የአሰቦት ገዳም ደን ዳግም ቃጠሎ
መጋቢት 3/2004 ዓ.ም
በእንዳለ ደምስስ
የአሰቦት ገዳም ደን ዳግም በመቃጠል ላይ ይገኛል፡፡ ከመጋቢት 2/2004 ዓ.ም.ከቀኑ አሥር ሠዐት ጀምሮ መነሻው ባልታወቀ ምክንያት ቃጠሎው በአዲስ መልክ እንደተቀሰቀሰ የገዳሙ ማኅበረ መነኮሳት ገልጸዋል፡፡
ከገዳሙ መነኮሳት በደረሰን የድረሱልን ጥሪ መሰረት እሳቱን ለማጥፋት ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ በመግለጽ የሚመለከተው አካል አስቸኳይ መፍትሔ እንዲፈልግላቸው በመማጸን ላይ ይገኛሉ፡፡ ከቀኑ አሥር ሠዐት የጀመረው ቃጠሎ በአባ ሳሙኤል ገዳም አቅጣጫ ሲሆን ከፍተኛ የደን ሀብት የያዘና ብዛት ያላቸው የዱር እንስሳትና አእዋፍ የሚገኙበት ነው፡፡ እንዲሁም ራሣቸውን ለእግዚአብሔር አሳልፈው የሰጡ መናንያን ስለ ሀገርና ወገን ዘግተው የሚጸልዩበት ቦታ እንደሆነ መነኮሳቱ ያስረዳሉ፡፡ ይህንን የደን ሀብት ከቃጠሎው ለመታደግ ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት፤ ለወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፤ ለፖሊስና ለፌደራል ፖሊስና ለምእመናን የድረሱልን ጥሪ በማሰማት አሳቱን ለማጥፋት የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ቃጠሎውን በቁጥጥር ሥር ለማድረግ እንዳልተቻላቸውና ወደ አባ ሳሙኤል ገዳም በመገስገስ በ100 /አንድ መቶ/ ሜትር ርቀት ላይ እንደደረሰ የገዳሙ መጋቢና ም/አበምኔት አባ ዘወልደ ማርያም በሀዘን ገልጸዋል፡፡ የቃጠሎው መባባስ ስጋት ውስጥ የከተታቸው መሆኑንና በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ጽላቱን ለማውጣት እንደሚገደዱ በመግለጽ የድረሱልን ጥሪያቸውን በማሰማት ላይ ናቸው፡፡
የገዳሙ አበምኔት አባ ተክለ ማርያም በአሁኑ ወቅት ለመንገዱ ሥራና በደኑ ቃጠሎ ዙሪያ መፍትሔ እንዲፈለግለት በተለይም መንግስት ጥበቃ እንዲመድብ አቤቱታ ለማቅረብ አዲስ አበባ ይገኛሉ፡፡ ከቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን የገለጹት አበምኔቱ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ እንደሚያሳውቁና በጥበቃ ዙሪያ ያለውን ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚፈታ ቅዱስነታቸው ቃል ገብተውልናል ብለዋል፡፡
የአሰቦት ገዳም ደን ከየካቲት 20 እስከ የካቲት 24/2004 ዓ.ም. ድረስ ሲቃጠል ቆይቶ በመነኮሳቱ፤ በፌደራል ፖሊስ፤ በኦሮሚያ ፖሊስና ምእመናን ከፍተኛ ተጋድሎ መጥፋቱ የታወሳል፡፡ አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ዳግም ቃጠሎው መቀስቀሱ እጅግ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡