የነፋስ ነገር
መምህር ቢትወደድ ወርቁ
ኅዳር ፳፮ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
እግዚአብሔር ያለ ምክንያት የፈጠረው ፍጥረት የለምና ነፋስንም በምክንያት ፈጥሮታል፡፡ ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል፡፡ ቀን ለቀን ነገርን ታወጣለች፤ ሌሊትም ለሌሊት እውቀትን ትናገራለች” በማለት እንደዘመረው ሥነ ፍጥረት አእምሮ ላለው የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን ባሕርያዊ መገለጫዎች ሥራና ፈቃዳት ያስተምራሉ፡፡ (መዝ.፲፰፥፩) ሰውንም ሲፈጥረው ከዐራቱ ባሕርያተ ሥጋ አምስተኛ ባሕርየ ነፍስን አድርጎ በመልኩና በምሳሌው እንደፈጠረው የታወቀ ነው፡፡ (ዘፍ. ፩፥፳፮) እነዚህ አራቱ ባሕርያተ ሥጋ የሚባሉትም ነፋስ፣ እሳት፣ መሬትና ውኃ ናቸው፡፡ በሥነ ፍጥረት ትምህርት እግዚአብሔር ሰውን ከእነዚህ ዐራት ባሕርያት የፈጠረበት ምክንያት በምልዓትና በስፋት ይተነተናል፡፡ በዚህ አጠር ያለ ጽሑፋችንም ከነፋስ ምን እንማራለን? የሚለውን እናነሣለን፡፡
ነፋስና የእግዚአብሔር ፈታሒነት
በመጽሐፍ ቅዱስ “አምላክህ እግዚአብሔር የሚበላ እሳት ነው” ተብሎ እንደተጻፈ እሳትን የፈጠረ እግዚአብሔር በእሳት እንደተመሰለ እንዲሁ በሰው የነፋስ ባሕርይ የእግዚአብሔር ፈታሒነቱን እንረዳለን፡፡ (ዘዳ.፬፥፳፬) ገበሬ በነፋስ አማካኝነት ምርቱና ግርዱን ፍሬና ገለባውን ይለያል፡፡ እግዚአብሔርም በፈታሒነቱ (በሚዛናዊ ፍርዱ) ኃጥኣንን ከጻድቃን እውነተኞችን ከሐሰተኞች ርኩሳንን ከቅዱሳን ይለያል፡፡ (ማቴ.፫፥፲፪፣ማቴ.፳፭፥፴፪) እርሱ ኃጥኡን ጻድቅ ነህ፥ ሐሰተኛውን እውነተኛ ነህ፥ አይለውምና፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን “ኃጥእ እንደ ዐውሎ ነፋስ ኅልፈት ይጠፋል፤ ጻድቅ ግን ተሠውሮ ለዘለዓለም ይድናል” ማለቱም የእግዚአብሔር ፈታሒነቱ በዓውሎ ነፋስ እንደሚመሰል ያስተምረናል፡፡ (ምሳ.፲፥፳፭)
ነፋስና የሰው አፈጣጠር
ሰው ከነፋስ የተፈጠረ ነውና ከነፋስ ጋር የሚያመሳስል ባሕርያት አሉት፡፡ ነፋስ ተንቀሳቃሽ እንደሆነ እንዲሁ የሰው ልጅም የነፋስ ተፈጥሮ አለውና ይንቀሳቀሳል፡፡ ከእግዚአብሔርም የተሰጠው የሕይወት እስትንፋስ አለው፡፡ ከዚህም ባሻገር የሰው የሕፃንነት ወራቱ በነፋስ ይመሰላል፡፡ ነፋስ በአንድ ስፍራ እንደማይረጋ ሕፃናትም ባስቀመጡአቸው ረግተው አይገኙም፡፡ ነፋስ ፈጣን እንደሆነ ሕፃናትም ፈጣኖች ናቸው፡፡
ነፋስና በጥምቀት ያገኘነው የጸጋ ልጅነት
የነፋስ መልኩ አለመታየቱ፣ ከየት መጥቶ ወዴት እንደሚሄድ አቅጣጫው አለመታወቁና አለመመርመሩ ክርስቲያኖች በጥምቀት አማካኝነት ያገኙት የልጅነት ጸጋ እንደማይመረመርና ልመርምረው ቢሉም እንደማይደረስበት ያመለክተናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማታ ተማሪ ኒቆዲሞስን ስለ ጥምቀት “እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” በማለት ካስተማረው በኋላ ይህን ረቂቅ ምሥጢር በእምነት ሊቀበሉት እንጂ በሥጋ መንገድ ሊመረምሩት እንደማይገባ ሲያስተምረው “ነፋስ ወደወደደው ይነፍሳል፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ከየት እንደመጣ ወዴትም እንደሚሄድ አታውቅም፤ ከእግዚአብሔርም የተወለደ እንዲህ ነው” ብሎታል፡፡ (ዮሐ.፫፥፭) ነፋስን እንከተል ብንል በየት አቅጣጫ እንከተለዋለን? ምንስ እንጠቀማለን? ከእግዚአብሔር በጥምቀት አማካኝነት ያገኘነውንም ጸጋ በእምነት ብንቀበል እንጠቀማለን እንጂ እንዴት ብለን ብንመረምር አንዳች አንጠቀምም፤ እንመርምረው ብንልም አንደርስበትም፡፡
ነፋስና የኀልዮ (የሐሳብ) ኃጢአት
የሰውን ልጅ ከእግዚአብሔር መንግሥት ውጪ የሚያደርገው ወደ ነቢብና (መናገር) ወደ ገቢር የሚወስደው የክፉ ሐሳብ ፈተናም በነፋስ ተመስሏል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአንቀጸ ብፁዓን በተራራው ስብከቱ “ይሄን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዐለት ላይ የሠራ ብልህ ሰውን ይመስላል፡፡ ዝናም ዘነመ፤ ጎርፍም ጎረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ያንም ቤት ገፉት፤ ነገር ግን አልወደቀም፤ በዐለት ላይም ተመሥርቷልና፡፡ ይህንም ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል፡፡ ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ያንም ቤት መታው፤ ወደቀም፤ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ፡፡” (ማቴ.፯፥፳፬-፳፯) ጌታችን በዚህ ትምህርቱ ቤት ብሎ የጠራው የእያንዳንዳችንን ቤተ ልቡና ነው፡፡
ሁለት ዓይነት ልቡና ያላቸው ሰዎች እንዳሉና እንደሚኖሩም አስተማረን፡፡ በዓለትና በአሸዋ የተመሠረቱ፣ በዓለት የተመሠቱ የተባሉት እርሱን ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው በተዋሕዶ የከበረ የባሕርይ አምላክ ብለው በማመን ዐለት በተባለ ቅዱስ ጴጥሮስ በመሰከረው እምነት ያሉት ናቸው፡፡ (ማቴ.፲፮፥፲፮-፲፱) ቤታቸውን በዓለት ላይ የመሠረቱ ማለትም “በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ ታንፃችኋል፤ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” ተብሎ እንደተነገረ በነቢያትና በሐዋርያት እምነት ጸንቶ የሚኖር ማለት ነው፡፡ (ኤፌ.፪፥፲፱-፳) እነዚህ አማኞች ላይ ዝናብ ወረደ፤ ጎርፍም መጣ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ በቅዱሳን እምነት ላይ ተመሥርተዋልና አልወደቁም፡፡ በዚህ የመጽሐፍ ክፍል በነፋስ የተመሰለው ምንድነው? ስንል ሊቃውንቱ በትርጓሜያቸው መከራና ፈተና ሲገጥመን “እግዚአብሔርን ካድ፤ እርሱን ስደብ፤ የምታመልከው አምላክህ ከዚህ አያድንህም” የሚሉ ክፉና ረቂቅ ሐሳቦችን በኅሊናችን የሚያመጡ አጋንንት ናቸው” በማለት አስቀምጠውልናል፡፡ (ትርጓሜ ወንጌል ገጽ ፺፭)
ጻድቁ ኢዮብ በእንዲህ ዓይነት ፈተና ተፈትኖ ነበር፤ ሰይጣን በሚስቱ አድሮ በዚህ መንገድ ሸንግሎ ድል ሊነሣው እንደሞከረ በመጽሐፍ ተጽፎልናል፡፡ እርሱ በጽኑ ዓለት ላይ ተመሥርቶ ነበርና ይህን ፈተና ድል ነሣው፡፡ (ያዕ.፭፥፲፫-፲፮) ቅዱስ ጳውሎስ “የሰይጣንን ተንኰል መቋቋም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ጋሻ ልበሱ” በማለት የመከረንም ሰይጣን እንደ ነፋስ የረቀቀ ሐሳቦችን እያመጣና እየሸነገለ ስለሚፈትነን ነው፡፡ (ኤፌ.፮፥፲፩) እግዚአብሔር “ስጠኝ” ያላቸውን ልቡናቸውን በጥርጥር በተመሰለ በአሸዋ ላይ የመሠረቱ ሰዎች ግን ቃሉን እንኳን ቢሰሙ ሰይጣን በኅሊናቸው የሚያመጣውን ክፉ ሐሳብ ወደ ንግግርና ወደ ገቢር እየለወጡ ታላቅ አወዳደቅን ይወድቃሉ፡፡
ሰይጣን ኃጢአት እንድንሠራ ያመቻቻል እንጂ አያስገድደንም፡፡ በመሆኑም ቅዱስ ያዕቆብ “የሚፈተን ሰው ቢኖር እግዚአብሔር ይፈትነኛል አይበል፤ እግዚአብሔር ለክፉ ነገር አይፈትንምና፤ እርሱስ ማንንም አይፈትንም፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል፡፡ ምኞትም ከፀነሰች ኃጢአትን ትወልዳታለች፤ ኃጢአትም ከተፈጸመች ሞትን ትወልዳታለች” በማለት እንደ ነፋስ የረቀቁና የሚፈጥኑ ክፉ ሐሳቦችን ወደ ተግባር ለውጠን ፈተና ውስጥ እንዳንገባ በእውነት አስጠነቀቀን፡፡ (ያዕ.፩፥፲፫-፲፭) ነፋስ የዚህ ዓለምን ክብር የሚሹ መምህራንን በሚወስድ ውዳሴ ከንቱም ይመሰላል፡፡
ቅዱስ ይሁዳ “እንደ እረኞች ያለ ፍርሃት ራሳቸውን ይጠብቃሉ፤ በነፋስ የተወሰዱ ውኃ የሌለባቸው ደመናዎች ፍሬ የማያፈሩ ሁለት ጊዜ የሞቱ ከነሥራቸው የተነቀሉ በበጋ የደረቁ ዛፎች” በማለት ተናግሯል (ይሁዳ ፩፥፲፪)፡፡ ኃይለኛ ነፋስ ከባድ የሚባሉ ነገሮችን እያንከባለለና እየገለባበጠ እንደሚወስድ፣ ጣሪያ እንደሚገነጥል፣ ዛፍ እንደሚያናውጥ የዚህ ዓለም ውዳሴ ከንቱም ታላላቅ ተብለው የሚጠሩ መምህራንን ሳይቀር ከመሠረታቸው ክርስትና ነቅሎ ለክፉ ሰይጣን የዓለምና የሥጋ ፈቃዳቸውም አሳልፎ ይሰጣቸዋል፡፡
ይቆየን!