የኢትዮጵያውያን ቅዱሳት አንስት አርአያነት
የመጀመሪያዋ ሴት ‹ሔዋን›ን ለአዳም ረዳት እንድትሆነው እግዚአብሔር አምላክ ፈጠራት፤ ‹‹እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍን አመጣ፤ አንቀላፋም፤ ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ መላው። እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት፡፡ ያን ጊዜም አዳም አለ÷ ‹‹ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት÷ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል፡፡›› (ዘፍ.፪፥፳፩-፳፫)
ሁለቱም በገነት ሲኖሩ አምላካቸውን ይታዘዙ፤ ቃሉንም ይፈጽሙ ነበር፡፡ እናታችን ሔዋን ባደረገችው አመጽ ከገነት ብትወጣም በእርሷ ምትክ የዓለም ቤዛ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ እናት፤ የመላእክት እህት፤ የሁሉ እመቤት ቅድስት ድንግል ማርያምን አምላካችን ፈጥሮልናል፡፡ ጌታችንም ከእርሷ ተወልዶ በመልዕልተ መስቀልም ተሰቅሎ የእርሱን ሕይወት ለእኛ ሰጠን፡፡ እኛም ‹‹እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም›› ብለን የምናከብራትና የምልጃዋን በረከት የምንማፀነው ለእናትነቷ ካለን ታላቅ አክብሮት የተነሣ ነው። ‹‹ሰው ሁሉ እናታችን ጽዮን ይላል›› (መዝ. ፸፮፥፭) ተብሎ በትንቢት የተነገረላት እና ጌታችን ኢየሱስም ለዮሐንስም ‹‹እነኋት እናትህ›› (ዮሐ. ፲፱፥፴፰) ያላት ክብርት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡
የቅዱሳት አንስት ገድል እንደ አርአያና ምሳሌ ሆኖ ለብዙ ምእመናን ትምህርት ሊሆን የሚችል ታሪክ ነው። የእነዚህም አንስት ተጋድሎ እንደየዘመናቱ ቢለያይም ለሕዝቡ ካለው ሚና አንጻር ሁሌም አስፈላጊነቱ የላቀ ነው፡፡ በየዘመናት ኖረው ድንቅ ተጋድሎን በመፈጸም በክርስቶስ ክርስቲያን የሆኑት ፴፮ቱ ቅዱሳት አንስት ማለትም ኤልሳቤጥ፣ ሐና፣ ቤርዜዳን ወይም ቤርስት፣ መልቲዳን ወይም ማርና፣ ሰሎሜ፣ማርያም መግደላዊት፣ ማርያም እንተ እፍረት እኅተ አልአዛር፣ ሐና ነቢይት፣ ማርያም እሞሙ ለደቂቀ ዘብዴዎስ፣ ሶፍያ (በርበራ)፣ ዮልያና (ዮና)፣ ሶፍያ (መርኬዛ)፣ አውጋንያን (ጲላግያ)፣ አርሴማ፣ ዮስቲና፣ ጤግላ፣ አርኒ (ሶፍያ)፣እሌኒ፣ ኢዮጰራቅሊያ፣ ቴዎክላ (ቴኦድራ)፣ክርስቲያና (አጥሩኒስ)፣ ጥቅሞላ (አሞና)፣ ጲስ፣ አላጲስ፣ አጋጲስ፣ እርሶንያ (አርኒ)፣ ጲላግያ፣ አንጦልያ (ሉክያ)፣አሞን (ሶፍያ)፣ ኢየሉጣ፣ መሪና፣ ማርታ እህተ አልአዛር፣ ማርያም የማርቆስ እናት፣ ሣራ (ሶፍያ) የይሁዳ እናት፣ ዮሐና (ዮላና) የኩዛ ሚስት እና ሶስና ተምሳሌቶች በመሆናቸው ቤተ ክርስቲያን ትዘክራቸዋለች፡፡ (ነገረ ቅዱሳን)
ኢትዮጵያውያን ቅዱሳት አንስት
በኢትዮጵያ ክርስትና ታሪክ የቅዱሳት አንስት ተጋድሎ እጅግ ድንቅ ነው፡፡ ከእነዚህም ቀደምት ተጠቃሽ የብሉይ ኪዳን እምነትን ለሕዝቦቿ በማስተማር ግዛቷ በሕገ ኦሪት ሥርዓት እንዲሆን ያደረገች የኢትዮጵያ ንግሥት ንግሥተ ዓዜብ ናት፡፡ (ክብረ ነገሥት) ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር ‹‹ንግሥተ ዓዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርዳለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ስትሰማ ከምድር ዳርቻ መጥታለችና፤ እነሆም፥ ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ (ማቴ. ፲፪፥፵፪)›› በማለት ተናግሯል።
ኢትዮጵያዊት ተምሳሌት ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ከእግዚአብሔር ለዲያብሎስ ምሕረት በጠየቀች ጊዜ ጌታችን «ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ዕፁብ ድንቅ ልመና ለመንሽኝ! ሌሎች በኋላሽም የነበሩ በፊትሽም የሚመጡ ያልለመኑትን ልመና ለመንሽኝ» ብሎ የመሰከረላት ጻድቅ ሴት ናት፡፡ ጠላት ዲያብሎስን ባነጋገረችው ጊዜም ፲ ሺህ ያህል ነፍሳት ከሲኦል በእርሱ ፈንታ እንዳወጣች መጽሐፈ ገድሏ ላይ ተመዝግቧል፡፡ (የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ መጽሐፈ ገድል)
ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አንዱን ያነፀችው ቅድስት መስቀል ክብራ፣በንጽሕና ኖራ ሰማዕትነትን የተቀበለችው ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ (እመ ምዑዝ)፣ የቅኝ ገዥ ካቶሊኮች በሀገራችን ኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳውያንን አስገድደው እምነት በማስለወጥ ላይ በነበሩበት ዘመን በቅድስናና በጥብዓት ሰማዕትነትን የተቀበለችው ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ የተከበሩ ኢትዮጵያውያት ቅዱሳት አንስት ናቸው።
ኢትዮጵያውያን ሴት አገልጋዮች
ሴት ሕገ እግዚአብሔር በፈቀደላት መጠን ፈጣሪዋን ታገለግላለች፤ ሴቶች የወንዶች የሕይወት አጋር እንዲሆኑ ከተፈጠሩበት ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔር አምላካቸውን ሲያገለግሉ ኖረዋል፡፡ ይህም በዘመናት ልዩነት ሳይገታ በሥርዓተ አምልኮት ለእምነታቸው ተጋድሎ በመፈጸም እንደተገለጸ ብዙኃን የቅዱሳት መጻሕፍት ጠቅሰዋል፡፡
ሴት መንፈሳዊ አገልጋዮች ቅድሚያ የግል ፍላጎታቸውን በመገደብ ራስን በመግዛት በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በመኖር ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች መዳን የሚተጉ ሴቶች ናቸው፡፡
ሴቶች በሕገ እግዚአብሔር እና በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በመኖር ፈጣሪን ማገልገል የተፈጥሮ ግዴታ መሆኑን ማወቅ ቀዳሚ ተግባራቸው ነው፡፡ ይህንንም የተገነዘቡ ሴቶች ከሰንበት ትምህርት ቤቶች ጀምሮ በዝማሬ፤ በሰበካ ጉባኤዎች እንዲሁም በሌሎችም መርሐ ግብሮችና በበዓላት ላይ በመሳተፍ በጉልበትም ሆነ በገንዘብ እንዲሁም በሞያቸው የሚያገለግሉ አሉ፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ ትምህርተ ሃይማኖት፣ ነገረ መለኮትን እና የአብነት ትምህርቶችን በመማር እስከ ምንኩስና ማዕረግን በማግኘት በቤተ ክርስቲያናት፣ ገዳማትና የተለያዩ አድባራት ውስጥ መንፈሳዊ አገልግሎቶች እየሰጡ የሚገኙ ሴቶች በሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙዎች ናቸው፡፡
ሀገራችን የቤተ ክርስቲያን መምህራን እንደ መምህርትሶስና በላይ የዳንግላ ወረዳ ቤተ ክህነት ጆንጂ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የቅዳሴ ዜማ ምዕራፍ መምህርት፤ መምህርት ሕይወት ፀሐይ፤ የርዕሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ቅዱስ ያሬድ መንፈሳዊ አብነት ትምህርት ቤት የቅኔ መምህርት እና ሌሎችም መምህራንን አፍርታለች፡፡ እነዚህም መምህራን ሴቶችን በመንፈሳዊው ዕውቀት በማነጽ፣ ምክር በመለገስ እንዲሁም በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ አገልግሎታቸው የሰፋ አንዲሆን በመርዳት ላይ ይገኛሉ።
በቅኔ ትምህርት ድንቅ ሥራን የሰሩት እማሆይ ሐይመት እንዲሁም እማሆይ ገላነሽ ቀጥሎም የመጡት ሴት የቅኔ መምህራት እማሆይ ኅርይትና እማሆይ ወለተ ሕይወት ያሳዩት አርአያነት ሴቶች ከባድ በሚባለው የቅኔ ዘርፍ ሳይቀር በማስተማር ጉልህ ድርሻ ሊኖራቸው እንደሚችል ማረጋገጫዎቻችን ናቸው። በርካታ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለቤተክርስቲያን ያበረከቱት እቴጌ እሌኒም እንዲሁ የቤተ ክርስቲያን ባለውለታ ናቸው።
ሆኖም ከዚህ በተጓዳኝ በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ለመኖር ፍላጎታቸው አነስተኛ የሆነ፣ የመፈጠራቸውን ምክንያት የማያውቁ ሴቶች በርካታ ናቸው፡፡ ከአለባበስ ጀምሮ የክርስቲያናዊ አለባበስ ሥርዓትን ያልጠበቁ አልባሳት በቤተ ክርስቲያን ሳይቀር የሚለብሱና የአምልኮተ ሥርዓቱን የሚተላለፉ ሴቶች እንዳሉ ዓይናችን ምስክር ነው፡፡ ስለዚህም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እንዲሁም ደግሞ ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ፤ እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት ሴቶች እንደሚገባ÷ መልካም በማድረግ እንጂ በሹሩባና በወርቅ ወይም በዕንቁ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸሉሙ፡፡››(፩ጢሙ. ፪፥፲-፲፩) ሲል አዟል፡፡
ሴቶች በእምነት በመኖር፣ አምልኮተ እግዚአብሔርን በመፈጸም፣ በቤተ ክርስቲያንም ከወንድ አገልጋዮች ጋር ሕጉ በፈቀደላቸው መጠን ፈጣሪን በማመስገን፣ በማወደስ እና በመዘከር በዝማሬና በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ማገልገል ይጠበቅባቸዋል፡፡ በጸሎትና በጾም በመትጋት በችግርና በመከራ ጊዜም ሱባዔ በመያዝ እስከ ምንኩስና ባለው ማዕረግ ፈጣሪን ማገልገል እንደሚችሉ የቅዱሳት አንስት ገድላት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በገዳማት እስከ እመምኔት ባለው አስተዳደር ሴቶች መንፈሳዊ አገልጋዮች መሆን ይችላሉ፡፡
እግዚአብሔር አምላክ አገልጋዮቹ እንድንሆን ይርዳን፤ አሜን፡፡