የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቀባበል ተደረገላቸው
መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ
ህዳር 09 ቀን 2007 ዓ.ም.
በ2007 ዓ.ም የጥቅምት ሲኖዶስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው የተመደቡት ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ሥራ ለመጀመር ከሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች፣ ከአጥቢያ ገዳማትና አድባራት ሓላፊዎች፣ ጸሐፊዎችና ምእመናን ጋር ትውውቅ አድርገዋል፡፡
ብጹዕነታቸው የሥራ መጀመሪያቸው ለሆነው የትውውቅ መርሐ ግብር ወደ ሀገረ ስብከታቸው ሲሔዱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ለጉባኤው ታዳሚዎች ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳን ‹‹እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ›› በሚለው ቃለ ወንጌል የቅድስና ሥራ መሥራት እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የፍቼ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስም ‹‹ለሁለት ጌታ፤ ለገንዘብና ለእግዚአብሔር መገዛት አንችልም፡፡ ለገንዘብ ስንገዛ የኖርንበትን ዘመን ትተን እስቲ ለእግዚአብሔር እንገዛ›› በማለት አባታዊ መልእክታቸውን ለጉባኤው ታዳሚ አስተላልፈዋል፡፡
አዲሱ የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስም የሀገረ ስብከቱን ሠራተኞችንና ሌሎች የአጥቢያ ባለጉዳዮችን በጽ/ቤታቸው ብቻ እንደሚያስተናግዱ ገልጸዋል፡፡
ለብፁዕነታቸው መልካም የሥራ ዘመን እንመኛለን፡፡