የአፋር ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና ጽሕፈት ቤትና የእንግዳ ማረፊያ ተመረቀ

መጋቢት 2 ቀን 2008 ዓ.ም

ከሎጊያ ማእከል

02afarr

በአፋር ሀገረ ስብከት በሠመራ ከተማ በግንባታ ላይ የሚገኘው የመንበረ ጵጵስና ጽሕፈት ቤትና የእንግዳ ማረፊያ በብፁዕ አቡነ ዮናስ የአፋር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የካቲት 6 ቀን 2008 ዓ.ም ተመረቀ፡፡

01aafarr

የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የሀገረ ስብከቱ ዓመታዊ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ከየካቲት 5-6 ቀን 2008 ዓ.ም በሎጊያ ደብረ ማኅቶት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በሐመረ ኖኅ ሰንበት ትምህርት ቤት አዳራሽ በመከናወን ላይ እያለ ሲሆን የመንበረ ጵጵስናውን የግንባታ ሥራ ክንውን አስመልከቶ ገለጻ ተደርጓል፡፡

03afarr

ብፁዕነታቸውም በሥራው ላይ ለተሳተፉ ባለሙያዎች፣ የሀገረ ስብከቱ ልዩ ልዩ መምሪያ ሓላፊዎችና ሠራተኞችን፣ የወረዳ ቤተ ክህነት ሓላፊዎችንና ሠራተኞችን እንዲሁም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማበርከት ላይ ለሚገኙ ማኅበራትና ምእመናን ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው የካቲት 5 ቀን 2008 ዓ.ም ጠዋት በ2፡30 በብፁዕ አቡነ ዮናስ የአፋር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጉባኤው በጸሎተ ቡራኬ ተከፍቷል፡፡ ጉባኤው በሁለት ቀናት ውሎው የሚነጋገርባቸውን አጀንዳዎች እና የሀገረ ስብከቱ የ2007 ዓ.ም የዕቅድ አፈጻጸም ዘገባ በመጋቤ ሥርዓት መሠረት ስዩም የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸው ጸድቀዋል፡፡ ቀጥሎም በሀገረ ስብከቱ ውስጥ የሚገኙት የአምስቱ ወረዳ ቤተ ክህነቶች የ2007 ዓ.ም የዕቅድ አፈጻጸም ዘገባ በተወካዮቻቸው አማካይነት አቅርበው ጉባኤው ተወያይቶባቸዋል፡፡

04afarrከመንበረ ጵጵስና ጽሕፈት ቤትና የእንግዳ ማረፊያው ምረቃ ቀጥሎም የማኅበረ ቅዱሳን ሎጊያ ማእከል የ2007 ዓ.ም የዕቅድ ክንውን፣ እንዲሁም ማእከሉ ያዘጋጀውን የሀገረ ስብከቱ የ20 ዓመት ሐዋርያዊ ጉዞ ረቂቅ ጽሑፍ ሰነድ ገለጻ የተደረገ ሲሆን፣ የ20 ዓመት ሐዋርያዊ ጉዞውን በማስመልከት ዐውደ ርእይ ቀርቦ ለጽሑፉ ግብዐት የሚሆኑ ውይይቶች ተካሒደዋል፡፡

በዐውደ ርእዩ ከዚህ ቀደም የአፋር ሀገረ ስብከትን በመምራትና በማስተዳደር የሚታወቁት ሊቃነ ጳጳሳት፣ እንዲሁም ብፁዕ አቡነ ዮናስ ወደ ሀገረ ስብከቱ ከመጡ በኋላ ያከናወኗቸውን መንፈሳዊ አገልግሎት እና ልማት ተዳስሰዋል፡ በዓመቱም ጥሩ ውጤት ላስመዘገቡ ወረዳ ቤተ ክህነቶች፣ ለአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት፣ ለሎጊያ ማእከልና ሰንበት ትምህርት ቤቶች የምሰክር ወረቀት ተሰጥቶ የጉባኤው የአቋም መግለጫ ከተነበበ በኋላ በብፁዕነታቸው ቡራኬና ጸሎት ተጠናቋል፡፡

በጉባኤው ላይ የሀገረ ስብከቱ የሥራ ሓላፊዎች፣ የወረዳ ቤተ ክህነት ሊቃነ ካህናት፣ የየአጥቢያው ተወካዮች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች፣ የሎጊያ ማእከል ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡