የትዕግሥት ፋና
በመዝሙርና ሥነ ጥበባት ክፍል
ግንቦት ፪፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
ዖፅ በሚባል አገር
በቅን ፍፁም ሲኖር
በጽድቁ የቀና
ሰይጣን ጠየቀና
አምላክ ሊያሳውቀው
ጻድቁን ቢገልጠው
ጠላቱን ሰደደው
ዱብዳ አውርዶ
ሊያስክድ አስገድዶ
ከሞት ያመለጠኮ
መልእክተኛ ልኮ
ብላቴኖችህ በስለት ወደቁ
በሬዎች በጐችህ ተጋዙ ጻድቁ
ከዚያም ምድረ በዳ
በነፈሰው ነፋስ
ቤታቸው ተንዶ
በአፍላ ሳያረጁ…
አለቁ ልጆችህስ
ይሄንን ነገረው…
ባንድ ቀትር ጊዜ
ሀብቱን አሟጠጠው
ለጤናው ትካዜ
በገል አሳከከው
አምላክን መፍራትህ
ጽድቅን መፈጸምህ
ከራሱ አጣልቶ…
የታለ እያለው
ከጌታው ሊለየው
ቆስሎ እያከከው፡፡
ምንም ሳይደነቅ
ስለምን መጣብን
ብሎ ሳይጨነቅ
ከእናቱ ማኅፀን
ባዶውን መውጣቱ
ባዶውን መሄዱ…
ከሚጠፋው ከንቱ
በልጦ ማንነቱ
መራራው መከራ…
በአንደበትህ ጣፍጦ
እግዚአብሔር ይመስገን…
ስትል ተለውጦ
ጠላትህ አፈረ
በንዳድ ጠቆረ፡፡
ከወርቅ የነጠረ
ኢዮብ ጻድቅ ሰው ነው
ምክር የመከረ
ኢዮብ ፍጹም ሰው ነው
የትዕግሥት ፋና
በገድል የከበረ!