የአዲስ አበባ ማእከል የግቢ ጉባዔያት ተማሪዎችን አስመረቀ
ሐምሌ 1 ቀን 2005 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
በማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማእከል የግቢ ጉባዔያት ማስተባበሪያ ክፍል፤ የቅዱስ ማርቆስ አካባቢ ማስተባበሪያ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አዳራሽ ሰኔ 30 ቀን 2005 በድምቀት አስመረቀ፡፡ ተማሪዎቹ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ /ከስድስት ኪሎ፤ ከአምስት ኪሎ ቴክኖሎጂ ፋኩልቲ፤ ከአራት ኪሎ የተፈጥሮ ሳይንስና ከቅዱስ ጳውሎስ/ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በድኅረ ምረቃና በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁ ሲሆኑ በግቢ ቆይታቸው መንፈሳዊ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ አንድ ሺህ የሚደርሱ ተማሪዎች ናቸው፡፡
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የኢሉባቦርና ጋምቤላ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመርሐ ግብሩ ላይ በመገኘት ባስተላለፉት ቃለ ምእዳንና ቡራኬ “ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያትን ካስተማራቸው በኋላ በሚሔዱበት ሁሉ አልተለያቸውም፡፡ እሱን መርህ አድርገው በዓለም ሁሉ ተበትነው ወንጌልን አስተማሩ፡፡ እናንተም የእምነትን መሣሪያ ይዛችኋል፤ በሥራችሁ ሁሉ እግዚአብሔር ይከተላችኋል፡፡ እናንተ ቀናዎች ከሆናችሁ ከሚመጣባችሁ ክፉ ነገር ይጠብቀችኋል፡፡ በቀኝ እጃችሁ እምነታችሁን፤ በግራ እጃችሁ ከዩኒቨርስቲ የቀሰማችሁትን እውቀት ይዛችሁ ተሰማሩ፡፡ ቤተ ክርስቲያንንም አገልግሉ” በማለት የአደራ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ቀሲስ ዶክተር ሰሙ ምትኩ በበኩላቸው ለተመራቂ ተማሪዎች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት ያሰተላለፉ ሲሆን “መማር ለማወቅ ነው፤ ማወቅ ለመሥራት፤ መሥራት ደግሞ ለውጤት ነው፡፡ በዚህ ሂደት የሰው ልጅ ባሕርይው እንደተጠበቀ ሆኖ ብዙ ለውጦችን ያሳያል፡፡ እነዚህን ለውጦች በአግባቡ ተጠቅሞ ወደ ውጤት ለመድረስ በተለይም በመንፈሳዊው ትምህርት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል ከተማሩ ወገኖች ብዙ ይጠበቃል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን በተማሩ ሰዎች ሊሠሩ የሚገባቸው በርካታ ተግባራት አሉ፡፡ እነዚህን ተግባራት ከአጥቢያ ጀምረን እስከ ላይ ድረስ ቀረብ ብለን በማየት፤ እንደየአቅማችንና እንደ ሥራው ሁኔታ ሠርተን ውጤት ልናመጣ ይገባል፡፡ ይህንንም መሠረት በማድረግ በምትሠማሩበት የሥራ ቦታ በግቢ ውስጥ በጥቂቱ የጀመራችሁትን መንፈሳዊ ጉዞ አብዝታችሁ እንድትቀጥሉ መንፈሳዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን ” ብለዋል፡፡
“ህያዋን ድንጋዮች” በሚል ርዕስ በዲያቆን ብርሃኑ አድማስ የወንጌል ትምህርት የተሰጠ ሲሆን የአዲስ አበባ ማእከል የመዝሙር ክፍል አባላት፤ እንዲሁም ተመራቂ ተማሪዎች ያሬዳዊ ወረብና ዝማሬ አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተመራቂዎች በማኅበሩ የተዘጋጀላቸውን የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡