የአዳማ ማእከል በአፋን ኦሮሞ ሥልጠና እየሰጠ ነው
በዝግጅት ክፍሉ
ሐምሌ ፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
በማኅበረ ቅዱሳን የአዳማ ማእከል ከምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ልዩ ልዩ ወረዳዎች ለተውጣጡ ሠላሳ ስድስት ሰባክያነ ወንጌል በአፋን ኦሮሞ የስብከተ ወንጌል እና የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና በአዳማ ከተማ እየሰጠ ነው፡፡
ሠልጣኞቹ በሀገረ ስብከቱ፣ በወረዳ ቤተ ክህነቶቹና በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ ፈቃድ የተመረጡ፣ በክርስቲያናዊ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው የቤተ ክርስቲያን ልጆች እንደ ኾኑ፤ የቤተ ክርስቲያን አባልነት፣ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን መላበስ፣ በሰንበት ት/ቤቶች ተሳትፎ ማድረግ፣ ቢቻል መዓርገ ክህነት መያዝ በተጨማሪም አማርኛ ቋንቋ እና አፋን ኦሮሞ መናገር መቻል በምልመላ መሥፈርቱ እንደ ተካተቱ የአዳማ ማእከል ለዝግጅት ክፍላችን አስታውቋል፡፡ ከሠላሳ ስድስቱ ሠልጣኞቹ መካከል አንዱ ቄስ፤ ሰባቱ ዲያቆናት መኾናቸውንም ለመረዳት ችለናል፡፡
እንደ ማእከሉ ዘገባ ሥልጠናው የሚሰጠው ለዐሥራ አምስት ቀናት ቀንም ሌሊትም ሲኾን፣ መሠረተ እምነት፣ ነገረ ቅዱሳን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ የስብከት ዘዴ፣ ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር፣ ወቅታዊ ጉዳዮች፣ የጊዜ አጠቃቀም፣ መንፈሳዊ አገልግሎት፣ መሪነትና ውሳኔ አሰጣጥ እንደዚሁም ምክረ አበው ለሠልጣኞቹ የሚሰጡ የትምህርት ክፍሎች፤ አሠልጣኞች ደግሞ በልዩ ልዩ የአገልግሎት ዘርፍ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን መምህራን ናቸው፡፡
ለሠልጣኞቹ ሰኔ ፳፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም የአቀባበል ሥርዓት በተደረገላቸው ጊዜ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ትፍሥሕት ሙሉጌታ ቸርነት ተገኝተው ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡
በትምህርታቸውም መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት ያደላቸውን በልዩ ልዩ ቋንቋ የመናገር ጸጋ ዋቢ በማድረግ ማእከሉ በአፋን ኦሮሞ የስብከተ ወንጌል ሥልጠና መስጠቱ በየገጠሩ በቋንቋ ችግር ምክንያት ወንጌል ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች ሰፊ አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳለው አስረድተዋል፡፡
ሀገረ ስብከቱ ሊደርስ ያልቻለባቸውን የአገልግሎት ክፍሎች በማሟላት የአዳማ ማእከል ለሚሰጠው ዘርፈ ብዙ ተልእኮም ማኅበረ ቅዱሳንን አመስግነዋል፡፡
ሀገረ ስብከታቸው ለወደፊት በአፋን ኦሮሞ የስብከተ ወንጌል ሥልጠና ለመስጠት ማቀዱን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ የማእከሉን አገልግሎት እንደሚደግፉም ቃል ገብተዋል፡፡
በትምህርታቸው ማጠቃለያም ‹‹የሚጠብቃችሁ ሕዝብ አለ፡፡ ሥልጠናውን ፈጽማችሁ ድረሱላቸው፡፡ ጕዟችሁ የወንጌል ጉዞ ነው፡፡ እንደ ሐዋርያት ለማታውቁት ሕዝብ ሳይኾን ለወገኖቻችሁ ወንጌልን የመስበክ አደራ አለባችሁ›› በማለት ሠልጣኞቹ የሚጠበቅባቸውን ተልእኮ በትጋት እንዲወጡ መክረዋል፡፡
የሀገረ ስብከቱ ሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ክፍል ሓላፊ ሊቀ ካህናት ነጋሽ ሀብተ ወልድ በበኩላቸው ክርስትና የዅሉም ሕዝብ እንጂ የተወሰኑ ሰዎች፤ ቋንቋም መግባብያ እንጂ መለያያ እንዳልኾነ ጠቅሰው ወንጌልን በየቋንቋው ለማዳረስ ማእከሉ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡
ለሠልጣኞቹም ‹‹ለዚህ ዕድል በመመረጣችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ! ቃለ ወንጌሉን ያልተማሩ፣ በነጣቂዎች የተወሰዱ በየገጠሩ የሚኖሩ ወገኖቻችሁን ታገለግሉ ዘንድ ተመርጣችኋልና ለእነዚህ ወገኖች ልትደርሱላቸው ይገባል›› በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በዕለቱ ከተገኙ በጎ አድራጊ ምእመናን መካከል አቶ ለማ ተፈሪ፣ አቶ ነገሠ ይልማ፣ እና አቶ ተስፋዬ መንገሻ የተባሉ የከተማው ነዋሪዎች ይህን ሥልጠና በመስጠቱ ማእከሉን አድንቀው በአፋን ኦሮሞ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት መሰጠቱ በየቋንቋው ወንጌልን በማስተማር ያመኑትን ለማጽናት፣ በመናፍቃን የተወሰዱትን ለመመለስ እና አዳዲስ አማኞችን ወደ ቤተ ክርስቲያን ለማምጣት የሚኖረውን ጠቀሜታ አብራርተዋል፡፡
የአዳማ ማእከል ሰብሳቢ መምህር ጌትነት ዐሥራት ደግሞ ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ የኾነውን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት የማሳካት ሓላፊነት እንዳለበት አስታውሰው በመናፍቃን ከሚፈተኑ አካባቢዎች መካከል ኦሮምያ ክልል አንዱ በመኾኑ ምእመናንን በሃይማኖታቸው ለማጽናትና ከነጣቂዎች ለመጠበቅ፤ ያላመኑትንም ለማሳመን ይቻል ዘንድ ማእከሉ በአፋን ኦሮሞ የስብከተ ወንጌል እና የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ለመስጠት መነሣሣቱን አስታውቀዋል፡፡
በመጨረሻም ለሥልጠናው መሳካት እገዛ ያደረገው የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከትን፤ ለሕክምና፣ ለምግብ፣ ለመጻሕፍትና ለትምህርት መሣርያዎች የሚያስፈልገውን ወጪ በማገዝ ሥልጠናውን የደገፉ በጎ አድራጊ ምእመናንን ሰብሳቢው በማኅበረ ቅዱሳን ስም አመስግነዋል፡፡
ከማእከሉ የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው የአዳማ ማእከል በአፋን ኦሮሞ የስብከተ ወንጌል ሥልጠና ሲሰጥ አሁን ሁለተኛው ነው፡፡
በመጀመርያው ዙር የሠለጠኑ ሃያ ዘጠኝ ሰባክያነ ወንጌል በክልሉ ገጠራማ ሥፍራዎች ለሚኖሩ ምእመናን ትምህርተ ሃይማኖትን ከማዳረሳቸው ባሻገር ሞጆ አካባቢ አምስት አዳዲስ አማኞችን በማስተማር የሥላሴ ልጅነትን እንዲያገኙ አድርገዋል፡፡
የሁለተኛው ዙር ሠልጣኞችም ተመርቀው በየቦታው ሲሰማሩ ከዚህ የበለጠ የአገልግሎት ፍሬ ያስመዘግባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሠልጣኞቹም ሐምሌ ፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ይመረቃሉ፡፡
ከዚህም ሌላ በአዳማ ማእከል የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል አስተባባሪነት በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እና የካህናት ማሠልጠኛ ተቋም ለሚገኙ መነኮሳትና አብነት ተማሪዎች ሰኔ ፳፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በነጻ የሕክምና አገልግሎት መሰጠቱን፣ የመድኃኒት ድጋፍም መደረጉን ማእከሉ ያደረሰን ዘገባ ያመላክታል፡፡
ከማእከሉ አባላት እና ከአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ግቢ ጉባኤ ተማሪዎች የተውጣጡ ሠላሳ አራት ሜዲካል ዶክተሮች በተሳተፉበት በዚህ አገልግሎት ለዐሥራ ስድስት አባቶች መነኮሳት፤ ለስድስት እናቶች መነኮሳይያት እና ለሰባ አምስት አብነት ተማሪዎች የሕክምና ርዳታ፤ የላቦራቶሪ ምርመራ እና የመድኃኒት ድጋፍ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም የግል እና የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ትምህርት በጤና ባለሙያዎች ተሰጥቷል፡፡
በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያም የሕክምና ባለሙያዎችን በማስተባበር ማእከሉ ላደረገላቸው ክብካቤና ድጋፍ የሕክምና አገልግሎት የተሰጣቸው የገዳሙ አባቶች እና እናቶች ማኅበረ ቅዱሳንን በእግዚአብሔር ስም አመስግነዋል፡፡