የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መዋቅራዊ ለውጥ ረቂቅ ተፈጻሚ እንዲሆን ተጠየቀ፡፡
ጥር 3/2006 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
– “ወደ ኋላ የምንመለስበት ምንም ምክንያት የለንም” /ቅዱስ ፓትርያርኩ/
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መዋቅራዊ ለውጥ ረቂቅ ደንብ ተፈጻሚ እንዲሆን ከአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት የተውጣጡ አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎች የሰበካ ጉባኤ ተወካዮች፣ የሰንበት ት/ቤቶት ተወካዮችና ምእመናን ጥር 2 ቀን 2006 ዓ.ም ከቀትር በኋላ ቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት በመገኘት ድጋፋቸውን ገለጹ፡፡
ድጋፋቸውን የገለጹት የቤተ ክርስቲያኒቷ ተወካዮች፤ ረቂቁ ተግባራዊ ሆኖ ቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ እድገት የምታሳይበትን ቀን እየናፈቅን ሳለ አንዳንድ አካላት ከቀናት በፊት “ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው ማኅበረ ቅዱሳን ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ያወጣውን ደንብ አንቀበልም!” በማለት ደንቡ ተፈጻሚ እንዳይሆን፣ እንዲሁም ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የቅዱስ ፓትርያርኩ ረዳት የአዲስ አበባና የጅማ አኅጉረ ስብከት ሊቀጳጳስን በመዝለፍ ያቀረቡትን ጥያቄ ተቃውመዋል፡፡
“ቅዱስ አባታችን ያለፈው መነቃቀፍ ይበቃል፣ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ላይ የሚደረግ የስም ማጥፋት ዘመቻና ሰድቦ ለሰዳቢ አሳልፎ መስጠት ሕገወጥ ተግባር መቆም አለበት፡፡” ያሉት እነዚሁ አካላት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና ለቅዱስነታቸው ሥራ መሣካት ወሳኝ አባት መሆናቸውን በመግለጽ የጀመሩትን የልማት፣ የመልካም አስተዳደር እንዲሁም የአቅም ግንባታና የአሠራር መርሕ ዕቅድ ማሣካት እንዲችሉ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሥራ አደረጃጀቱን ተግባራዊ ለማድረግና ከሕዝቡ የሚገኘውን አስራት በኩራቱን፣ መብዓውንና በልማት ዘርፎች የሚገኘውን ገቢ በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል፣ የሒሳብ አጠቃቀምን ከወቅቱ ሥልጣኔ ጋር አዛምዶ አለማቀፋዊነቱን ጠብቆ መሥራት፣ ስብከተ ወንጌልን በተገቢው ሁኔታ ማዳረስ ወቅቱ የሚጠይቀው ሁኔታ በመሆኑ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት ተወካዮች እቅዱ ተግባራዊ እንዲሆን ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በሰጡት ምላሽም “ባለፈው ጊዜ የመጡትም ሆነ ዛሬ የመጣችሁት እናንተም ሁላችሁም የቤተ ክርስቲያን ልጆች ናችሁ፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የምትመሩ፣ የምታስተዳድሩና ምእመናንን የምታስተምሩ ናችሁ፡፡ ሁላችሁም ልጆቻችን ስለሆናችሁ አስተናግደናችኋል፡፡ በእኩልነት የሁሉንም ሀሣብ መስማትና ከፍጻሜ የማድረስ ኃላፊነት አለብን” ብለዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በመቀጠልም “ከቀናት በፊት የመጡት ገንቢና ተገቢ ያልሆነ አነጋገር ተናግረዋል፡፡ አግባብ ያልሆነ አነጋገር ማንም አይወድም፡፡ በሥነሥርዓት፣ በግብረገብነት፣ በቤተ ክርስቲያን ሰውነት፣ በእርጋታና በሰከነ አዕምሮ መነጋገር ትልቅ ነገር ነው፡፡ ንግግራችን ሁልጊዜ ቤተ ክርስቲያንን ያማከለ መሆን አለበት፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን ሕልውና ይቀድማል፡፡ እናንተ ያቀረባችሁበት መንገድ የሚያስመሰግናችሁ ነው፡፡ የሰከነ መንፈስ ይታያል፡፡ በቀረበው ጥናት ላይ ሊቃውንቱ ይጨመሩበት የሚል ሀሳብ ስለቀረበም ከ9-11 አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራውን ለመሥራት ዝግጅት ላይ ነው፡፡ ወደኋላ የምንመለስበት ምንም ምክንያት የለንም፡፡ መስመሩም አይለወጥም፡፡ በታቀደው መሠረት ቤተ ክርስቲያኒቱ ቀናና መልካም እንዲሁም ተጠያቂነት ያለው አስተዳደር እንዲኖራት ነው ጥረታችን$፡፡ በማለት ለተወካዮቹ ገልጸዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተውጣጡ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ የልዩ ልዩ ክፍፍ አገልጋዮች፣ የሰበካ ጉባኤና የሰንበት ት/ቤቶች ተወካዮች ረቂቅ ህገ ደንቡን በመደገፍ ያዘጋጁትን የአቋም መግለጫና ያሰባሰቡትን ፊርማ ለቅዱስነታቸው አስረክበዋል፡፡