የኒቂያ ጉባኤ
መስከረም ፳፪፤፳፻፲፰ ዓ.ም.
የአርዮስ ክህደት በተስፋፋበት በ፫፻፳፭ ዓ.ም የእግዚአብሔር ወልድን የባሕርይ አምላክነት የማይቀበሉ መናፍቃን ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ጊዜውም ታላቁ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ‹‹አብያተ ጣዖታት ይትአጸዋ አብያተ ክርስቲያናት ይትረኀዋ፤ የጣዖታት ቤቶች ይዘጉ! አብያተ ክርስቲያናት ይከፈቱ!›› የሚል ዐዋጅ የነገረበት ስለነበር ንጉሡ በኒቅያ የሃይማኖት ጉባኤ እንዲካሄድ በየአገሩ ለነበሩ ሊቃውንት መልእክት አስተላለፈ፡፡
ከሚያዝያ ፳፩ ቀን ጀምሮ እስከ መስከረም ፳፩ ቀን ድረስ ፳፫፻፵፰ (ሁለት ሺሕ ሦስት መቶ ዐርባ ስምንት) ሊቃውንት በኒቅያ ተሰበሰቡ፡፡ ሊቃውንቱ በሱባኤና በጸሎት ከቆዩ እስከ ኅዳር ፱ ቀን በንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ሊቀ መንበርነት፣ በእለእስክንድሮስ አፈ ጉባኤነት ጉባኤው ተጀመረ፡፡ ንጉሡ ሊቃውንቱን ‹‹ስማችሁን፣ አገራችሁንና ሃይማኖታችሁን ጽፋችሁ ስጡኝ›› ባላቸው ጊዜም ከ፳፫፻፵፰ቱ መካከል ፫፻፲፰ (ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ) ሊቃውንት ሃይማኖታቸውን ሲገልጹ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው ‹‹ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ፤ ወልድ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኮት፣ በሥልጣን፣ በፈቃድ፣ በህልውና አንድ ነው›› ብለው ጽፈው ሰጡት፡፡ ንጉሡም ‹‹ሃይማኖት እንደ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት ይሁን›› ብሎ ዐዋጅ አስነግሯል፡፡ እነዚህ ሊቃውንት በኦሪት ዘፍጥረት የተጠቀሱት ፫፻፲፰ቱ የአብርሃም ብላቴኖች ምሳሌዎች ናቸው /ዘፍ.፲፬፥፲፬/፡፡
፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት በጉባኤው አርዮስን አውግዘው በመለየት ‹‹ነአምን በአሐዱ አምላክ፤ በአንድ አምላክ እናምናለን›› የሚለውን የሃይማኖት ጸሎት (የሃይማኖት መሠረት) እና ሌሎችንም የሃይማኖት ውሳኔዎችን ደንግገዋል፡፡
የቅዱሳን አባቶቻችን ጸሎት፣ አማላጅነትና ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን!