ሦስቱን ዓለም ዓቀፍ ጉባኤያትን (ጉባኤ ኒቅያ፣ ጉባኤ ቍስጥንጥንያ እና ጉባኤ ኤፌሶን) በማንሣት ውሳኔዎቻቸውን አስቀምጧል፤ ይኸውም፡- በ፫፳፭ ዓ.ም ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት አርዮስን ለማውገዝ በኒቅያ ባደረጉት ጉባኤ ጸሎተ ሃይማኖትን (መሠረተ እምነት) ማርቀቃቸውን፤ በ፫፹፩ ዓ.ም ፻፶ው ሊቃውንት መቅዶንዮስን ለማውገዝ በቍስጥንጥንያ ባደረጉት ጉባኤ ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ እግዚእ ወማኅየዊ ዘሠረጸ እምአብ፤ ጌታ፣ ማኅየዊ በሚኾን ከአብ በሠረጸ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን የሚለው ሐረግ በጸሎተ ሃይማኖት መካከተቱን፤ በ፬፴፩ ዓ.ም ደግሞ ፪፻ ሊቃውንት ንስጥሮስን አውግዘው በአንዲት የተዋሕዶ ሃይማኖት የሚያጸና ትምህርት ማስተማራቸውን ያትታል፡፡
በተጨማሪም በአገራችን በኢትዮጵያ በሃይማኖት ምክንያት በዐሥራ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሰንበትን አከባበር አስመልክቶ በቤተ ኤዎስጣቴዎስና በቤተ ተክለ ሃይማኖት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት በ፲፬፻፶ ዓ.ም በደብረ ምጥማቅ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ አማካኝነት ጉባኤ ተደርጎ ሁለቱም ሰንበታት እኩል ይከበሩ የሚል ውሳኔ ስለመተላለፉ፤ ነሐሴ ፲፫ ቀን ፲፰፻፵፮ ዓ.ም በጎንደር ክፍለ ሀገር በደብረ ታቦር ከተማ አምባጫራ በተባለ ቦታ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አባቶች ከቅባትና ከጸጋዎች ጋር የሃይማኖት ጉባኤ አድርገው ጸጋና ቅባቶች ስለመረታታቸው፤ የቅባትና የጸጋ ትምህርት ፈጽሞ ባለመጥፋቱ ግንቦት ፳፩ ቀን ፲፰፻፸፭ ዓ.ም በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት በቦሩ ሜዳ በድጋሜ ከቅባትና ከጸጋዎች ጋር የሃይማኖት ጉባኤ ተደርጎ ቅባትና ጸጋ ተረተው የተዋሕዶ ሃይማኖት ስለመጽናቷ ይገልጻል፡፡
በመጨረሻም የመናፍቃን ሰርጎ ገብነትና የተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻዎች የዘመናችን የቤተ ክርስቲያን ፈተናዎች መኾናቸው በዚህ ትዕይንት ከማስረጃ ጋር ቀርቧል፡፡
ትዕይንት አራት፡- ምን እናድርግ?
ይህ ትዕይንት ደግሞ ምእመናን በዐውደ ርእዩ ከተመለከቷቸውና ከሰሟቸው እውነታዎች በመነሣት የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ከመጠበቅና ድርሻቸውን ከማወቅ አኳያ ልዩ ልዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ወደፊት ምን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የሚያስረዱ መረጃዎችን አካቷል፡፡
የመጀመሪያው ነጥብ ሐዋርያዊ ተልዕኮን የተመለከተ ሲኾን በርእሱም በ፲፬ አህጉረ ስብከት፣ በ፯፻፳ አጥቢያዎች በተደረገ ጥናት ፫፵፮ አብያተ ክርስቲያናት መዘጋታቸው፣ ፪፻፺፮ቱ አገልጋይ ካህናት እንደሌሉባቸው፣ ፻፷፰ቱ ደግሞ በዓመት/በወር አንድ ጊዜ ብቻ ቅዳሴ የሚቀደስባቸው እንደኾኑ ያስረዳል፡፡
በተያያዘ መረጃ ከ፲፱፻፹፬-፳፻ ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ ሰባት ሚልየን ሰባት መቶ ሰባ ስድስት ሺሕ ሁለት ሃያ ስድስት ምእመናን ወደ ሌሎች ቤተ እምነቶች መወሰዳቸው፣ እንደዚሁም በአዲስ አበባ እና በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያልተመጣጠነ የአገልጋዮች ሥርጭት መኖሩ በዚህ ርእስ ሥር ተገልጿል፡፡
በትዕይንት አራት ሌላው ነጥብ የመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም ንጽጽር ሲኾን በንጽጽሩም የግብፅ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፻፴፬ የመካነ ድር፣ ፲፩ የቴሌቭዥን እና ፲ የሬድዮ ሥርጭት ሲኖራት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግን ፲፪ የመካነ ድር፣ ፪ የሬድዮ፣ እና ፩ የቴሌቭዥን ሥርጭት ብቻ እንዳላት ተጠቅሷል፡፡
ሁለተኛው የትዕይንት አራት ጭብጥ ደግሞ ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች በመተዳደሪያ ዕጦት፣ በድርቅ፣ በመዘረፍ፣ በበሽታ፣ ወዘተ የመሰሉ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ያስረዳል፡፡
በዚህ ትዕይንት ሦስተኛው ነጥብ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ያልተቋቋሙባቸው አጥቢያዎች መኖርና ያሉትም በቂ አለመኾናቸው፣ የሰባክያነ ወንጌል እጥረትና ግቢ ጉባኤያት ያልተመሠረቱባቸው የትምህርት ተቋማት መኖራቸው ቤተ ክርስቲያን ካጋጠሟት ችግሮች መካከል እንደሚጠቀሱ ይናገራል፡፡
በአራተኛ ደረጃ የተቀመጠው ነጥብ እንደሚያስረዳው የንስሐ አባትና የንስሐ ልጆች ግንኙነት መላላት፣ የምእመናንን መንፈሳዊ የእርስበርስ ግንኙነት (ፍቅር) መቀነስ እንደዚሁም ችግሩ እኔን አይመለከተኝም ብለው የሚያስቡ ምእመናን መበራከት ከቤተሰብና ከማኅበራዊ ኑሮ አኳያ ቤተ ክርስቲያን ያጋጠሟት ችግሮች ናቸው፡፡
በአምስተኛ ደረጃ ከተቀመጠው ነጥብ እንደምንገነዘበው ደግሞ ውጤት ተኮር ዕርዳታ የመስጠት ችግር፣ በልዩ ልዩ ሱስና በአእምሮ ሕመም የተጠቁ ምእመናንን ማገዝ አለመቻሉ፣ ውስን በኾኑ የልማት ሥራዎች ላይ ማተኮር ቤተ ክርስቲያን በማኅበራዊ አገልግሎትና በልማት የጋጠሟት ችግሮች ናቸው፡፡
እነዚህን ከላይ የተዘረዘሩትንና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ በጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ በማኅበረ ቅዱሳን፣ በጽርሐ ጽዮን እና በደጆችሽ አይዘጉ ዓይነት ማኅበራት በስብከተ ወንጌልና በጥምቀት አገልግሎት፣ በሥልጠና፣ እንደዚሁም በሌላ ማኅበራዊና ልማታዊ እንቅስቃሴእየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ቢኾንም ነገር ግን ይህ ብቻ በቂ ስላልኾነ ኹሉም የድርሻውን ቢወጣ የተሻለ ሥራ መሥራትና ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ይጠቁማል፡፡
ይህ ኹሉ ችግር በዚህ ከቀጠለ ቤተ ክርስቲያን ወደፊት በሚሊየን የሚቈጠሩ ምእመናንን፣ አገልጋይ ካህናትን፣ አርአያ የሚኾኑ ገዳማውያን መነኰሳትን ማጣት፤ በቤተሰብ ደረጃም ፍቅር የሌላቸውና ተስፋ የሌላቸው ወጣቶች እንዲበዙ ያደርጋል፡፡
በአጠቃላይ ከላይ የተጠቀሱ ችግሮች በዚሁ ከቀጠሉ ቤተ ክርስቲያን በምጣኔ ሀብትም፣ በማኅበራዊ አገልግሎትና በሌሎችም ዘርፎች ዓቅም የሌላትና ተሰሚነት ያጣች ትኾናለች የሚለው ዐሳብ በትዕይንቱ የተገለጸ ሥጋት ነው፡፡
ከዚህ ቀጥሎ በሥዕል መልክ የተቀናበረው መልእክት እርስዎ የትኛው ነዎት? ያልተረዳ? ያንተ/ያንቺ ድርሻ ነው የሚል? ተወቃቃሽ? ሳይመረምር የሚከተል? ማሰብ ብቻ ሥራ የሚመስለው? ተስፋ የቈረጠ? አልሰማም፤ አላይም፤ አልናገርም የሚል? የሚያወራ፣ የሚተች፣ ግን የማይሠራ? ሲል ይጠይቃል፡፡ የትዕይንቱ ማጠቃለያም ምን እናድርግ? በሚል ርእስ አራት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፤
፩. የክርስቶስ አካል በኾነችው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሕያው አካል እንኹን፤
፪. ቤተ ክርስቲያንን በመሰለን ብቻ ሳይኾን በኾነችው እንወቃት፤ እንረዳትም፤
፫. ስለ ቤተ ክርስቲያን ያገባኛል፤ ይመለከተኛል ብለን እንሥራ፤
፬. ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የኾነውና የማዳን ተግባሩን ኹሉ የፈጸመው ለሰው ልጅ ነው፤
ሰው! ሰው! ሰው!
ኑ፤ አብረን እንሥራ፤ ለውጥም እናመጣለን የሚለው ኃይለ ቃልም እንደማንቂያ ደወል የተቀመጠ መልእክት ነው፡፡
ዐውደ ርእዩ ከነዚህ ዐበይት ትዕይንቶች በተጨማሪ የሕፃናት ትዕይንትም የተካተተበት ሲኾን፣ በዚህ ትዕይንት ለሕፃናት አእምሮ የሚመጥኑ መንፈሳውያን ትምህርቶች ተዘጋጅተውበታል፡፡
በትዕይንቱ ውስጥም የአዳምና የሔዋን ታሪክ፣ ነገረ ድኅነት እና ነገረ ቅዱሳን በሥዕላዊ መግለጫ ቀርቧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የቤተ ክርስቲያን የዜማ መሣሪያዎችና ንዋያተ ቅድሳት፣ እንደዚሁም ፊደለ ሐዋርያና ሌሎችም የልጆችን ስሜት ሊያስደስቱ የሚችሉ የትዕይንቱ ክፍሎች ተዘጋጅተዋል፡፡ ሕፃናቱም ክፍሉ ውስጥ እየዘመሩ ይማራሉ፤ ይደሰታሉ፡፡
ከሁሉም በተለየ መንገድ ደግም ከቍጥር ፩ አዳራሽ በስተሰሜን አቅጣጫ ካሉት ዛፎች ሥር ጊዜያዊ ጎጆ ቀልሰው የሚገኙት የሁሉም ገባኤያት (የንባብ፣ የዜማ/የድጓ፣ የቅዳሴ፣ የቅኔ፣ የአቋቋም፣ የመጻሕፍትና የአቡሻሕር ጉባኤ ቤቶች) መምህራን ደቀ መዛሙርታቸውን በተግባር ሲያስተምሩመታየታቸው የኤግዚብሽን ማዕከሉን የኹሉም ጉባኤያት መገኛ ገዳም አስመስሎታል፡፡
የንባብ ተማሪዎች ከመምህራቸው ከመምህር ተክለ ጊዮርጊስ ደርቤ እግር ሥር ቁጭ ብለው መጽሐፎቻቸውን በአትሮንሶቻቸው ዘርግተው ተነሽ፣ ተጣይ፣ ወዳቂና ሰያፍ ሥርዓተ ንባብን ለመለየት ይችሉ ዘንድ ተጠንቅቀው ያነባሉ፡፡
የቅዳሴ ደቀ መዛሙርት ከመጋቤ ስብሐት ነጋ፤ የዜማ/የድጓ ደቀ መዛሙርት ደግሞ ከሊቀ ምሁራን ይትባረክ ካሣዬ፤ የዝማሬ መዋሥዕት ደቀ መዛሙርትም ከመጋቤ ብርሃናት ፈንታ አፈወርቅ እግር ሥር ቁጭ ብለው ትልልቅና ባለምልክት የዜማ መጻሕፍቶቻቸውን በአትሮንሶቻቸው ላይ አስቀምጠው በግዕዝ፣ ዕዝልና በዓራራይ በተመሠረተው የቅዱስ ያሬድ ሰማያዊ የዜማ ሥርዓት መሠረት ያዜማሉ፤ መምህራኑም እርማት ይሰጣሉ፡፡
የቅኔ ደቀ መዛሙርትም አንድም ግስ በማውረድ፣ አንድም ከመምህራቸው ፊት ኾነው ቅኔ በመንገርና በማሳረም፣ አንድም መምህራቸው የዘረፉላቸውን ቅኔዎች በመቀጸል ግቢውን አድምቀውታል፡፡ የአቋቋም ደቀ መዛሙርት ደግሞ ከመምህራቸው ከመምህር ዮሐንስ በርሄ ፊት ለፊት ክብ ሠርተው በመቀመጥ በዕለቱ የሚቀጽሉትን ቃለ እግዚአብሔር በጣቶቻቸው እያጨበጨቡ፣ በእግሮቻቸው እያሸበሸቡ ሲያዜሙ የንጋት አዕዋፍን ዝማሬ ያስታውሳሉ፡፡
የአቡሻሕርና የድጓ መምህር የኾኑት መጋቤ አእላፍ ወንድምነው ተፈራም እርጅና ሳይበግራቸው የዘመናት፣ የበዓላት፣ የዕለታትና የአጽዋማት ማውጫ ቀመር የኾውን የባሕረ ሐሳብ ትምህርት ለደቀ መዛሙርታቸው በማስቀጸል ላይ ናቸው፡፡ መምህር ዘለዓለም ሐዲስም የመጻሕፍት ትርጓሜ ደቀ መዛሙርታቸውን ከፊት ለፊታቸው አስቀምጠው ብሉዩንም፣ ሐዲሱንም፣ ሊቃውንቱንም፣ መነኰሳቱንም ለደቀ መዛሙርታቸው ይተረጕማሉ፡፡
ምን ይኼ! ብቻ የብራና መጻሕፍት አዘገጃጀትም የጉብኝቱ አካል ኾኖ ሰንብቷል፡፡ ከዚህ ሌላ ለትዕይንቱ መጨረሻ ከኾነው አዳራሽ ውስጥ ከሚጎበኙ የማኅበሩ ልዩ ልዩ ክፍሎች መካከል አንዱ በኾነው የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮግራም የትዕይንት ክፍል ውስጥ ከጠረፋማ አከባቢዎች የመጡትና የአብነት ትምህርት በመማር ላይ የሚገኙት ሕፃናት ሴቶችና ወንዶች ብትፈልጉ ውዳሴ ማርያም፣ ቢያሻችሁ ደግሞ መልክዐ ማርያም ያነበንቡላችኋል፡፡ ይህም ቤተ ክርስቲያናችን በብሔር፣ በዘር፣ በቀለም፣ በጎሣና በጾታ ሳታበላልጥ የማይነጥፈውን መንፈሳዊ እውቀቷን ለኹሉም እንደምታካፍል አመላካች ነው፡፡
በልማት ተቋማት አስተዳደር ተዘጋጅተው ለሽያጭ የቀረቡት ንዋያተ ቅድሳት (መንበር፣ ልብሰ ተክህኖ፣ አክሊል፣ መጎናጸፊያ፣ ጽንሐሕ/ጽና፣ ቃጭል፣ ወዘተ) እንደዚሁም የቤተ ክርስቲያን የዜማ መሣሪያዎች በሥርዓት ተደርድረው እዩን፤ እዩን፤ ግዙን፤ ግዙን ይላሉ፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍቱም እንደዛው፡፡
ከዐውደ ርእዩ ጎን ለጎን ከምሽቱ 11፡00 ጀምሮ የንባብ፣ የቅዳሴና የሰዓታት፣ የአቋቋምና የዝማሬ መዋሥዕት፣ ባሕረ ሐሳብ (የአቡሻኽር ትምህርት)፣ ቅኔ፣ ትርጓሜ መጻሕፍት፣ ዜማ/ድጓ ምንነታቸውን፣ አገልግሎታቸውን፣ አቀራረባቸውንና ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር ያላቸውን ትስስር የሚያስረዱ ጥናቶች በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሲቀርቡ ሰንብተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ እሑድ ግንቦት ፳፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ሙስናን ከመዋጋት አንጻር ያለው ሚና እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ፈተናዎችና መፍትሔዎቻቸው በሚሉ አርእስት በዐዲስ አበባ መንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን አዳራሽ ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡
ባጠቃላይ በዐዲስ አበባ ኤግዚብሽ ማዕከል በተዘጋጀው አምስተኛው የማኅበረ ቅዱሳን ዐውደ ርእይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ተነቧል፤ ተተርጕሟል፤ ተብራርቷል፡፡ በዓለማዊ ጉዳዮች ተጨናንቆ የነበረው የኤግዚብሽን ማዕከሉ በመንፈሳዊ ትምህርትና ጣዕመ ዜማ ደምቆ ለስድስት ቀናት ያህል በመሰንበቱ እጅግ ተደስቷል፡፡ ዐውደ ርእዩ በድጋሜ ቢታይ የሚልም ይመስላል፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአምስተኛው የማኅበረ ቅዱሳን ዐውደ ርእይ በዐዲስ አበባ ኤግዚአብሽን ማዕከል በግልጽ ታይታለችና፡፡ እርሷን ማየት፣ ትምህርቷንም መስማት፣ ጣዕመ ዜማዋን ማጣጣም እጅግ አስደሳች ነውና፡፡
ከላይ በገለጽነው መልኩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ለምእመናን ሲያስረዳ የነበረው ይህ ዐውደ ርእይ ግንቦት ፳፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ከምሽቱ 4፡00 ገደማ በሰላም ተጠናቋል፡፡ ይህ ዐውደ ርእይ በእግዚአብሔር ኃይል፣ በቅዱሳን ተራዳኢነት በሚያስደስትና በሚማርክ መልኩ ያለምንም ችግር ተከናውኗል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡