የቱን ታስታውሳላችሁ?
የጥያቄዎቹ ምላሾች

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ነሐሴ ፳፰፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? በየዓመቱ በጉጉት የምጠብቃት ጾመ ፍልሰታ እንዴት አለፈ? እንዴት አቅማችን በመጾም፣ በመጸለይ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከቤዛዊት ዓለም በረከትን ተቀብለን እንዳለፍንበት ተስፋችን እሙን ነው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ከጾመ ፍልሰታ በፊት “የቱን ታስታውሳላችሁ?” በሚል ርእስ ስንማራቸው ከነበሩ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር መካከል የተወሰነ ጥያቄዎችን ጠይቀናችሁ እናንተም ምላሹን ልካችሁልን ነበር፤ ለጥያቄዎቹ ተገቢውን ምላሽ ለሚሰጡም እንደተለመደው ሽልማቶችን እንደምናዘጋጅ ነግረናችሁ ነበር፡፡ የሽልማት መርሐ ግብሩን በተለየ መርሐ ግብር እናዘጋጃለን፡፡

በ “የቱን ታስታውሳላችሁ?” መርሐ ግብራችን ላቀረብናችሁ ጥያቄዎች ትክክለኛ ምላሾች የሚከተሉት ናቸው፡፡

፩. ውድ ልጆች! እርሱን የያዘ ሰው ድሀ ሀብታም፣ ኃጥእ፣ ጻድቅ ሳይል ሁሉን እኩል ይወዳል፤ በፍጹም ልቡ እርሱን የያዘ ጻድቅ ነው ብሎ አይወድም፤ ኃጥእ ብሎ አይጠላም፤ እኩል ይወዳል፤ በሰዎች ክፉ አያደርግም፤ ክፉ አያደርግበትም፤ ወንድሙ ሲያጠፋ ቢያየው እንኳን ይመክረዋል፤ ገበናውን ይሸፍንለታል፤ አሳልፎ አይሰጠውም፤ ለራሱ ብቻ ጥፋቱን ይነግረዋል፡፡ ታዲያ እርሱ ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ ትክክለኛው ምላሽ ‹‹ፍቅር›› ነው፡፡ በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ትምህርታችን ስለ ፍቅር በጥልቀት ተምረናል ፤ያንን ማስታወሻ ደግማችሁ በማንበብ ስለ ፍቅር የበለጠውን ግንዛቤን ያዙ፡፡

፪.አባቱ ያዕቆብ ለወንድሞቹ ስንቅ አድርስ ብሎ ላከው፤ መንገዱ ሩቅ ስለነበር በጣም ደከመው፤ በዚያም ላይ ራበው፤ የያዘውን ምግብ እንዳይበላ ደግሞ የወንድሞቹ ነው፤ የሚበላ ይዞ ተራበ፤ ለአባቱ በመታመን ለወንድሞቹ አድርስ የተባለውን ቢርበውም አልበላውም፤ በዚህም የተነሣ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና በተአምራት ድንጋዩን ዳቦ አድርጎለት በላ፤ እርሱ ማን ነው? ያደረገለት ‹‹ዮሴፍ›› ይባላል፡፡

፫. ከንጉሣቸው ታዘው ሊይዙት የመጡትን የሶርያ ንጉሥ ወታደሮችን በእግዚአብሔር ቸርነት ማርኮ ከእስራኤሉ ንጉሥ ዘንድ ወሰዳቸው፤ ምንም እንኳን እነርሱ ሊገድሉት ቢመጡም እርሱ ግን ይቅርታን በማድረግ እንጀራ በልተው በሰላም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አደረገ፤ እርሱ የእግዚአብሔር ነቢይ የሆነ ማን ነው? ‹‹ነቢዩ ኤልሳዕ›› ነው፡፡

፬. እምነቱ፣ ታጋሽነቱ ይለካ (ይታይ) ዘንድ ንብረቱ ወደመበት፤ እንደገናም ልጆቹ ሞቱበት፤ ይህም ብቻ አይደለም፤ እርሱ ራሱ በጣም ለብዙ ዘመን ታመመ፤ እግዚአብሔር እየረዳው ሁሉን በትዕግሥት አሳለፈ፤ ከዚህ ሁሉ መከራ በኋላ እግዚአብሔር አዳነው፤ ሀብት ንብረቱንም ሰጠው፤ ለትዕግሥት (ለመታገስ) ምሳሌ አድርገው የሚጠሩት ‹‹ጻድቁ ኢዮብ›› ይባላል፡፡

፭. ስለ መታዘዝ በተማራችሁት መሠረት በአጭሩ ግለጹ!
መልስ፡- መታዘዝ “እሺ” ማለት፣ የተሰጠን ኃላፊነት መፈጸም” ነው፡፡ በትእዛዝ ውስጥ አድርጉ እና አታድርጉ የሚሉ መልእክቶች (መመሪያዎች) አሉ፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር እንድንፈጽመው (እንድናደርገው) ያዘዘን እንዳለ ሁሉ እንዳናደርገው ያዘዝን ትእዛዝም አለ፡፡ ለምሳሌ ብንወስድ አትስረቅ የሚል ትእዛዝ እንዳናደርገው (ስርቆትን እንዳንፈጽመው ) የተከለከልነው ትእዛዝ ነው፡፡ የእኛ ያልሆነውን እንዳንነካ፣ እንዳንወስድ፣ እንዳንመኝ ተከልክለናል (ታዘናል)፡፡ እንድናደርገው ከታዘዝነው ትእዛዝ ለአብነት (ለምሳሌ) ብንመለከት ‹‹ሰንበትን አክብር ….ባልንጀራህን ውደድ…›› እነዚህን የመሳሰሉ ደግሞ ልናደርጋቸው የሚገቡ ትእዛዛት ናቸው፡፡

፮. የእስራኤል ንጉሥ በነበረበት ጊዜ ከቤተልሔም ምንጭ ውኃ መጠጣት ፈለገ፤ “ከቤተልሔም ምንጭ ውኃ ማን ባጠጣኝ” ሲልም ተመኘ፤ በዚህ ጊዜ የጭፍሮቹ አለቆች አዲኖን፣ ኢያቡስቴ እና ኤልያና ለእርሱ ካላቸው ፍቅር የተነሣ ወደ ጠላቶቻቸው ጦር ሄደው፣ ውኃውን ቀድተው አመጡለት፤ ለእርሱም ፍቅር ብለው ደማቸውን ለማፍሰስ መድፈራቸውን ተገንዝቦ ወንድሞቹ ያመጡለትን ውኃ አልጠጣም ብሎ ውኃውንም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት በማድረግ ያፈሰሰው ‹‹ንጉሥ ዳዊት›› ነው፡፡

፯.ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ያስነሣው አልዓዛር የተባለው ሰው እኅቶች መልካም ምግባር የነበራቸው ጌታችንም ይወዳቸው የነበሩ ማርያም እና ማርታ ይባላሉ፡፡

፰. ባላጠፋችው በሐሰት (በውሸት) ተከሳ ለፍርድ ቀረበች! ምስክሮቹ በውሸት መሰከሩባት፤ ያለ ጥፋቷም ሊትቀጣ ስትል እግዚአብሔር ነቢዩ ዳንኤልን ልኮ የሐሰተኛ ምስክሮችንና ክፉ ሥራቸውን አጋለጠ፤ እርሷም ከመቀጣት ዳነች፤ ሐሰተኞቹ ግን ተቀጡ፡፡ ውድ ልጆች መዋሸት ጥሩ አይደለም እሺ! እግዚአብሔር ከሐሰተኛ ምስክሮች የጠበቃት ‹‹ሶስና›› ትባላለች፡፡

፱. እግዚአብሔር በልጅነቱ ንጉሥ አድርጎ ሾመው፤ ንጉሥ ሳኦል የተባለው በእርሱ ቀንቶ ብዙ ጊዜ ሊገድለው ሞከረ፤ እግዚአብሔር ግን አዳነው፤ ሁለት ጊዜ ሊገድሉት የመጣውን ንጉሥ ሳኦልን አግኝቶ ምንም ሳያደርገው በይቅርታ አለፈው፤ ውድ ልጆች! እግዚአብሔር እንደልቤ በማለት የሚጠራው የእስራኤል ንጉሥ ‹‹ንጉሥ ዳዊት›› ይባላል፡፡

፲. አባ ባይሞን ታዛዥነቱን ለማየት የደረቀ እንጨት ተክሎ ውኃ እንዲያጠጣ አዘዘው፤ እርሱም የመምህሩን ትእዛዝ በመቀበል ለሁለት ዓመታት ያንን ደረቅ እንጨት ውኃ አጠጣው፤ በሦስተኛውም ዓመት እግዚአብሔር ታዛዥነቱን ተመልክቶ የደረቀው እንጨት ፍሬ እንዲያፈራ ያደረገለት ጻድቅ ‹‹ዮሐንስ ሐጺር›› ይባላል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ትማሩት ከነበረው ትምህርት “የቱን ታስታውሳላቸሁ?” በሚል ጥቂቱን ብቻ ጠየቅናችሁ፤ ምላሻችሁን እንጠብቃለን፡፡ እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍቅር ልዩ ነው! ውለታውን ሳንረሳ ትእዛዙን በመጠበቅ እኛ ደግሞ ለእርሱ ያለንን ፍቅር እንግለጽ፡፡ ወላጆቻችን ለእኛ ብዙ ነገር እያደረጉልን በትምህርታችን ጎበዝ ስንሆን፣ በሥነ ምገባር ስንታነጽ ደስ እንደሚላቸው እኛም ፈጣሪ እግዚአብሔር ያዘዘንን ትእዛዝ በመፈጸም ለእርሱ ያለንን ፍቅር እንግለጥ፡፡

ቸር ይግጠመን!!!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!