የትሩፋት ሥራ በቆጠር ገድራ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

መጋቢት ፳፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

አሁን የምንገኝበት የዐቢይ ጾም ሳምንት ስለ ገብር ኄር (ታማኝ አገልጋይ) እና ገብር ሐካይ (ሰነፍ አገልጋይ) የሚነገርበት ወቅት ነው፡፡ ይኸውም ስለ አገልግሎት ትርፋማነትና ዋጋ የምንማርበት ሳምንት ነው፡፡ በተሰጣቸው መክሊት እጥፍ አትርፈው እንደ ተወደሱት ታማኝ አገልጋዮች እኛ ምእመናንም በሃይማኖት ጸንተን፣ በክርስቲያናዊ ምግባር ጎልምሰን እግዚአብሔር እንደየአቅማችን በሰጠን ልዩ ልዩ ጸጋ ተጠቅመን መንፈሳዊ ትርፍ ካስመዘገብን ከአምላካችን ዘንድ ዋጋ እናገኛለን፡፡ በአንጻሩ በሃይማኖታችን ካልጸናን፣ በክርስቲያዊ ምግባር ካልበረታን፣ ጸጋችንን እንደ ሰነፉ ባርያ ደብቀን መንፈሳዊ ትርፍ ካላስመዘገብን እጣ ፋንታችን ቅጣት ይኾናል፡፡

በምድራዊው ሕይወታችን የተሰጠንን ጸጋ ደብቀን ያለ ምግባር የምንኖር ምእመናን ብዙ የመኾናችንን ያህል፣ ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ከሚበሉት ቈርሰው፣ ከሚጠጡት ቀንሰው፣ ከሚለብሱት ከፍለው ለችግረኞች የሚደርሱ፤ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መፋጠን የሚሽቀዳደሙ፤ በሚጠፋ ገንዘባቸው የማያልፈውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ የሚተጉ በጎ አድራጊ ምእመናንም አይታጡም፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን እግዚአብሔር አምላክ በሰጣቸው ልዩ ልዩ ጸጋ ለማትረፍ የተነሡ፣ እንደ ልጅነታቸው ቤተ ክርስቲያን የምትጠብቅባቸውን ክርስቲያናዊ ሓላፊነት ለመወጣት የወሰኑ በጎ አድራጊ ምእመናን በቆጠር ገድራ መካነ ቅዱሳን ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ገዳም በማከናወን ላይ የሚገኙትን አርአያነት ያለው የትሩፋት ሥራ ልናስታውሳችሁ ወደድን፡፡ በመጀመርያም የገዳሙን ታሪክ በአጭሩ እናቀርባለን፤

‹ቆጠር› የሚለው ቃል ቦታውን የመሠረቱት ግለሰብ ስም ሲኾን፣ በጊዜ ሒደት ቃሉ የጎሣ መጠርያ ኾኖ ቀጥሏል፡፡ ‹ገድራ› በአካባቢው ቋንቋ የዛፍ ዓይነትን የሚያመለክት ቃል ነው፡፡ አካባቢው ‹ገድራ› የተሰኘው ዛፍ የሚበዛበት በመኾኑ ቦታው ‹ቆጠር ገድራ› ተብሎ ይጠራል፡፡ አካባቢው በተፈጥሮ ደን የተከበበ ሥፍራ ሲኾን፣ ነዋሪዎቹ ከዚህ ደን ውስጥ ዕፀዋትን እንዳይቆርጡ ቃል ኪዳን ገብተዋል፡፡ ስለዚህም የደኑ ህልውና ተጠብቆ ይኖራል፡፡ የቆጠር ገድራ መካነ ቅዱሳን ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ገዳምም በዚህ ቦታ የተመሠረተ ጥንታዊ ገዳም ነው፡፡ ገዳሙ ከጉራጌ ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና ወልቂጤ ከተማ በአምሳ ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡

በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የነበሩ የአካባቢው ምእመናን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ሊያስገነቡ ቦታዎችን መርጠው ዕጣ ሲጥሉ ዕጣው በተደጋጋሚ ‹ይነኹራ› ለተባለው ቦታ ወጣ፡፡ በዚያ ሥፍራም በመድኃኔ ዓለም ስም ቤተ ክርስቲያን አነጹ፡፡ ይህ ቤተ ክርስቲያን በዕድሜ ብዛት በመጎዳቱ በየጊዜው ዕድሳት እየተደረገለት እስከዛሬ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ለበርካታ ሕዝበ ክርስቲያን አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ በወቅቱ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የዚህን ሕንጻ የመሠረት ድንጋይ ለማስቀመጥ በ፳፻፪ ዓ.ም ወደ ቦታው በሔዱ ጊዜ ‹ቆጠር ገድራ› ከሚባለው ደናማ ሥፍራ ሲደርሱ በቦታው በመማረካቸው ከደኑ ውስጥ ገብተው ‹‹ገዳም ገዳም ሸተተኝ፤ ከዚህ ቦታ አልወጣም›› አሉ፡፡ ከጥቂት ሰዓታት ቆይታ በኋላ ጉዟቸውን ቀጥለው ይነኹራ መድኃኔ ዓለም ደርሰው ትምህርተ ወንጌልና ቃለ ቡራኬ ሰጥተው ‹‹ዛሬ ከዚህ ቦታ ላይ የመሠረት ድንጋይ እንዳኖር እግዚአብሔር አልፈቀደልኝም›› ብለው የመሠረት ድንጋዩን ሳያስቀምጡ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ተመለሱ፡፡

በሌላ ጊዜ ከሕዝበ ክርስቲያኑ ጋር ውይይት አካሒደው በዕድሳት መልክ በድጋሜ ከሚታነጸው ይነኹራ መድኃኔ ዓለም በተጨማሪ በቆጠር ገድራም በኪዳነ ምሕረት ስም ቤተ ክርስቲያን እንዲታነጽ አዘዙ፡፡ ብፁዕነታቸው ፍጻሜውን ሳያዩ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ ቢያርፉም በጥቅምት ወር ፳፻፫ ዓ.ም እርሳቸው በመረጡት ቦታ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ ነሐሴ ፲፮ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም የቤተ ክርስቲያኑ ቅዳሴ ቤት ከበረ፡፡ በቆጠር ገድራ በአንድ ወቅት በተደረገ ቁፋሮ ሰባት ጥንታውያን የዋሻ ቤተ መቅደሶች፣ ሦስት የሱባዔ መያዣ ቦታዎችና ልዩ ልዩ ንዋያተ ቅድሳት ተገኝተዋል፡፡ ይህም በዚያ ሥፍራ ቀደም ሲል ቤተ ክርስቲያን ታንጾ እንደ ነበር የሚጠቁም ማስረጃ ነው፡፡ በቁፋሮ የተገኙ ሰባቱ የዋሻ ቤተ መቅደሶችም፡- የደብረ ቢዘን ቤተ መቅደስ፣ ቤተ ጎልጎታ፣ ቤተ መድኅን፣ ቤተ ጠበብት፣ ቤተ ኤፍራታ፣ ቤተ ደብረ ብርሃን እና ቤተ ደናግል ይባላሉ፡፡

ከእነዚህ ቤተ መቅደሶች መካከል በቤተ ጎልጎታ የኦሪት መሥዋዕት ይቀርብበት እንደ ነበረ፤ በውስጡም ከወርቅ የተሠራ መሠዊያ እንደ ተገኘና ይህን መሠዊያም በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሥፍራው ሲያገለግሉ የነበሩ አባ ማትያስ የተባሉ አባት እንዳይዘረፍ ብለው ቆፈረው እንደ ቀበሩት የአካባቢውን ታሪክ የሚያውቁ አባቶች ይናገራሉ፡፡ የቦታው ታሪክና የንዋያተ ቅድሳቱ ዝርዝርም በቁፋሮው በወጣው ‹ዝንቱ መጽሐፍ ዘአቡነ ማትያስ› በተባለው የብራና መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ በቁፋሮ የወጡት የወርቅ መሠዊያ፣ የብራና መጻሕፍት፣ ቅዱሳት ሥዕላት፣ እርፈ መስቀል እና ሌሎች ጥንታውያን ንዋያተ ቅድሳት ቤተ መዘክር እስከሚሠራላቸው ድረስ እንዳይጠፉ በምሥጢር እንዲጠበቁ ተደርገዋል፡፡ በዚህ ሥፍራ ከአሁን በፊት ያልወጡና ወደ ፊት በቁፋሮ የሚገኙ ንዋያተ ቅድሳት እንዳሉም ይታመናል፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም በገዳሙ የፈለቁት፣ በአምስት ቅዱሳን ማለትም በኪዳነ ምሕረት፣ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ፣ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እና አባ ማትያስ ስም የተሰየሙት ጠበሎች ለበርካታ ሕሙማን ፈውስ እየሰጡ ተአምራትን እያሳዩ ነው፡፡ በቍጥር ወደ ፳፪ የሚደርሱ የሌላ እምነት ተከታዮችም በገዳሙ ጠበሎች ከሕመማቸው ተፈውሰው፣ የክርስትና ጥምቀትን ተጠምቀው የሥላሴን ልጅነት አግኝተዋል፡፡

ምንጭ፡

  • የማኅበረ ቅዱሳን ኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚድያ ዋና ክፍል፤
  • የገዳሙ ሕንጻ አሠሪ ኰሚቴ ያሳተመው በራሪ ወረቀት፤
  • የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም እና መንግሥት ኮሚኒኬሽን፡፡
img_0748

መርሐ ግብሩ በጸሎተ ወንጌል ሲከፈት

የዚህ ዅሉ ታሪክ ባለቤት ለኾነችው ቆጠር ገድራ መካነ ቅዱሳን ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ገዳም ደረጃውን የጠበቀ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን፣ የአብነት ት/ቤት፣ የካህናት ማሠልጠኛ ተቋም እና ቤተ መዘክር ለመሥራት እግዚአብሔር ያስነሣቸው የአካባቢው ተወላጆች ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ፈቃድ አግኝተው በመፋጠን ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ በጎ አድራጊ ምእመናን ከሀገረ ስብከቱና ወረዳ ቤተ ክህነቱ ጋር በመተባበር ገዳሙን የትምህርትና የልማት ማእከል ለማድረግ እንቅስቃሴ ላይ ናቸው፡፡ የገዳሙን ታሪክ ለትውልድ ለማስተላለፍ ያመች ዘንድ ሰባክያነ ወንጌልንና አስጐብኚዎችን ለመመደብም ታቅዷል፡፡

003

በአጠቃላይ ገዳሙን ወደ ጥንት ስሙና ታሪኩ ለመመለስ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በዚህ መልካም የትሩፋት ሥራም የሕንጻዎቹን ዲዛይን በነጻ በመሥራትና ኰሚቴውን በማስተባበር፣ እንደዚሁም ዓላማውን በማስተዋወቅ ማኅበረ ቅዱሳን ድጋፍ በማድረግ ላይ ሲኾን፣ ማኅበረ ጽዮንም ሌላው አጋር አካል ነው፡፡ ለዚህ መልካም ተግባር የተቋቋመው ሕንጻ አሠሪ ኰሚቴም ለታቀዱት ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች ገቢ በማሰባሰብ መንፈሳዊ ተልእኮውን በአግባቡ እየተወጣ ነው፡፡ ኰሚቴው ካከናወናቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብራት መካከልም የካቲት ፳፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ቦሌ አየር ማረፊያ አካባቢ በሚገኘው ዮድ አቢሲንያ የባህል ምግብ አምባሳደር ያደረገው ልዩ መርሐ ግብር አንዱ ነው፡፡

img_0795

የመርሐ ግብሩ ታዳሚዎች በከፊል

በጸሎተ ወንጌል በተከፈተው በዚህ መርሐ ግብር በካህኑ የተነበበው፣ በዓለ ደብረ ታቦርን የሚመለከተው፣ ‹‹… ሦስት ዳስ እንሥራ …›› የሚለው ኃይለ ቃል የሚገኝበት የወንጌል ክፍል ከገዳሙ የልማት ሥራ ጋር የሚተባበር ምሥጢር አለው (ማቴ. ፲፯፥፩-፬)፡፡

img_0809

መምህር አባ ኤልሳዕ ከደቀ መዛሙርታቸው ጋር ኾነው የአብነት ሥርዓተ ትምህርትን በተግባር ሲያሳዩ

በዕለቱ የገዳሙ አስተዳዳሪ መምህር አባ ኤልሳዕ ከደቀ መዛሙርታቸው ጋር ተገኝተው ንባብ፣ ዜማ፣ ቅኔ፣ የመጻሕፍት ትርጓሜ እና የአቋቋም ሥርዓተ ትምህርትን ለመርሐ ግብሩ ታዳሚዎች በተግባር አሳይተዋል፡፡

img_0757

ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ ትምህርተ ወንጌል ሲሰጡ

ዲ/ን ብርሃኑ አድማስም ‹‹የመስጠትና የመቀበል ስሌት›› (ፊልጵ. ፬፥፲-፳) በሚል ኃይለ ቃል ገንዘብንም ኾነ ሌላ ንብረትን ለመንፈሳዊ ዓላማ ማዋል ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያሰጠውን ልዩ ጸጋና የሚያስገኘውን ጥቅም ቅዱሳት መጻሕፍትን ዋቢ በማድረግ አስተምረዋል፡፡

ቀሲስ ምንዳዬ ብርሃኑ እና መጋቤ ስብሐት ዓለሙ አጋ ደግሞ መዝሙር አቅርበዋል፡፡

img_0753

ቀሲስ ምንዳዬ ብርሃኑ መዝሙር ሲያቀርቡ

img_0779

መጋቤ ስብሐት ዓለሙ አጋ በገና ሲደረድሩ

የመርሐ ግብሩ መሪ ዲ/ን ደረጀ ግርማ በበኩላቸው በበጎ አድራጊ ምእመናን የተጀመረው ይህ ገዳሙን የማሳደግ ሥራ ዓላማው በየጊዜው እየቀዘቀዘ የመጣውን የአብነት ትምህርት ለማስፋፋት፣ ጥንታውያን ቅርሶችን በመጠበቅ ለትውልድ ለማስተላለፍ፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለማሳደግ እና ስብከተ ወንጌልን በስፋት ለማዳረስ መኾኑን አስገንዝበዋል፡፡

img_0815

የሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ዲዛይን ተመርቆ ሲከፈት

የገዳሙን ታሪክ የሚያስቃኝ ዘጋቢ ፊልምም ሌላው የመርሐ ግብሩ አካል የነበረ ሲኾን የኰሚቴው ሰብሳቢ እና የዮድ አቢሲንያ የባህል ምግብ አምባሳደር ባለቤት አቶ ትእዛዙ ኮሬ ‹‹የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፤ እኛ በርያዎቹም ተነሥተን እንሠራለን›› በሚል ርእስ በዘገባ መልክ የኰሚቴውን እንቅስቃሴ ለጉባኤው አስረድተዋል፡፡ በዚህ መርሐ ግብር በገዳሙ ሊሠራ የታቀደው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን፣ ዘመናዊ የአብነት ት/ት ቤት እና የቤተ መዘክር ዲዛይን በአባቶች ቡራኬ ተመርቋል፡፡ በመርሐ ግብሩ የታደሙ ምእመናንም ለዚህ መልካም ሥራ በመሽቀዳደም የሚችሉትን ዅሉ ለማድረግ ቃል ከመግባታቸው ባለፈ በዕለቱ በሚሊዮን የሚቈጠር ገንዘብ ገቢ አድርገዋል፡፡ የሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ዲዛይን በከፍተኛ መንፈሳዊ ፉክክር በአንድ መቶ ሃያ ሺሕ ብር ጨረታ መሸጡም ብዙዎችን አስደንቋል፡፡ ይህም ሕዝበ ክርስቲያኑ ገንዘቡን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ለማዋል ያለውን ቍርጠኝነት ያሳያል፡፡

001-copy

ይህን የትሩፋት ሥራ በመደገፍና በማስተባበር የተሳተፉ አካላትን ዅሉ የኰሚቴው ሰብሳቢ አቶ ትእዛዙ ኮሬ በእግዚአብሔር ስም አመስግነው የአካባቢው ተወላጆች ሥራውን ቢጀምሩትም ሓላፊነቱ ግን ለዅላችንም ነውና እያንዳንዱ ምእመን እግዚአብሔር ከሰጠው ገንዘብ ላይ ዐሥራት በማውጣት የገዳሙን ልማት መደገፍ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ በመቀጠል በዕለቱ የተሰበሰበውን ገንዘብ ያበረከቱ ምእመናንን ሰብሳቢው ካመሰገኑ በኋላ ይህ ገቢ ለታቀደው ልዩ ልዩ ተግባር በቂ ስለማይኾን መላው ሕዝበ ክርስቲያን በያሉበት ርብርብ እንዲያደርጉና የገዳሙን ልማት በጋራ እንዲደግፉ በኰሚቴው አባላት ስም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ መርሐ ግብሩም በአባቶች ጸሎት ተፈጽሟል፡፡

img_0774

አቶ ትእዛዙ ኮሬ የኰሚቴውን የሥራ እንቅስቃሴ ሪፖርት ሲያደርጉ

በቆጠር ገድራ መካነ ቅዱሳን ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ገዳም ሊሠራ የታቀደውን መንፈሳዊ ተግባር በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በቁሳቁስ ወይም በሐሳብ ለመደገፍ የምትፈልጉ ምእመናን በስልክ ቍጥር፡- 09 11 72 27 93 ወይም 09 21 06 23 82 በመደወል ተጨማሪ መረጃ መጠየቅና ድጋፍ ማድረግ የምትችሉ መኾኑን ኰሜቴው ያሳስባል፡፡ እኛም እንደ ዝግጅት ክፍል የኰሜቴው ሥራና የምእመናኑ ተሳትፎ አርአያነት ያለው፣ ሊበረታታ የሚገባው ተግባር በመኾኑ ይህን መንፈሳዊ እንቅስቃሴ በዚህ መልኩ አስታወስናችሁ፡፡ በመጨረሻም ይህን የትሩፋት ሥራ በመደገፍ የሚጠበቅብንን የልጅነት ድርሻ እንወጣ በማለት መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡