የነነዌ ጦም (ለሕፃናት)
ጥር 29/2004 ዓ.ም
አንድ ቀን እግዚአብሔር ዮናስ ወደ ተባለ ሰው መጥቶ “ተነሥተህ ወደ ነነዌ ከተማ ሒድ፤ ሕዝቡ ኀጢአት ስለሠሩ ልቀጣቸው ነው፡፡ ነገር ግን አንተ ሔደህ ካስተማርካቸው እና እነሱም ከጥፋታቸው ከተመለሱ እምራቸዋለሁ፡፡” አለው ዮናስ ግን ወደ እነርሱ ሔዶ እግዚአብሔር የነገረውን ቢነግራቸው ይጎዱኛል ብሎ አሰበ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ያዘዘውን መልእክት ላይናገር ወስኖ ተርሴስ ወደምትባል ሀገር ለመሸሽ ፈለገ፡፡ እግዚአብሔር እርሱን ፈልጎ እንደማያገኘውም አሰበ፡፡ ነገር ግን ማንም ከእግዚአብሔር መሸሽ አይችልም፡፡ ዮናስ ግን ይህን አላወቀም ነበር፡፡
ዮናስ በመርከቧ ላይ ሳለ ከባድ አውሎ ነፋስ ተነሣ፡፡ የመርከቧ ተሳፋሪዎች በሙሉ ተጨነቁ መርከቧ ከተገለበጠች እንዳይሞቱ አሰቡና እግዚአብሔር እንዲረዳቸው ጸለዩ፡፡ ዮናስ ግን ከእግዚአብሔር ሸሽቶ መምጣቱን አሰበ እሱን ወደ ውኃው ቢወረውሩት አውሎ ንፋሱ እንደሚቆም ነገራቸው፡፡ ሰዎቹ በጣም አዘኑ ነገር ግን መርከቧ እንዳትሰምጥባቸው ዮናስን ወደ ባሕሩ ወረወሩት፡፡ ዮናስ በውኃው ውስጥ እንዲሞት ግን እግዚአብሔር አልተወውም፡፡ ዮናስን ሳይጎዳው እንዲውጠው ዓሣ አንበሪ ላከ፡፡ ከሦስት ቀን በኋላ ዓሣ አንበሪው እየዋኘ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ወጥቶ ዮናስን ተፋው፡፡ ከተፋው በኋላ እግዚአብሔር ዮናስ ወደ ነነዌ ሔዶ እንዲያስተምራቸው በድጋሚ ነገረው፡፡ ዮናስም ወደ ነነዌ ሔደ እግዚአብሔር የነገረውን ነገራቸው፡፡ ሰዎቹም ሰሙት፡፡ በነነዌ የነገሠው ንጉሥ የዮናስን ትምህርት በሰማ ጊዜ ሕዝቡን ሁሉ ሰበሰበ፡፡ ሕፃን፣ ሽማግሌ ሳይሉ እንስሳትም ሳይቀሩ ለሦስት ቀን እንዲጦሙ እና እንዲጸልዩ አዘዘ፡፡ ሕዝቡም ሁሉም ሦስት ቀን ጦሙ ጸለዩ፡፡ እግዚአብሔርም ሕዝቡ በጥፋታቸው ስለተጸጸቱ እና ስለጦሙ ከጥፋት አዳናቸው፡፡
ከታሪኩ የምንረዳው፡-
- ጦም እና ጸሎት ሊደርስብን ከሚችለው መከራ እና ችግር እንደሚያድን
- እግዚአብሔር በሁሉም ቦታ እንዳለ እና በየትም ቦታ ብንሆን የምንሠራውን ሉ እንደሚመለከተን ያስረዳል፡፡