የአዳማ አቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤትን ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ
ነሐሴ 2 ቀን 2006 ዓ.ም.
እንዳለ ደምስስ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን የአዳማ ማእከል ለሚያስገነባው የአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የአጸደ ሕፃናትና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሣልሳይ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የበላይ ሓላፊ ሐምሌ 27 ቀን 2006 ዓ.ም. የመሠረት ድንጋይ አኖሩ፡፡
በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሣልሳይ መሪነት፤ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፤ የናዝሬት ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ካህናትና አገልጋዮች፤ የማእከሉ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው ምእመናን በተገኙበት ጸሎተ ወንጌል በማድረስ ብፁዕነታቸው የመሠረት ድንጋይ ባኖሩበት ወቅት በሰጡት ቃለ ምእዳን “ከሁሉም ነገር በፊት የሰው ሀብት ዕውቀት ነው፡፡ ዕውቀት ደግሞ የማይሠረቅ ሀብት በመሆኑ የማይሠረቀውን፤ የማይዘረፈውን ሀብተ እግዚአብሔርን መያዝ መልካም ነው፤ የመሠረት ድንጋይ የምናኖረውም ድንቁርናን ለማጥፋት ነው” ብለዋል፡፡
ማኅበሩ የሚያከናውናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራትና ለቤተ ክርስቲያን እያበረከተ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ብፁዕነታቸው “ሁላችንም የምንሠራው የቤተ ክርስቲያናችንን ሥራ በመሆኑ፤ መሠረቱም፤ ጣሪያውም አንድ ነው፡፡ የማኅበሩ አባላት ቤተ ክርስቲያናችሁን እንደምትወዱ፤ እንደምታከብሩም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታውቃለች፤ ሁላችንም እንመሠክራለን፡፡ ትውልድን በሃይማኖትና በሥነ ምግባር ኮትኩቶ ማሳደግ ተገቢ በመሆኑ ከጎናችሁ ነን፤ በርቱ” በማለት የትምህርት ቤቱ ሕንፃ ግንባታ በፍጥነት ተጀምሮ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቃ ተመኝተዋል፡፡
ቀሲስ እሸቱ ታደሰ የማኅበሩን መልእክት ሲያስተላልፉ “ማኅበረ ቅዱሳን የተማረ ትውልድን ለመቅረጽ፤ ትምህርት ለማስፋፋት እንደ አንድ ዓላማ አድርጎ በመያዝ በየአኅጉረ ስብከቱ ዐሥር ትምህርት ቤቶችን በመክፈት ቤተ ክርስቲያንን የሚያውቅና በዕውቀት የበለጸገ ትውልድ ለማፍራት በመሥራት ላይ ነው፡፡ የአዳማ ማእከል ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ቤት ተከራይቶ የዐፀደ ሕፃናትና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመክፈት አገልግሎት እየሠጠ ቢሆንም፤ የተማሪዎቹ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ በመምጣቱ ሰፋ ያለ ቦታ ማግኘት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሆነ፡፡ በዚህም መሠረት የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስን በማስፈቀድ በአንድ ሚሊዮን ብር ከአባላት በማሰባሰብ በአዳማ ከተማ መሬት በመግዛት በዛሬው እለት በብፁዕነታቸው የመሠረት ድንጋይ ለማኖር በቅተናል” ብለዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ሕፃናትን በቃለ እግዚአብሔር ኮትኩቶ ማሣደግን ከፍተኛ ትኩረት ይሰጡ እንደነበር የገለጹት ቀሲስ እሸቱ ከብፁዕነታቸው ኅልፈት በኋላም በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሣልሣይ ቀጣይነት ኖሮት በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የካህናት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት፤ እንዲሁም በሀገረ ስብከታቸው የሚያከናውኗቸው የትምህርትና የልማት ሥራዎች ለሁሉም አርአያ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡
የአዳማ አቡነ ጎርጎርዮስ የአጸደ ሕፃናትና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ2004 ዓ.ም. ቤት ተከራይቶ 32 ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የጀመረ ሲሆን፤ የማእከሉ አባላት የቤት ኪራይ በመክፈል፤ የጽዳት ሥራውን በማሰራት፤ እንዲሁም ጊዜያቸውን መሥዋዕት በማድረግ በነጻ ያስተምሩ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታቸው እንደሆነ አባላቱ ይገልጻሉ፡፡
በ2300 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚገነባው ባለ4 ፎቅ የተማሪዎች መማሪያ ሕንፃ 12 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅም ከማእከሉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡