የቱን ታስታውሳላችሁ?
የጥያቄዎቹ ምላሾች
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ታኅሣሥ ፳፰፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ! ነቢያት በብሉይ ኪዳን “አቤቱ ከሰማያት ወርደህ፣ ተወልደህ አድነን” ብለው የተነበዩት ትንቢት ተፈጽሞ አምላካችን ቅዱስ እግዚአብሔር ወልድ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደበትን ቀን በድምቀት እናከብር ዘንድ ይገባል፡፡
ልጆች! ለዛሬ “የቱን ታስታውሳላችሁ?” በሚለው ላቀረብንላችሁ ጥያቄዎች ምላሾቹን ይዘን ቀርበናል፡፡ አንብባችሁ ምላሽ የሰጣችሁ በርቱ! ያልመለሳችሁ ደግሞ በቀጣይ በምናዘጋጀው ጥያቄና መልስ ተሳተፉ!
ለሚከተሉት ጥያቄዎች ትክክለኛውን ምላሾች ምረጡ!
……፩. የቅዱሳን አማላጅነት ያስፈለገበት ምክንያት ———————–ነው፡፡
ሀ. እግዚአብሔር ከኃጥአን-ጸሎት ይልቅ የወዳጆቹ የቅዱሳንን ጸሎት ስለ ሚቀበል
ለ. ጸሎታችን በፍጥነት ወደ እግዚአብሔር እንዲደርስልን
ሐ. ፈጣሪያችንም ስለ እነርሱ ሲል ቸርነቱን ስለሚያደርግልን ነው፡፡
መ. ሁሉም መልስ ነው
…… ፪. በአማላጅነት ተግባር ውስጥ መኖር ያለበት ———————–ነው፡፡
ሀ. አማላጅና የሚማለድለት ለ.ተማላጅ
ሐ. ሀ እና ለ መልስ ናቸው፡፡ መ. መልሱ የለም
…… ፫. ለተጠማ ሰው ውኃ አጠጥቶ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያማለደችውና ከመከራ የታደገችው ሰው ማን ይባላል?
ሀ. አብርሃም ለ. ነዌ
ሐ. አልአዛር መ. ስምዖን ( በላዔ ሰብእ)
….. ፬. ለእግዚአብሔር ቅድስናው——————
ሀ. የጸጋ ነው ለ. የባሕርይ ገንዘቡ ነው
ሐ. ከማንም ያልተቀበለው ነው መ. ለ እና ሐ መልስ ናቸው
——–፭. ‹‹…በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ …›› (፪ኛ ቆሮ. ፭፥፲፱) የሚለው ኃይለ ቃል ምንን ያመለክታል፡፡
ሀ. የቅዱሳንን አማላጅነት ለ. አማላጅነትን የፈቀደው እግዚአብሔር እንደሆነ
ሐ. አማላጅ እንደማያስፈልግ መ. ሀ እና ለ
ለሚከተሉት ጥያዌዎች ትክክለኛውን ምላሽ ጻፉ!
፮. እመቤታችን ከልጇ አማልዳ ጌታችን ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ የቀየረበት ቦታ ምን ይባላል?
መልስ፡-ቃና ዘገሊላ ይባላል፤ጌታችን እመቤታችን እንዲሁም ቅዱሳን ሐዋርያት በዶኪማስ ሠርግ ቤት በነበሩ ጊዜ ለሰው የሰጡት ወይን ጠጅ አለቀባቸው እመቤታችንም ከልጇ ከጌታችን አማልዳ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ እንዲቀይርላቸው አደረገች፡፡ (ዮሐ.፪፥፩-፲፩)
፯. አማላጅ ማለት ምን ማለት ነው? ቅዱሳን ያማልዳሉ ስንል ምን ማለት ነው? ይህንን ከተማራችሁት በአጭሩ አብራሩ!
መልስ፡-አማላጅ ማለት፡- ስለሌላው የሚጸልይ፣ የሚለምን ማለት ነው፤ ቅዱሳን ያማልዳሉ ስንል በኃጥአን ፈንታ ስለ ኃጥአን ወደ እግዚአብሔር ምልጃን ያቀርባሉ፡፡ የሚማለደው (የሚለመነው) እግዚአብሔር የአማላጁን (የቅዱሳንን) ጸሎት፣ልመና ተቀብሎ የፈቃዱን የቸርነቱን ሥራ ለሚማለድላቸው ሰዎች ያደርጋል፡፡
፰. የቅዱሳን አማላጅነት ያስፈለገበት ምክንያት ምንድን ነው?
መልስ፡–የቅዱሳን አማላጅነት ያስፈለገበት ምክንያት እግዚአብሔር ከኃጥአን-ጸሎት ይልቅ የወዳጆቹ የቅዱሳንን ጸሎት ስለሚቀበል ጸሎታችን በፍጥነት ወደ እግዚአብሔር እንዲደርስልንና ፈጣሪያችንም ስለእነርሱ ሲል ቸርነቱን ስለሚያደርግልን ነው፡፡ ለአብነት ብንመለከት እግዚአብሔር የቅዱሳንን ጸሎት እንደሚሰማና ምልጃቸውም ግዳጅ ፈጻሚ መሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ተገልጿል፤ ‹‹…ኢዮብም ስለ ወዳጆቹ በጸለየ ጊዜ እግዚአብሔር ምርኮውን መለሰለት…›› (ኢዮ.፵፪፥፲)
፱. የቅዱሳንን በዐጸደ ሥጋ አማላጅነትን ከተማራችሁት ጠቅሳችሁ ጻፉ!
መልስ፡–አብርሃም በሰዶምና በገሞራ ያሉ ሰዎች በበደላቸው መከራ እንደሚመጣባቸው ሲነገረው ስለእነርሱ ከእግዚአብሔር ምሕረትን ለምኗል፡፡ (ዘፍ.፲፰÷፲፮-፴፫)
ቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ ለወገሩት ሰዎች ምሕረት ለመነላቸው፡፡ ‹‹…ተንበርክኮም ጌታ ሆይ ይህንን ኃጢአት አትቁጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ይህንንም ብሎ አንቀላፋ ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር፡፡ (የሐዋ.ሥ.፯÷፷)
፲. አቤሜሌክ የተባለን ሰው እግዚአብሔር በሕልሙ ተገልጾ ጥፋት እንዳያጠፋ፣ ሊሠራ ስላሰበው በደል ግን ‹‹…ነቢይ ነውና ስለ አንተም ይጸልያል፤ ትድናለህም..›› በማለት ወደ እግዚአብሔር ጸልዮ ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ መሥዋዕትን ወደ እግዚአብሔር አቅርቦለት በደሉ ይቅር እንዲባል ያደረገ ቅዱስ ማን ነው?
መልስ፡- አባታችን አብርሃም ነው፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ትማሩት ከነበረው ብዙ ትምህርት “የቱን ታስታውሳላቸሁ” በሚል ለጠየቅናችሁ ጥያቄዎች ምላሾቹ እነዚህ ናቸው፡፡
በሌላም ጊዜ ከምንነግራችሁ ታሪክ እንዲሁም መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ምን ያህሉን እንደተረዳችሁ ለማወቅ ጥያቄ ይዘን እንመጣለን፡፡ ወላጆቻችን ለእኛ ብዙ ነገር እያደረጉልን በትምህርታችን ጎበዝ ስንሆን፣ በሥነ ምግባር ስንታነጽ ደስ ይላቸዋልና በርትታችሁ ተማሩ፤ በሌላ ትምህርት እስክንገናኝ ቸር ይግጠመን!!!