የንሂሳው ኮከብ
ጥቅምት ፬፤፳፻፲፰ ዓ.ም.
በዐፄ ላሊበላ ዘመነ መንግሥት፣ ዐሥራ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ የመጡት ግብጻዊው ቅዱስ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የትውልድ ስፍራቸው በላዕላይ ግብጽ ንሂሳ እንደሆነ ገድላቸው ይጠቅሳል፡፡
አባታቸው ስምዖን እናታቸው አቅሌስያ የተባሉት ወላጆቻቸው እግዚአብሔርን የሚፈሩ ደጋግ ሰዎች እንደነበሩ ሆኖም ልጅ አጥተው ፴ (ሠላሳ) ዘመን ሲያዝኑ መኖራቸውንም ታሪካቸው ያነሣል፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀንም እናታቸው አቅሌሲያ ቤተ እግዚአብሔር ገብታ ከሥዕለ ሥላሴ ሥር ወድቃ ስትማጸን ክብሩ ከሰማይ ከፍታ የሚበጥ ልጅ እንኪ ተቀበይ የሚል ድምጽ ሰማች፡፡ ‹‹ሥልጣኑ ከሰማይ ከፍታ ከፍ የሚል ንጽሕናው ከሚካኤል ከገብርኤል የሚተካከል ክህነቱ እንደ መልከጼዴቅ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ እንደ ነቢይ ኤልያስ የሆነ ልጅ እንቺ ተቀበይ›› አላት፡፡ አቅሌስያም በመጋቢት ፳፱ ቀን ፀንሳ በታኅሣሥ ፳፱ ቀን ደም ግባቱ እጅግ የሚያምር ወንድ ልጅ እንደወለደች መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በሰው አምሳል መጥቶ ‹‹የዚህ ልጅሽ ስሙ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ይሁን›› አላት፡፡ ወዲያውም ሕፃኑ ተነሥቶ ከእናቱ ጭን ወርዶ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ሦስት ጊዜ ሰገደ፡፡ ዳግመኛም ‹‹ከጨለማ ወደ ብርሃን ለአወጣኸኝ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን›› አለ፡፡
አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የተፀነሱት መጋቢት ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን፣ የተወለዱት ደግሞ ታኀሣሥ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ነው፡፡ አባታችን ዓይን በገለጡ ጊዜ ከሚታይ ነገር ላይ እንዲያርፍ እርሳቸውም በተወለዱ ጊዜ ተነሥተው «ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ ዘዓውፃእከኒ እምጽልመት ውስተ ብረሃን» ብለው አመስግነዋል። አባታችን ለአምላክ ሰግደው አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ካመሰገኑ በኋላ እናታቸው አላቀፈቻችውም፤ ጡትም አልጠቡም፡
ጻድቁ አባታችን አኗኗራቸው እንደ መላእክት በምድረ በዳ የነበር፣ በዝቋላ ተራራ ባለው ባሕር ውስጥ ፻ (መቶ) ዓመት ተዘቅዝቀው ለኢትዮጵያ ሰዎች ምሕረትን የለመኑና ምሕረትን ያሰጡ ቅዱስ ናቸው፡፡ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ከ፭፻ (አምስት መቶ ዓመታት) በላይ በዚህ ምድር ላይ መኖራቸውንና ከትግራይ እስከ ሸዋ ባለው ክፍል ተዘዋውረው ማስተማራቸውን ገድላቸው ያትታል፡፡ በዚህም ምክንያት ዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስንና ምድረ ከብድ ገዳማትን መትከላቸውን ታሪካቸው ያሳያል፡፡ ያረፉት በዐፄ ሕዝብ ናኝ ዘመን መጋቢት አምስት ቀን ነው፡፡ የምሕረት ቃልኪዳን የተቀበሉት ደግሞ ጥቅምት አምስት ቀን ነው፡፡ የከበረው በድነ ሥጋቸውም በምድረ ከብድ ይገኛል፡፡ ጻድቁ በትግራይ አቡዬ፣ በአማራው አቡነ፣ በኦሮሞዎች ዘንድ ደግሞ አቦ በመባል ይታወቃሉ፡፡
የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፤ በጸሎታቸው ይማረን!
ምንጭ፡ – ገድለ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ ተስፋ ገብረ ሥላሴ ፲፱፻፺፪ ዓ.ም