የነነዌ ሰዎች እምነት ንስሓና የጾም አዋጅ

 

መ/ር ቢትወደድ ወርቁ

ትንቢተ ዮናስ አራት ምዕራፎች ያሉት፤ እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚነሣ ትውልድ ሁሉ ሊማርበትና ራሱን ሊያስተካክልበት የተጻፈ ታላቅ የትንቢት መጽሐፍ ነው፡፡ በዚህ የነቢዩ ዮናስ መጽሐፍ የተጠቀሱት ነቢዩ ዮናስን ጨምሮ የነነዌ ሰዎች ፣ንጉሡ ፣ዮናስ በየዋህነት ከእግዚአብሔር ፊት ወደ ተርሴስ ሊኮበልልበት የተሳፈረበት መርከብ ባለቤቶች /መርከበኞች/ እና ሌሎች ፍጥረታት ዓሣ አንበሪው፣የባሕር ማዕበሉ፣እግዚአብሔር ነቢዩ ዮናስን ያስተማረበት ትልና ቅሉ ሁሉ የነነዌ ሰዎች በኃጢአት ምክንያት ከመጣባቸው የጥፋት ዋዜማ አንስቶ ከኃጢአት ተመልሰው መዓቱ በምሕረት ቊጣው በትዕግሥት እሰከ ተለወጠላቸውና ከቅጣቱም እስከዳኑበት ጊዜ ድረስ የነበራቸው ተግባርና እግዚአብሔር የሠራላቸው የቸርነት ሥራዎች የተገለጡበት መጽሐፍ ነው፡፡

  መጽሐፉም እያንዳንዱ ቢዘረዘር ትልቅ መጽሐፍም ሊወጣው የሚችል ከመሆኑ አንጻር ያን ወደ ቤተክርስቲያን መጥተን ሊቃውንቱንና መምህራንን በመጠየቅ እንዲሁም ሌሎች ምሥጢራትን የሚያብራሩ  ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ መረዳት እንችላለን፡፡ አሁን ግን ባለንበት ወቅት በግላዊ፤ ቤተሰባዊና ሀገራዊ አኗኗራችን ከገባንበትና ሊገጥመን ከሚችሉ ችግሮች አንጻር የነነዌ ሰዎችን ታሪክ መስተዋት አድርገን ራሳችንን እንመለከትበት ዘንድ ታሪካቸውን በአጭሩ መቃኘትና የንስሓ መንገዳቸውን መከተል ተገቢ ይሆናል ፡፡ በመጽሐፍ ያለው ታሪክ በሙሉ የተጻፈልን ለፍጹም ትምህርትና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀን እንሆን ዘንድ እንዲሁም ለተግሣጽ ልባችንንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ጥበብ ይጠቅማልና (፪ጢሞ ፫÷፲፮-፲፯)

                የነነዌ ሰዎች የጥፋት ዋዜማ

ለነነዌ ሰዎችና ለከተማይቱ ጥፋት ምክንያት ሊሆን የነበረው  ምን እንደነበር መጽሐፍ ሲነግረን “የእግዚአብሔር ቃል ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ እንዲህ ሲል መጣ፤ ተነሥተህ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፤ ክፋታቸውም ወደፊቴ ወጥቶአልና፤ በእርሷ ላይ ስበክ”(ዮናስ ፩÷፪ )ይላል፡፡ የነነዌን ከተማ “ታላቂቱ ከተማ” ያሰኛት ብልፅግናዋና እድገቷ ብቻ ሳይሆን በሥሯ የነበሩ ሰዎች ይፈጽሙ የነበረው ታላቅ ክፋት ነበር፡፡ስለዚህም የነዋሪዎቿ ክፋት እግዚአብሔርን አሳዝኖት ከክፋታቸው እንዲመለሱ የክፋት ሥራቸውን እንዲተውና ንስሓ እንዲገቡ ይነግራቸው ዘንድ ነቢዩ ዮናስን ወደ እነርሱ እንዲሄድ ላከው ፡፡ ባዕድ አምልኮትንና ጣዖትን ማስፈን፤ ለጣዖታት መስገድና መሠዋት ፣ ጥንቆላን ማስፋፋት ፣ሥር እየማሱ ቅጠል እየበጠሱ የሰዎችን አኗኗር ማጎሳቆልና ማዘበራረቅ ፣በዘፈንና አስረሽ ምችው ሰክሮ ዝሙትንና ሌሎች የሥጋ ፈቃዳትን በራስና በሌሎች ላይ ማንገሥ ነው፤ (ገላ ፭÷፲፯-፲፱)፡፡  የኃጢአት ሥራ  ከእግዚአብሔር ይልቅ ደስታና ተድላን በመውደድ ለዚያም በሰዎች መካከል ጠብን ከመዝራትና እንዲጋጩ ከማድረግ አንስቶ የራስን ጥቅም ብቻ በመመልከትም ማታለልን ሰዎች የሚጠፉበትንም መንገድ መቀየስና ለዚያም ቀንና ሌሊት በመትጋት ወደ ፍጻሜ ማድረስ ነው፤(ምሳ ፮÷፲፮-፲፱)፡፡ ክፉ ሰዎች የሚጠፉበትንና እግዚአብሔር የሚያሳዝኑበትን ሐሳብ ንግግርና ተግባራትን አጠቃሎ ይይዛል፡፡

   ክፋትንም የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር  ዘንድ የተጠላ ነው፤ ዘዳ ፳፭÷፲፭፡፡  የነነዌ ሰዎችንም ለጥፋት ያቀረባቸውና ከተማይቱንም “በሦስት ቀን ውስጥ ትገለበጣለች” (ዮናስ ፫÷፬) እስከ መባል ያደረሳት ክፋታቸው ነው፡፡ ሰው ልቡናውን ከክፋት ካላራቀ ራሱም ይጠፋል፡፡ ክፋቱም በዙሪያው ላሉት ሁሉ ተርፎ ሌላ ጥፋትን ይወልዳል ፡፡ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በቀድሞው ዘመን ለእስራኤል ዘሥጋ ” ኢየሩሳሌም ሆይ ትድኚ ዘንድ ልብሽን ከክፉ ነገር እጠቢ”፤ (ኤር ፬÷፲፬ ) ማለቱም ለዚህ ነው፡፡ ዛሬም ከራሳችን አንስቶ ዙሪያችንን ስንመለከት እግሮቻችን ወደ ክፋት የሚሮጡ፤ እጆቻችንም ደምን ለማፍሰስ የሚፋጠኑና በራሳችንም የክፋት ሐሳብ እየተራቀቅን ጠቢባን ሆነናል የምንል ሰዎች በዝተናል (ምሳ ፩÷፲፮)፡፡ ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት እንደተናገረውም “ከኃጢአታችን ተመልሰን ንስሓ ካልገባን ክፋታችን ይገድለናል”፤(መዝ ፴፫÷፳፩)፡፡ የነነዌ ሰዎች ጥፋታቸው እስኪነገራቸው ድረስ በኃጢአት ሥራ ጸንተው ይኖሩ እንደ ነበር፤ ዛሬም በክፉ ሐሳብ ንግግርና ተግባር ላይ ካለን እኛም በጥፋት ዋዜማ ላይ እንደሆን ልንረዳ ይገባናል ፡፡

                  የእግዚአብሔር ቸርነትና የንስሓ ጥሪ

የነነዌ ሰዎች በመጥፎ ምግባራቸውና ኃጢአታቸው ምክንያት ሊጠፉ ሲገባቸው የቸርነት ባለቤት አምላካችን እግዚአብሔር እንዳይጠፉ በነቢዩ ዮናስ አንደበት የቸርነቱን የንስሓ ጥሪ አሰምቷቸዋል፡፡ “ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፤ የምነግርህንም ስብከት ስበክላት”(ዮናስ ፫÷፪) እንዲል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን እኛ ከኃጢአታችን ከተመለስን ከስሕተታችን ተምረን ለመታረምና ሕይወታችንን ለማስተካከል ከፈቀድን እንደ ወጣችሁ፤ እንደ ጠፋችሁና እንደ ረከሳችሁ ቅሩ አይልም፡፡ በበደላችንና በኃጢአታችን ካሳዘነው ይልቅ በኃዘንና በጸሎት ፍጹም በሆነ ንስሓ ከተመለስን ይደሰታል፡፡ እርሱ ብቻ ሳይሆን ቅዱሳን መላእክቱም በሰማይ ይደሰታሉ፤ “ንስሓ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ ምክንያት በሰማይ መላእክት ዘንድ ታላቅ ደስታ ይሆናልና”(ሉቃ ፲፭÷፲) እንደተባለ፡፡ ስለሆነም ዛሬም በገባንበት የጥፋት መንገድ ፣ ተመቻችተንና ተደላድለን እየኖርን ካለንበት የኃጢአት መንደር በመውጣት ንስሓ በመግባት ሰላማዊ አኗኗርንና መንግሥተ ሰማያትን ገንዘብ እንድናደርግ ያስተምረናል ፡፡ “ንስሓ ግቡ፤ ኃጢአትም እንቅፋት እንዳይሆንባችሁ ከኃጢአታችሁ ተመለሱ፤ የበደላችሁትን በደል ሁሉ ከእናንተ ጣሉ፤ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስም ለእናንተ አድርጉ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ ስለምን ትሞታላችሁ ? የሟቹን ሞት አልፈቅድምና ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ” (ሕዝ ፲፰÷፴-፴፪ )እንዲል፡፡ዛሬም ቢሆን በኃጢአት እየኖርን የሚታገሠን ንስሓ እንድንገባ ነው፤ (፪ጴጥ ፫÷፱) ንስሓ ካልገባንም ቅጣት መምጣቱ የማይቀር መሆኑን ልብ ማለት ይገባናል፤(ሮሜ ፲፩÷፳፪)፡፡

የነነዌ ሰዎች መመለስ

የነነዌ ሰዎች ንስሓ እንደማይገቡና በልባቸው ትዕቢት ሞልቶ፤ ከጀመረ ይጨርሰኝ ካፈርኩ አይመልሰኝ፤ብለው በበደላቸው ጸንተው እንደሚኖሩ ሰዎች አልሆኑም ፡፡ ኃጢአታቸውና በደላቸው እንዲሁም ንስሓ ካልገቡ ሊመጣ ያለው ጥፋት ሲነገራቸው በዙፋን ካለው ንጉሥ በዐደባባይ እስካለው ችግረኛ ሁሉም በአንድነት ሆነው ነቢዩ ዮናስ የሰበከውን የንስሓ ስብከት በልቡናቸው አምነው ተቀበሉ፡፡ ማመናቸውንም ከንጉሣቸው ጋር በመሆን ለጾም አዋጅ በመንገር ገለጡ፡፡ እምነታቸውንና ጾማቸውንም በንስሓ አጅበው አለቀሱ፡፡በዚህም እግዚአብሔር ቊጣውን በትዕግሥት መዓቱን በምሕረት ለወጠላቸው ፡፡

 “የነነዌ ሰዎችም እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም አዋጅ ነገሩ፤ ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ፤ንጉሡም ከዙፋኑ ተነሥቶ መጎናጸፊያውን አውልቆ ማቅም ለበሰ፤ በአመድም ላይ ተቀመጠ” (ዮናሰ ፫÷፭-፮) ተብሎ እንደ ተነገረ፡፡ ኃጢአታቸውን አምነው ንስሓ በማይገቡ ሰዎች እግዚአብሔር “የወደቁ አይነሡምን ? የሳተስ አይመለስምን ? ምን አድርጌሃለው ብሎ ከኃጢአቱ ንስሓ የገባ የለም …”(ኤር ፰÷፬) በማለት ይገረማል፤ ይደነቃልም፡፡ የነነዌ ሰዎች ግን በእምነታቸው፤በንስሓቸውና በጾማቸው እግዚአብሔርን አስደሰቱት፡፡ በዚህም በሐዲስ ኪዳን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ንስሓ በማይገቡ ላይ እንደሚፈርዱ ሲመሠክርላቸው “የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሓ ገብተዋልና ብሏል”፤ (ማቴ ፲፪÷፵፩)፡፡ ስለሆነም ከጥፋት እንድንድን ከክፉ ሐሳባችን፤ ንግግራችንና ተግባራችን ተመልሰን ንስሓ እንግባ ፡፡ “የንስሓ ኃዘን መዳንን፤ የዓለምም ኃዘን ሞትን ያመጣልና”፤(፩ ቆሮ ፯÷፲) እምነትን፤ ንስሓንና እውነተኛ ጾምን ገንዘብ አድርገን ለክብር ለመብቃት እንድንችል እግዚአብሔር በቸርነቱ ይርዳን፤ እመቤታችንም በምልጃዋ፤ ቅዱሳንም ሁሉ በጸሎታቸው አይለዩን አሜን!!