የአባቶች ዕርቀ ሰላም መፍጠር፤ ለቤተ ክርስቲያንሐዋርያዊ አገልግሎትና ለሀገራዊ መግባባት ወሳኝ ሚና አለው!
በዮሐንስ አፈወርቅ
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መሠረቷኗ ጉልላቷ ክርስቶስ በመሆኑ የሰላም ደጅ ናት፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ በጻፈው መልእክቱ “የሰላምም ጌታ ራሱ በሁሉ መንገድ ዘወትር ሰላምን ይስጣችሁ፡፡ ጌታ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፡፡” (2ኛ ተሰሎ 3፡16) እንዳለ በክርስቶስ ሰላም እየተጠበቀች አንድነቷ ላይ የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች ሁሉ እየተቋቋመች አገልግሎቷን በማስፋፋት ምእመናንን ትጠብቃለች፡፡ አባቶችም ከቤተ ክርስቲያን የተቀበሉትን አደራ ተግተው በመጠበቅ መንጋውን በክርስቶስ ሰላም ማጽናት ይኖርባቸዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቁ ዘንድ ለመንጋውና ለራሳቸውም መጠበቅ ጥንቃቄ ያደርጉ ዘንድ የእግዚአብሔር ቃል ያስተምረናል፡፡ «በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ፣ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጐ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ» ሐዋ 20፡28
በመሆኑም የቤተ ክርስቲያን ጭንቀቷ ለጊዜያዊውና ለሚያልፈው ሳይሆን ለዘላለሙ፣ ለምድራዊው ሳይሆን ለሰማያዊው ሕይወት በመሆኑ፣ ዓለሙ ከሚከፋፈልበት የዘር፣ የጐሳ፣ የቋንቋና የርዕዮተ ዓለም አመለካከት ልዩነቶች የራቀች መሆን ይጠበቅባታል፡፡ የመንፈስ ልጆቿን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ወልዳ ከማይጠፋ ዘር በክርስቶስ ሥጋና ደም አንድ አድርጋ የምትመራ ለአንድና ለማያልፍ የእግዚአብሔር መንግሥት የምትሠራ ነፍሳትንም ለዚህ ክብር የምታዘጋጅ ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ጉልላቷ አንድ በመሆኑ፣ ልጆቿ ሁሉ በእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ የአንድ አካል ብልቶች እንዲሆኑ ትሠራለች፡፡ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች ሁሉ፣ ትእዛዛተ እግዚአብሔርን የሚፃረሩ በመሆናቸው፤ ለጥላቻዎችና መለያየቶች መንስኤ የሆኑ ነገሮችን አጥርቶ ማየትና መፍትሔ ለመስጠት መሄድ ሕገ እግዚአብሔርን መፈጸም ነው፡፡
ጥላቻዎችና መለያየቶች ሰላመ ቤተክርስቲያንንና ሕዝበ እግዚአብሔርን የሚያውኩ በመሆናቸው፣ በእነዚህ አትራፊ የሚሆነው፣ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ብቻ እንጂ፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ተከታዮቿ የሆኑት ሕዝበ እግዚአብሔር አይደሉም፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዓለሙ የሚለያይባቸውን ነገሮች የምታወግዝ እንጂ፣ አካሏን ለሚለያይና ፍቅርን ለሚያደበዝዙ ክፍተቶች አሳልፋ መተው የለባትም፡፡ እንኳን የራስን አካል ቀርቶ ቃሉ ጠላትንም መውደድ እንዲገባን ያስተምረናል፤ “እኔ ግን እላችኋለሁ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ የሚረግሙአችሁን መርቁ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ ይላልና—“ (ማቴ 5፡44-45) ክርስቲያኖች ሁሉ እውነተኛ ጨው ሆነን ዓለሙን ማጣፈጥ ሲገባን ይህን ቸል ብለን መንጋውን ለዓለሙ ክፉ ሐሳብ፤ መለያየትና ለዘረኝነት መራራ ፍሬ አሳልፈን እንዳንሰጥ መጠንቀቅ ይገባናል፡፡
ቅዱሳን ሐዋርያት ለዓለሙ ጨው ሆነው የወንጌልን ፋና ያበሩት፣ በአንድ ልብ ሆነው በጸሎትና በጾም በመትጋታቸው የመንፈስ ፀጋን በመጎናጸፋቸው ነው እንጂ፤ እርስ በርሳቸው በመለያየት አይይደለም፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፡- በአጥቢያዎች፣ በወረዳና በአህጉረ ስብከት የተደራጀች ስትሆን፤ እነዚህ መዋቅሮቿ፣ ጉልላቷና መሠረቷ የሆነውን የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትእዛዛት፣ መርሓቸው አድርገው የሚሄዱ እንጂ «ከእርሱም የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፣ በተሰጠለት በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና እያተያያዘ፣ ራሱን በፍቅር ለማነፅ አካሉን ያሳድጋል» ኤፌ 4፡16 ተብሎ የተጻፈውን በመቃረን፣ በየራሣቸው የሚመሩ፣ የማይነጋገሩና የማይተጋገዙ፣ አንዱ ለሌላኛው ግብኣት የማይሆኑ ብልቶች ሆነው በየግላቸው የሚጓዙ አይደሉም፡፡
ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚያርቁ ምክንያቶችና ክስተቶች፣ የክርስቶስ አካል በሆነችው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሉዓላዊነት ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ስለሆኑ፤ እነዚህን ምክንያቶችና ሁኔታዎች እያንዳንዳችን ትኩረት ሰጥተን መመርመርና ማየት ይገባናል፡፡ በመሆኑም ፈራጅ በመሆን ብቻ ወይም አጋጣሚውን ለየግል ፍላጐታችን መጠቀሚያ በማድረግ፡- መለያየትንና ጥላቻን የምናበረታታና የምናሣድግ፣ በአጠቃላይም ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የማይጠቅሙ ነገሮች እድል እንዲያገኙና ተደብቀው እንዲያድጉ፣ በቸልተኝነት ቀዳዳ የምንፈጥር እንዳንሆን መጠንቀቅ ይገባናል፡፡
ዓለሙ በራሱ ፍልስፍናና ምድራዊ ጥበብ፣ ሕግጋተ እግዚአብሔርን ባለመጠበቅ፣ የቅድስት ቤተክርስቲያንን ህልውና ለራሱ በሚመቸውና በሚጠቅመው መንገድ እንዲሆንለት ይሠራል፡፡ ጥበብ ምድራዊን መርሑ አድርጐ የሚሄድ ሰው ወይም አካል፡- የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሉዓላዊነት ዕውቅና ሰጥቶ ከመጠበቅ ይልቅ፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለእርሱ ተገዢና ዓላማ ማስፈጸሚያ እንድትሆንለት ይሻል፡፡ በዚህ ጊዜም የቅድስት ቤተክርስቲያን አባቶች በጥበብ ምድራዊ አመለካከት የሚገጥማቸውን ፈተና በጸሎት ተግተው፣ እየተመካከሩ ድል ያደርጉታል እንጂ፣ ፈተናው ከራሳቸው አልፎ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አንድነት፣ ህልውናና አገልግሎት እንዲገዳደር ዕድልና ቀዳዳ የሚፈጥሩለት አይሆኑም፡፡
የቤተ ክርስቲያንን አድነት ለማስጠበቅ አባቶች፡- ፈቃድ፣ አቅጣጫ፣ ኃይልና ጥበብ የሚጠይቁት፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን መሪ ከሆነው ከመንፈስ ቅዱስ እስከሆነ ድረስ፤ የዓለሙን ፍላጐትና ሐሳብ የሚከተል፣ በእርሱም ተጠልፎ የሚወድቅ አይደለም፡፡ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባቶች ሕይወትና ሥራ ሙሉ ለሙሉ የእግዚአብሔርን ክብርና የቤተክርስቲያንን ደኅንነት ቅድሚያ ሰጥቶ ለማረጋገጥ የቆመና ቁርጠኝነት ያለው ሲሆን፤ የዓለሙ ፍላጐት፣ ተፅዕኖ ሊያሳርፍበት አይገባም፡፡
የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት፡- በጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሠረትነት ላይ የታነፀ፣ መንገዱም፡- ግልፅ፣ አንድና የቀና እንጂ፤ ለግል አመለካከትና ፍላጐት ተገዢ የሚይሆን፤ በፈለግን ጊዜ የምንሄድበት? ባልፈለግን ጊዜ ደግሞ መዝጋትም ሆነ መገደብ የምንችለው አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ «ማንም እራሱን አያታል፤ ከእናንተ ማንም በዚች ዓለም ጥበበኛ የሆነ ቢመስለው፣ ጥበበኛ ይሆን ዘንድ ሞኝ ይሁን» 1ቆ 3፡18 ተብሎ እንደተጻፈው የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ህልውና የሚፈታተኑ ነገሮችና ሐሳቦች በሚፈጠሩበት ጊዜ፣ በመግባባትና በመተማመን ለመፍታት መሄድ ይገባል እንጂ፣ በራሳችን ጥበብ ጌታችን በሥጋና በደሙ ለመሠረታት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም መጠናከር አስተዋጽኦ ለማያደርጉ ሁኔታዎች አሳልፈን የምንሰጥ እንዳንሆን መጠንቀቅ ይገባናል፡፡
አባቶች የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሰላም፣ ሉዓላዊነትና አንድነት ጠንክረው የሚያስከብሩ በሚሆኑበት ጊዜ፣ ምእመናን ለፈተና ባለመጋለጥ ጸንተው በአጸዷ ውስጥ ለመኖር ያግዛቸዋል፡፡ በዓለሙ ያሉ ሰዎችም፣ ለአባቶች ክብር እንዲሰጡ ያደርጋቸዋል፡፡ አባቶች ሲናገሩ ተደማጭነትን፣ ሲመክሩ ደግሞ ተሰሚነትን ከሕዝቡ ሁሉ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል፡፡ «የራሷ ሲያርባት የሰው ታማስል» የሚለው አባባል ሳይጠቀስባቸው፣ ከራሳቸው በመትረፍ፣ በሀገሪቱ ችግሮች አፈታት ላይ ከፍ ያለ ቦታና ተፈላጊነት ያላቸው እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፤ ክብርና ሞገስም ያስገኝላቸዋል፡፡ ብዙዎችን በፍቅር መሸምገል የሚገባው እርሱ ለሽምግልና አስቸጋሪ ሊሆን አይገባም፡፡ ክርስትና በተግባር የሚታይ ሕይወት ነውና፡፡
ቤተ ክርስቲያን አንዲት ሆና እያለች «የውጪ እና የሀገር ውስጡ ሲኖዶስ» በሚል ሐዋርያዊ አገልግሎቷና የምእመናን አስተዳደሯ እርስ በርሳቸው በማይመካከሩና አንዱ ለሌላኛው ዕውቅና በማይሰጣጡ አካላት ለመምራት ሲኬድ የቆየ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎትና በምእመናን ሕይወት ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሮ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም እያንዳንዳችን ለችግሩ መፈጠር በቀጥታ ምክንያት ላንሆን ብንችል እንኳ፤ ከክስተቱ በኋላ ከትእዛዛተ እግዚአብሔርና ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አንጻር ተመልክተን ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ ለመስጠት በሚገባው መጠን ያህል ያልሄድን፤ ለቅድስት ቤተክርስቲያን አንድነት ቅድሚያ ባለመስጠት በቸልተኝነት ሁኔታው እየተባባሰ እንዲሄድ ያደረግን፤ ወይም ችግሩን መንፈሳዊ ከሆኑ አቅጣጫዎች ይልቅ፣ ዓለማዊና ግላዊ ከሆኑ ነገሮች አንፃር ስንመለከተው የቆየን ከሆነ፤ ለተፈጠረው ችግር የሚመለከተን ሁሉ ከሚጠበቅብን አንፃር፣ ባለድርሻዎች ናችሁ ብንባል፤ ቢያንሰን እንጂ የሚበዛብን አይሆንም፡፡
በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር መለያየት ምክንያት በውጭ ያሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አድባራት፡- በሀገር ውስጥ ባለው ሲኖዶስ የሚመሩ፣ በውጭ ሀገር የተቋቋመውን ሲኖዶስ እንደግፋለን በሚሉና ከሁለቱም ሳይሆኑ ገለልተኛ ነን በሚሉ ሦስት ቡድኖች ተከፋፍለው የሚገኙ ሆነዋል፡፡ የዚህ ሁሉ ክፍፍል መንስኤው፣ የተፈጠረውን ችግር በወቅቱ ሃይማኖታዊ በሆነ መንገድ ፈቶ መሄድ ባለመቻሉ፣ ማለትም የአንድነት አለመኖር ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ግልጽና የታወቀ ነውና፣ በመንፈሳዊነት ማሸነፍና መሸናነፍ ባለመቻሉ፣ ዓለማዊ የሆኑ ፍላጐቶችና ተፅዕኖዎች አይለውና ተሰሚነት አግኝተው በመቆየታቸው ነው፡፡ አሁንም ይህ መከፋፈል ካልተገታ፣ አሁን ካለው እያደገ በመሄድ፣ ብዙ ውስብስብና አስፈላጊ ያልሆኑ ሁኔታዎችን ሊፈጥር ይችላል፡፡
የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባቶችና ምእመናን ዘመኑን የዋጁ ካልሆኑ፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ጉዳዮች፣ ዓለማዊ የሆኑ ፍላጐቶችና ተፅዕኖዎች ምን ጊዜም መፈታተናቸው የማይቀር ነው፡፡ በዚህ ጊዜም፡- ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰላም፣ አንድነትና ህልውና ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን እየወሰድንና እየተባበርን የቅድስት ቤተክርስቲያን አንድነት የተጠናከረ፣ አገልግሎቷ የሰመረ፣ ምእመኖቿ በመንፈስ ቅዱስ መሪነትና በማንኛውም አቅም የተሰናሰሉና የጠነከሩ፣ ተስፋ መንግሥተ ሰማያት ያላቸው እንዲሆኑ፣ ዕንቅፋቶችን ሁሉ ማስወገድ እንደየድርሻችን የሁላችንም ተግባር ነው፡፡ ይህንን መፈጸም አባቶችና ምእመናን ከራሳቸው በማለፍ ለሀገሪቱ ዕድገትና ሰላም ድርሻቸው የላቀ እንዲሆን፤ ባጠቃላይም የሀገርን ችግር በመፍታቱ በኩል የሚኖራቸው ተፈላጊነትና ድርሻ ከፍ ያለ ደረጃ እንዲኖረው ያደርጋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በውጪ ሀገር ካሉ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር መግባባት እንዲኖር በተለያዩ ጊዜያት የዕርቀ ሰላም ልዑካንን በመላክ፣ በውጭ ሀገር ያሉ አባቶችም ለድርድር ፈቃደኛ በመሆን፣ ውይይቶች እየተጀመሩ እልባት ላይ ሳይደረስ፣ እንዲሁ ይቀሩ የነበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምት 2ዐ1ዐ ዓ.ም. ባደረገው መደበኛ ጉባኤው፣ አጀንዳ ቀርጾ ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች መካከል፡- በውጭ ሀገር ካሉ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር ተጀምሮ የነበረው የዕርቀ ሰላም ድርድር ቀጥሎ መፍትሔ እንዲያገኝ የሚለው አንዱ ነው፡፡ ነገሩ ሁለት ዐሥርት ዓመታትን ያሳለፈ ስለሆነ፣ እንደ ጉዳዩ አሳሳቢነት በፍጥነት እየተሄደበት ነበር ባይባልም፣ ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ በቋሚ ሲኖዶሱ አስፈላጊው ዝግጅት ሲደረግበት ከቆየ በኋላ፣ በአሁኑ ሰዓት ለሕዝበ ክርስቲያኑና ለሚመለከታቸው አካላት ግልጽ ተደርጐ፣ በሁለቱም ወገን ተወያይ የሆኑ አባቶች እና የዕርቀ ሰላም ኮሚቴው ለዝግጅቱ ደፋ ቀና በማለት ላይ ይገኛሉ፡፡
የምንስማማውና ዕርቅ የምናደርገው፡- ያስቀየምንና የተቀየምን፣ የበደልንና የተበደልን፣ ይቅር ልንልና ልንባባል ነው፡፡ በአባቶች መካከል ለተፈጠረው አለመግባባት ዕርቀ ሰላም የምናደርገው በሐዋርያት ሥራ 2ዐ፡28 እንደተገለጸው፣ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአባቶች የሰጠው የኖላዊነት ተግባር በአግባቡ ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ በዚህም፡- ምእመናን ወደ ለመለመው መስክ ሊመራቸው የሚገባ ጠባቂ በማጣት ለነጣቂ ተኩላ ሳይጋለጡ፤ በአንድ በረት ውስጥ ተጠብቀው፣ የመንግሥተ ሰማያት ወራሾች ይሆኑ ዘንድ ለማስቻል፣ ዕንቅፋት የሚሆኑ ነገሮችን ጊዜና ፋታ ሳይሰጡ ማስወገድና ማስተካከል የትጉህ እረኛ ተግባር ነው፡፡
ከዚህ አኳያም፡- የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባቶች የዓለሙን ክብርና ጥቅም ንቀው የሚተጉ ናቸውና፤ በድርድራቸው ላይ የሚያስቀድሙት የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፍላጐትና ህልውና ስለሆነ፤ መግባባት የማይችሉባቸው ነጥቦች ይኖራሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ አባቶች ተለያይተው በመቆየታቸው አንዳቸው በሌላኛው ላይ የሚያነሷቸው ነጥቦች ሊኖሩ ቢችሉ እንኳ፣ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገትና ህልውና ተፃራሪና ድብቅ የሆነ ነገር በመካከላቸው የሌለ እስከሆነ ድረስ፣ ይቅር ለመባባል በግንባር ቀደምትነት መቀመጥ ከሚገባቸው የጋራ መርሖዎች (የማስማሚያ ነጥቦች) በተጨማሪ፡- በቀጣይ መስተካከልና መታረም ያለባቸውን ቀሪ ዋና ዋና ነገሮች ርእሰ ጉዳይ አስቀድሞ ለይቶ በጥቅሉ በመያዝ፣ ከይቅር መባባሉ በኋላ በአደራዳሪዎች አማካኝነት በዝርዝር በመነጋገር እየፈቱ ለመሄድ፣ ከወዲሁ ሥርዓት ማበጀት አጋዥነት ያለው ነው፡፡ ርእሰ ጉዳያቸው በቅድሚያ ተመዝግቦ በቀጣይነት ለሚነሡ ነጥቦች ሁሉ፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዓት፣ ገዢነትና መሪነት ያለው በመሆኑ፤የዕርቀ ሰላሙ ሂደት የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያልሆነ፣ የግልም ሆነ የቡድን ፍላጐት፣ አቋምና አካሔድ ጥላ ሊያጠላበት የሚችል አይደለም፡፡ዋናው ነገርም ዕርቀ ሰላሙን አጽንቶ ለመሄድ፣ በልዩነቱ ጊዜ ውስጥ የተፈጠሩ መታረም፣መታየትና የጋራ መደረግ ያለባቸውን ሁኔታዎችና አሠራሮች፣ከሁሉም ወገን ሰብስቦ፣በአደራዳሪ ሽማግሌዎች አማካኝነት ቅቡልነት ያለው አቅጣጫ እንዲያዝባቸው ማድረግ ነው፡፡
ስለ ዕርቀ ሰላሙ አስፈላጊነት፣ የአፈጻጸም ቅደም ተከተል፣ ስለ ምእመናንና የካህናት ድርሻ፣ በደንብ ታስቦበት በተዘጋጀ ሁኔታ፣ በየጊዜው በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ሂደቱ ስለሚገኝበት ደረጃ መግለጫዎችንና መረጃዎችን መስጠት፣ የዕርቀ ሰላም ኮሚቴው ተግባር ለውጤቱም አጋዥነት ያለው ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሁለቱም ወገን ለመነጋገርና በመሃል ላይ ሆኖ ለማነጋገር የምንቀርብ አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችም፣ ከዚህ በፊት ተጀምረው የነበሩ ውይይቶች ውጤት ያላመጡት ለምንድን ነው? በሁለቱም ወገኖች አቀራረብ ላይ የነበረው ጠንካራና ደካማ ጐን ምን ነበር? አሁን በቀጣይ ለሚደረገው ምክክር፣ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት መጠናከር ሲባል በእኔ/በእኛ በኩል፣ ተስተካክሎ መቅረብ የሚገባው አቋም ምንድን ነው? ብሎ በተለያዩ የአማራጭ አቅጣጫዎች አስቀድሞ በግልና በቡድን ደረጃ ማየት፣ መዘጋጀትና መሥራት አስፈላጊ ነው፡፡
ሰላመ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፣ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ሲል ትልቅ ዋጋ የከፈለበት ሀብተ ክርስትናችን ስለሆነ፣ የምናጸናው አባቶችና ምእመናን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ህልውና በእውነት በመትጋት በአንድነት ሆነን እንደየድርሻችን አገልግሎቷን ስንፈጽም ነውና፤ ዕርቀ ሰላሙ ጊዜ የሚሰጠው አይደለም፡፡ በተለይም መለያየትን መግቢያ ቀዳዳው በማድረግ ጠላት ዲያብሎስ የራሱን ተልዕኮ ለመፈጸምና ለማስፈጸም ወደ ኋላ አይልምና፤ ዕርቀ ሰላሙን ዳር ለማድረስ ባለፉት ዓመታት ውጤታማ መሆን ባይቻልም፤ ከሚመጣው 2ዐ11 ዓ.ም. መቅደም መቻል ብልህነት ነው፡፡ ስለሆነም ኅብረታችን የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ከሚያፋጥኑ ጋር እንጂ፤ በውስጧ ሆነው ከሚቦረቡሯት የተሐድሶ መናፍቃን ጋር አይደለምና፤ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር፣ ሐዋርያዊ አገልግሎቷን፣ አንድነቷንና ዐቅሟን ለማጠናከር የሚረዱ ነገሮችን ለመፈጸም፣ ኃይለ እግዚአብሔርን አጋዥ አድርጐ መንቀሳቀስ ዘመኑን መዋጀት ነው፡፡
የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነትና ዐቅም እንዲጠናከር በተቻለው መጠን እየሠራ ያለው ማኅበረ ቅዱሳንም፣ በአባቶች መካከል ተፈጥሮ መፍትሔ ሳይሰጠው የቆየው መለያየት፣ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አይጠቅምም በማለት አቋሙን ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ለምሳሌም በሐመር መጽሔት ላይ ብቻ ካስተላለፋቸው መልእክቶች መካከል፣ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ከወጡት ላይ የተወሰኑትን ብንመለከት፡- በ1999 ዓ.ም. ሐመር 15ኛ ዓመት ቁጥር 1 የጥርና የካቲት ዕትም ላይ፣ ከቅርብ ዓመታት በፊት በ2ዐዐ5 ዓ.ም. ላይ ደግሞ በሐመር 2ዐኛ ዓመት ቁጥር 5 መስከረም ወር ዕትም ላይ «ለቤተ ክርስቲያናችን አንድነት፣ ዕርቅና ሰላም መሠረት ናቸው» በሚል ርእስ እንዲሁም በሐመር 2ዐኛ ዓመት ቁጥር 6 የጥቅምት ወር ዕትም ላይ፡- ወቅቱ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው ምክንያት በምትካቸው ሌላ ፓትርያርክ ለመሾም ጥረት እየተደረገበት የነበረ ጊዜ በመሆኑ «ከሁሉም ነገር በፊት ዕርቀ ሰላም፣ ማሠራቱ የተረጋገጠለት ሕገ ቤተክርስቲያንና የምርጫ መመሪያ ያስፈልጋል» በማለት መልእክት አስተላልፏል፡፡ አሁንም ቢሆን ማኅበሩ ዕርቀ ሰላሙ የተሳካ እንዲሆን ጽኑ የሆነ ፍላጐት ያለው ስለሆነ፤ የሚችለውን ድጋፍ ለማድረግና በአባቶች የሚታዘዘውን በዐቅሙ ለመፈጸም ዝግጁ መሆኑን ይገልጻል፡፡
በአጠቃላይም፡-
1. የዕርቀ ሰላሙ ድርድር የሚጀመረው በጸሎትና በአባቶች ቡራኬ በመሆኑ፤ ሕዝበ ክርስቲያኑም መለያየቱ ዓመታትን በመውሰዱ ላይ እያዘነ ስለሆነ፤ የሚታረቁና የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው ተብሎ በተጻፈው መሠረት እኛ ፈቃደኞችና ቁርጠኞች እስከሆን ድረስ፣ ፈቃደ እግዚአብሔር የማይለየን ስለሆነ፣ ዕርቀ ሰላሙ ይሳካል ብሎ በሙሉ ልብ መጀመር፡፡
2. ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለሀገሪቱ ሰላምና አንድነት ብዙ እንዳላበረከተች ሁሉ፤ አጀንዳ ሁኖ የሚገኘውን ይህን የራሷን ጉዳይ ሳትፈታ መቆየቷ፣ የሰላም ባለቤት የሆነውን እግዚአብሔር የማያስደስት፣ ያላትን ክብርና ዝና ዝቅ የሚያደርገው ስለሆነ፤ በሀገራችን ውስጥ ሲንፀባረቅ ለቆየው የመለያየት መንፈስ፣ እኛም በየፊናችን አስተዋጽኦ አላደረግንም ወይ? ብሎ ራስ ራስን መጠየቅ፡፡
3. ዕርቀ ሰላሙ፣ በውጭ ሀገርና በሀገር ውስጥ ባለው ሕዝበ ክርስቲያን በጉጉት የሚጠበቅ ቢሆንም፤ ከዚህ በፊትም ከ2 ጊዜ በላይ የተደረጉ ጥረቶች ውጤታቸው እና ችግራቸው ምን እንደሆነ ሳይታወቅ እንዲሁ የቀረ ነው፤ በመሆኑም በፊታችን ሐምሌ 2010 ዓ.ም ባለው ድርድር፣ ዕርቀ ሰላም ላይ፣ መድረስ አለመቻል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ዕርቅና ሰላም የከፈለልንን ዋጋ እንደቀላል ማየት ነው ብሎ በማመን፣ ዕርቀ ሰላሙ ሳይቋጭ ከተያዘው የድርድር ጊዜ (ሐምሌ 2010 ዓ.ም) ማለፍ የለበትም ብሎ መነሣት፡፡
4. ዕርቀ ሰላሙ፡- ሙሉ ለሙሉ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ በመሆኑ፣ ከቅድስት ቤተክርስቲያን ጥቅም አንፃር የሚታይና የሚመዘን እንጂ፣ በጉዳዩ ዙሪያ ካሉ፣ የግል ፍላጐቶች፣ አመለካከቶችና አቋሞች አንፃር እንዲመራ የሚተው አለመሆኑን ማመንና መቀበል፡፡ “ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር” እንዲል በዚህ ወቅት ሁሉም ሰው ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መነሣቱ እውነትም የይቅርታና የሰላም መምጫ ጊዜው ደርሶ ነው ብሎ በቅንነት መነሣት ይገባል፡፡
5. በአባቶች መካከል ለድርድር የሚቀርቡ ሐሳቦች እና ድርድሩ የሚመራበት መንገድና ስልት፣ ለቅድስት ቤተክርስቲያን ጠቃሚ የሆነ ነገር ማስገኘት የሚችል መሆኑን ማረጋገጥ ስለሚገባ፤ የተሻለውን እየተስማሙ መምረጥና መያዝ፣ ጥሩ መነሻ የሌለውን ሐሳብ ከዚህ ወገን ከዚያ ወገን የመጣ ነው ሳይባል፣ ከላይ በተራ ቁጥር 4 ከተገለጸው አኳያ ገንቢ የሆኑ ሐሳቦችና አቅጣጫዎች እየቀረቡበት፣ ግትር ሳይሆኑ፣ በሁሉም የባለቤትነት ስሜት እንዲዳብር፣ ነፃ ሆኖ መቀበልና ማንሸራሸር፡፡
6. በሁለቱም ወገን ተደራዳሪ የሚሆኑ አባቶች፣ በድርድሩ ላይ የሚነሱ ሐሳቦችና የማስማሚያ ነጥቦች ቅቡልነት ያላቸው መሆኑን በማረጋገጥ ይሁንታ የሚሰጡት፤ ከላይ በተራ ቁጥር 4 ላይ ከተገለጸው ዓላማ አንጻር እንጂ፣ ሲንፀባረቅ ከቆየና ቀደም ብሎ ከተያዘ አቋም አኳያ ጽንፍ በመያዝ እንዳይሆን ራስን መፈተሽ፡፡
7. ውጭ ሀገርም ሆነ ሀገር ውስጥ ያለው ሕዝበ ክርስቲያን ዕርቀ ሰላሙን በጉጉት የሚጠብቀው ስለሆነ፤ መስማማት ያልተቻለባቸውን ነጥቦች አደራዳሪዎች ለይተውና ቀርፀው በማቅረብ ላለመስማማት የተያዙትን አቋሞች ያንፀባረቋቸው ወገኖች፣ የገለጿቸውና የእነሱ መሆናቸውን በቅድሚያ እንዲያረጋግጡ በማድረግ፣ እነዚህን ነገሮች (ልዩነቶች) በሚዲያ ምእመኑ እንዲያውቃቸው በማድረግ ምእመናን ልዩነቱ እንዲፈታ የድርሻቸውን እንዲወጡ ማድረግ፡፡
8. ስምምነት ሂደት በመሆኑ፤ ድርድርና ብዙ ጊዜ በማይወስዱ ዋና ዋና በሆኑ ጉዳዮች ላይ ዕርቀ ሰላም ለመፍጠር የሚያስችሉ ግንባር ቀደም የሆኑ ነጥቦችን ለይቶ መስማማት፡፡ ከዚህ በመቀጠልም በአደራዳሪዎች አማካኝነት በቀጣይ ሊታዩ የሚገባቸውን ርእሰ ጉዳዮች ዝርዝርና የሚታዩበትን ሁኔታ አቅጣጫ ማስቀመጥ፡፡
9. በማንኛውም ደረጃ የሚገኙ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባቶችና ምእመናን፤ ለዕርቀ ሰላሙ መሳካት እግዚአብሔርን በጸሎት እየጠየቁ፣ አስፈላጊውን ዕገዛና ድጋፍ ማድረግ፡፡ አደራዳሪዎችና ሚዲያዎችም ለሕዝበ ክርስቲያኑ መድረስና መታወቅ ያለበትን መረጃ አስፈላጊነቱን በማየት ሳይዛባ በወቅቱ ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ፡፡ አጋዥና ወሳኝነት ያለው ስለሆነ«አባቶች ዕርቀ ሰላምን በመፍጠር፤ ለቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎትና ለሀገራዊ መግባባት ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ ይገባል!» በማለት ማኅበሩ መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፤ሐመር መጽሔት 26ኛ ዓመት ቁጥር 2 ሰኔ 2010 ዓ.ም