የኆኅተ ሰማይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን ለማጠናከር የልማት ሥራ ጥሪ ቀረበ

በድሬዳዋ ኈኅተ ሰማይ ቅድስት ማርያም ሰበካ ጉባኤ ሥር የተቋቋመው የአካባቢ የልማት ኮሚቴ እያከናወነ ያለውን የልማት ሥራ ለማገዝ ሕብረተሰቡ የድጋፍ እጁን እንዲዘረጋ የደብሩ አሰተዳዳሪ ጥሪ አቀረቡ፡፡ ልማት ኮሜቴው ከሦስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር በላይ ውጪ የሚጠይቅ ትምህርት ቤት ግንባታ ጀምሯል፡፡  
የደብሩ አሰተዳዳሪ መጋቢ ካህናት አባ ገብረየሱስ አሻግሬ ሰሞኑን እንደገለጹት፤ ቤተክርስቲያኒቱ ለአካባቢው ምእመናን ከምትሰጠው መንፈሳዊ አገልግሉት በተጓዳኝ በዘላቂ ልማት ራሷን እንድትችል ለተጀመረው ጥረት የልማት ኮሚቴው እንቅስቃሴ ሊበረታታ ይገባዋል፡፡

በልማት ኮሚቴው አማካኝነት ቤተክርስቲያኒቱ ባላት ሰፊ ግቢ ውስጥ ከ1999 ዓ.ም አንስቶ አንድ መዋዕለ ሕፃናትና 1ኛ ደረጃ ት/ቤት አገልግሎት እየሰጠበት መሆኑን የገለጹት አስተዳዳሪው፤ ይህንኑ ት/ቤት አስፋፍቶ እስከ 2ኛ ደረጃ ለማሳደግ ባለ 3ፎቅ ህንፃ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ልማት ኮሚቴው ከከተማው አስተዳደር አስፈቅዶ በቤተ ክርስቲያኒቱ አቅራበያ ከሐረር ቢራ አክሲዮን ማኅበር ባገኘው ሙሉ ድጋፍ የሕዝብ መናፈሻ እየሠራ እንደሚገኝ አስተዳዳሪው ገልፀው፤ ልማት ኮሚቴው እያከናወነ ያለው ተግባር ለቤተክርስቲያኒቱም ሆነ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ጠቃሚ በመሆኑ ሕብረተሰቡ የድጋፍ እጁን እንዲዘረጋ ጠይቀዋል፡፡

የልማት ኮሚቴውና የትምህርት ቤቱ አመራር ቦርድ ጸሐፊ አቶ አደፍርስ ተሾመ በበኩላቸው የኮሚቴው ዋና አላማ ቤተክርስቲያኒቱ በራሷ ቋሚ ገቢ እየታገዘች መንፈ ሳዊ አገልግሎቷን በተሳካ ሁኔታ እንድታከናውን እንዲሁም የአካባቢው ማኅበረሰብ ልጆች የጥሩ ሥነ ምግባርና እውቀት ባለቤት የሚሆኑበትን ትምህርት ቤት ማስፋፋት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዐውደ ምህረት ላይ በአካባቢው ማኅበረሰብ የተቋቋመው 18 አባላት ያለው የልማት ኮሚቴ ከቤተክርስቲያኒቱ ሰበካ ጉባኤ፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብና ከከተማው የመንግሥት ሥራ ሓላፊዎች ጋር በመቀናጀት እቅዱን በተግባር እያዋለ እንደሚገኝ የገለጹት ጸሐፊው፤ ለጥረቱ መሳካት የሕብረተሰቡ ትብብር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኮሚቴው ከኅብረተሰቡ፣ ከባለሀብቶች፣ ከደብሩ ሰበካ ጉባኤ፣ ከልማት ኮሚቴው አባላትና ከመንግሥት ሠራተኞች ባገኘው ድጋፍ ከግማሽ ሚሊዩን ብር በላይ ውጪ አንድ የመዋዕለ ነሕፃናት እና 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ሠርቶ በማጠናቀቅ በአሁኑ ወቅት ከ350 በላይ ተማሪዎችን በጥሩ አገልግሎት እያስተማረ እንደሚገኝ ጸሐፊው ገልጸው ከእነዚህ ውስጥ ከአሁን ቀደም በከተማው ተከስቶ በነበረው የጎርፍ አደጋ ወላጆቻቸውን ያጡና የችግረኛ ቤተሰብ የሆኑ ሃያ ልጆች በነፃ እየተማሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የኮሚቴው ራእይ ይህንን ት/ቤት እስከ ኮሌጅ ማድረስ መሆኑን የገለጹት ጸሐፊው በአሁኑ ወቅት እስከ 10ኛ ክፍል ማስተማር የሚያስችል ባለ 3 ፎቅ ሕንፃ ግንባታ ተጀምሮ መሠረት ወጥቶለት የመጀመሪያው ፎቅ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ግንባታውን ለማጠናቀቅ ከሦስት እስከ አራት ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ አሁን ባለው ሁኔታ ኮሜቴው ይህንን ሕንፃ ለመቀጠል ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት እንዳለበት ጸሐፊው ገልጸዋል፡፡ በመ ሆኑም  የአካባቢው ማኅበረሰብ፤ በሀገር ውሰጥ እና በውጭ ያሉ በጎ አድራጊዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

የእርዳታ እጃቸውን መዘርጋት ለሚፈልጉ በቅድስት ማርያም መዋዕለ ሕፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ስም በተከፈተው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድሬደዋ ዐቢይ ቅርንጫፍ የባንክ ሒሳብ ቁጥር 4076 ቢልኩ እንደሚደርስም ጠቁመዋል፡፡